1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

የፈረንሳይ ፕሬዝዳንታዊ ምርጫ ሂደትና ውጤት

ማክሰኞ፣ ሚያዝያ 4 2014

ኢማኑኤል ማክሮና ማሪ ለፔን ለሁለተኛ ጊዜ የሚፎካከሩበት የዘንድሮው የፈረንሳይ ምርጫ ውጡት አጓጉቷል። በቅርብ ዓመታት የፈረንሳይ ፕሬዝዳንታዊ ምርጫዎች ታሪክ፣ ስልጣን ላይ የነበረ መሪ ደግሞ የተመረጠበት አጋጣሚ አልነበረም። ማክሮ ግን ይህ እድል ይገጥማቸዋል ተብሎ ላይታሰብ ይችላል። የአውሮጳ ኅብረት ማሪን ለፔን እንዲመረጡ አይፈልግም።

https://p.dw.com/p/49rN3
Frankreich | Erste Runde der Präsidentschaftswahlen 2022 | Marine Le Pen und Emmanuel Macron
ምስል Paulo Amorim/IMAGO

የፈረንሳይ ፕሬዝዳንታዊ ምርጫ ሂደትና ውጤት

የፈረንሳይ ፕሬዝዳንታዊ ምርጫ አሸናፊ ከ12 ቀናት በኋላ በሚካሄደው ምርጫ ይለያል።ከትናንት በስተያ እሁድ የተካሄደውን የመጀመሪያ ዙር ምርጫ ያሸነፉት ፕሬዝዳንት ኢማኑዌል ማክሮና ሁለተኛውን ደረጃ ያገኙት ተቀናቃኛቸው ማሪን ለፔን የሚወዳደሩበት የመለያው ምርጫ ውጤት ተቀራራቢ ሊሆን እንደሚችል ተገምቷል። የዛሬው አውሮጳና ጀርመን ዝግጅታችን በፈረንሳይ ፕሬዝዳንታዊ ምርጫ ላይ ያተኩራል። ዘንድሮም እንደ ዛሬ አምስት ዓመቱ፣ የመሀል ፖለቲካ የሚያራምዱት የፈረንሳዩ ፕሬዝዳንት ኢማኑዌል ማክሮና ቀኝ አክራሪዋ ማሪን ለ ፔን ለፈረንሳይ ከፍተኛ ስልጣን በመለያው ምርጫ ዳግም ሊፎካከሩ ነው። የፈረንሳይ የሀገር ውስጥ ጉዳይ ሚኒስቴር ትናንት ባወጣው የእሁዱ የመጀመሪያ ዙር ምርጫ ውጤት መሠረት ማክሮን 27.84 በመቶ ለ ፔን ደግሞ 23 .15 በመቶ ድምፅ በማሸነፍ ለሁለተኛው ዙር ምርጫ አልፈዋል። የግራ አክራሪው ፓርቲ መሪ ዦን ሉክ ሜሎንሾ በ21.95 በመቶ ድምፅ ሦስተኛ ደረጃ አግኝተዋል። ማክሮ በመጀመሪያው ዙር ፕሬዝዳንታዊው ምርጫ ከ12 እጩዎች ጋር ተፎካክረው ነው ያሸነፉት። ቀድሞ የፈረንሳይ ሶሻሊስት ፓርቲ አባል ነበሩ ። በ2016 «ላ ሪፐብሊክ ኦን ማርሽ» የተባለ የመሀል አቋም የሚያራምድ እና ነፃ ገበያን እና መፍቀሬ-አውሮጳ የፖለቲካ አቋም ያለው ፓርቲ መሰረቱ። በዓመቱ በ2017 በተካሄደው ምርጫም ከተቀናቃናቸው ማሪን ለፔን ጋር ተወዳድረው 66.1 በመቶ ድምፅ በማሸነፍ የሀገሪቱ ፕሬዝዳንት ሆኑ። 39 ዓመታቸው ነበር ያኔ።በፈረንሳይ ታሪክ ወጣቱ ፕሬዝዳንትም ተባሉ። በስልጣን ዘመናቸው ውጣ ውረድ ባይለያቸውም በፈረንሳይ የተለያዩ ተሀድሶዎችን በማድረግ ስማቸው ይነሳል። ከመካከላቸው በሠራተኞች  ሕግና በቀረጥ አከፋፋል ላይ ያደረጓቸው ተሀድሶዎች እና የኮቪድ 19 ወረርሽኝን ለመከላከል የወሰዷቸው ርምጃዎችም ይጠቀሳሉ። ለሁለተኛ የስልጣን ዘመን የሚወዳደሩት ማክሮ ድላቸው ይፋ ከተደረገ በኋላ ለደጋፊዎቻቸው ባሰሙት ንግግር በጎርጎሮሳዊው ሚያዚያ 24 ቀን 2022 ዓም ከሚደረገው የመለያ ምርጫ በኋላ ሁኔታዎች እንደከዚህ ቀደሙ አይቀጥሉም ብለዋል። በዚህ ለውጥ ለመሳተፍ የሚፈልጉ ላሏቸው ዜጎች በሙሉም ጥሪ አቅርበዋል።» 
«የፈረንሳይ ህዝብ መጻኤ እድል በሚወሰንበት በዚህ ወቅት ላይ ምንም ነገር እንዳለ አይቀጥልም። ለዚህ ነው ለፈረንሳይ መሥራት ለሚፈልጉት ሁሉ መልዕክቴን ማድረስ የምሻው። በሚቀጥሉት ዓመታት ለህዝባችን የጋራ ርምጃ የተለያዩ አመለካከቶችና አስተምህሮቶችን በማሰባሰብ አዲስ ነገር ለመፍጠር ዝግጁ ነኝ። ይህ የኛ ሃላፊነት ነው።»
በሁለተኛው ዙር ምርጫ ከማክሮ ጋር የሚወዳደሩት የ53 ዓመትዋ የብሔረተኛው የ«ፍሮ ናስዮናል» ፓርቲ መሪ ጠበቃና ፖለቲከኛ ማሪ ለፔን የዛሬ አምሳ ዓመት ፓርቲውን የመሰረቱት የጆን ማሪ ለፔን ልጅ ናቸው ለፔን በጎርጎሮሳዊው 1986 ነበር የፓርቲው አባል የሆኑት። የዛሬ ዐሥር ዓመት በተካሄደው ፕሬዝዳንታዊ ምርጫ ከኒካላ ሳርኮዚ ጋር ተፎካክረው በ17.9 በመቶ ድምፅ ሥስተኛ ደረጃ ሲያገኙ፤ በ2017ቱ ምርጫ ደግሞ ከማክሮ ጋር ተወዳድረው 33.9 በመቶ ድምፅ በማሸነፍ ሁለተኛ ሆነው ነበር። ለፔን በቀደሙት ምርጫዎች ፈረንሳይ ከአውሮጳ ህብረትና ከዩሮ ተጠቃሚዎች ማኅበር እንድትወጣ እንዲሁም ድንበርዋን እንድትዘጋ ያቀነቅኑ ነበር ። የፖለቲካ ተንታኞች  አሁን አቋማቸው በመጠኑም ቢሆን አለስልሰዋል ይሏቸዋዋል። ለፔን ፍልሰት እንዲገደብ፣ ግርዛት ሕጋዊ እንዳይሆን ይፈልጋሉ። የአሜሪካንና የኔቶ የፖለቲካ መርሆችም ተቃዋሚ ናቸው። ሀገራቸውን ፈረንሳይን ከአሜሪካና ከኔቶ ተጽእኖዎች ለማላቀቅ ቃል የገቡም ፖለቲከኛ ናቸው። በእሁዱ ምርጫ ሁለተኛውን ደረጃ በማግኘት ለመለያ ምርጫ ያለፉት ለፔን እንደ ማክሮ ሁሉ እርሳቸውም ለፈረንሳውያን ጥሪ አቅርበዋል።
«በዚህ ወቅት ላይ ለሁሉም ፈረንሳውያን ለሁሉም ወገኖች የቀኝ የግራም ሌላም አቋም ያላችሁ የየትኛውም ዝርያ የሆናችሁ ፈረንሳውያን በሙሉ ይህን ታላቅ ብሔራዊና ህዝባዊ ንቅናቄ እንድትቀላቀሉ ጥሪ አቀርባለሁ።ፈረንሳይ የሚያስፈልጋትን ይህን ታላቅ ለውጥ በፍቅርና በቁርጠኝነት ለማሳካት በጋራ ድሉን እውን በማድረግ ሀገራችንን በደስታ ወደ ሦስተኛው ሚሊንየም እንወስዳታለን። ሪፐብሊኩ ለዘላለም ይኑር ፈረንሳይ ለዘላለም ትኑር።»
ማክሮ እና  ለ ፔን በተፎካከሩበት በ2017ቱም ምርጫ ድምፅ ለመስጠት የወጣው ህዝብ ቁጥር 73.69 በመቶ ነበር። ለዘንድሮው ምርጫ የተመዘገቡት መራጮች ቁጥር 48.7 ሚሊዮን ነው።አስተያየት ሰጭዎች እንደሚሉት ማክሮ ተፎካካሪያቸውን ማሪ ለ ፔንን እንዳለፈው ምርጫ በሰፊ ልዩነት ማሸነፍ  መቻላቸው ያጠራጥራል።  አሁን በተካሄደ የህዝብ አስተያየት መመዘኛ ማክሮን ከ51 እስከ 54 በመቶ ድምፅ፣ ለ ፔን ደግሞ ከ46 እስከ 49 በመቶ ድምፅ ሊያገኙ ይችላሉ ተብሎ ተገምቷል። ለሁለተኛ የስልጣን ዘመን የሚወዳደሩት የፈረንሳዩ ፕሬዝዳንት ኢማኑኤል ማክሮ ድሉን በእርግጠኛነት የራሳቸው ለማድረግ እየጣሩ ነው። ማክሮ አሁን በተለይ አሁን በመጀመሪያው ምርጫ ለሌሎች እጩዎች ድምፅ የሰጡትን መራጮችን የመሳብ ሙከራ ላይ ናቸው። 
«ለጽንፈኞቹ ድምፃችሁን ላልሰጣችሁ ወይም ድምፃችሁን ላለመስጠት ለወሰናችሁ ፈረንሳውያን በሙሉ፤ እኩልነት ባለመስፈኑ፣ ዓለማችን በመጎዳቷ፣ በየቀኑ ደኅንነታችን አስተማማኝ ባለመሆኑ፣ ምን ጠንክሮ ቢሠራም የተሻለ ሕይወት መመራት አለመቻሉ፤ የሚያበሳጫችሁ ወይም ደግሞ የሚያዳምጣቸው ያጡ፣ ከቁብም የሚቆጥራቸው ያለ ለማይመስላቸው፣ ለሚፈሩ እና ለዘመናችን ፈተናዎች መልዕክቴ ይህ ነው። የኛ ፕሮጀክት ከጽንፈኞቹ እቅድ ጋር ሲነፃጸር የተሻለ ጠንካራ ምላሽ እንደሚሰጣቸው በሚቀጥሉት ቀናት ላሳምናቸው እፈልጋለሁ። በኔ ላይ እምነታችሁን መጣል ትችላላችሁ። 
ማክሮን በተለይ ሦስተኛ የወጡት የግራ አክራሪው ፓርቲ መሪ የዦን ሉክ ሜሌንሾን ወጣት ደጋፊዎች በመለያው ምርጫ ድምፃቸውን ለርሳቸው እንዲሰጡ እየተማጸኑ ነው። ማክሮ የመጀመሪያው ዙር ምርጫ አሸናፊ መሆናቸው ይፋ እንደተደረገ ደጋፊዎቻቸው በሆታ ሲቀበሏቸው «የለም አትሳሳቱ ድሉ ገና ነው፤ ሲሉ አሳስበዋቸዋል። 
«አንታለል አንድም የተወሰነ ነገር የለም። በሚቀጥሉት ሳምንታት የምናካሂዳቸው ክርክሮች ለሀገራችንም ለአውሮጳም ወሳኝ ናቸው።»
ማክሮን ይህን ቢሉም ለደጋፊዎቻቸው ተስፋ መስጠታቸው አልቀረም። 
«በመጪው ሚያዚያ 24 ለፈረንሳይና ለአውሮጳ አዲስ ዘመን እንዲመጣ ማድረግ እንችላለን።ሚያዚያ 24 ቀን ተስፋን መምረጥ እንችላለን። ሚያዚያ 24 ፈረንሳይንና አውሮጳን በአንድ ላይ መምረጥ እንችላለን። ሪፐብሊኩ ለዘላለም ይኑር!ፈረንሳይ ለዘላለም ትኑር !» 
ምንም እንኳን በሁለተኛው ዙር ምርጫ የማክሮን ማሸነፍ ጎልቶ ቢወራም ለ ፔንም  ከአሁኑ የተሻለ ድምጽ አግኝተው ሊያሸንፉ ይችላሉ የሚል ስጋት ያደረባቸው አልጠፉም። ከነዚህ አንዱ የአውሮጳ ኅብረት ነው። የአውሮጳ ኅብረት ኔቶንና መሰል ድርጅቶችን ይቃወሙ የነበሩት ለፔን እንዲመረጡ አይፈልግም። ትናንት በዚህ ላይ አስተያየታቸውን የሰጡት የሉክስምበርግ ውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ዦን አሰልቦርን ይህ በጣም አሳሳቢ ጉዳይ ነው ብለዋል።
«አዎ በጣም ያሳስበኛል። በፈረንሳይ አምናለሁ። በሉክስምበርግ የፈረንሳይ ቴሌቪዥን አለን። የፖለቲካ የጦርነት ውስጥ እንዳሉ በግልጽ ማየት ይቻላል። በምርጫው ውጤት መሰረት ቀኝ አክራሪው ያገኘው ድምፅ በጀርመን ተመሳሳይ ፓርቲዎች ካገኙት ከእጥፍ በላይ ነው። ይህ በጣም በጣም የሚያሳስብ ነው።» 
አሰልቦርን ለ ፔን ፕሬዝዳንት ከሆኑ በኅብረቱ ውስጥ ሊያስከትል የሚችለውን ችግር ገልጸው፣ ይህ እንዳይሆን የማድረግ ኃላፊነቱን ለፈረንሳይ ህዝብ ሰጥተዋል። 
«ማሪን ለ ፔን የፈረንሳይ ፕሬዝዳንት ሆነው በአውሮጳ ኅብረት ውስጥ እንደማናገኛቸው ተስፋ እንናደርጋለን። ያ ከሆነ ከኅብረቱ እሴቶች የሚያፈነግጥ ብቻ ሳይሆን መንገዱን ሙሉ በሙሉ የሚያስቀይር ነው የሚሆነው። ይህን ደግሞ የፈረንሳይ ህዝብ ማስቀረት ይኖርበታል።ይህ ደግሞ እንደሚመስለኝ እጅግ በጣም አስፈላጊው ጉዳይ ነው።»
ኢማኑኤል ማክሮ ና ማሪ ለፔን ለሁለተኛ ጊዜ የሚፎካከሩበት የአዘንድሮው የፈረንሳይ ምርጫ ውጡት አጓጉቷል። በቅርብ ዓመታት የፈረንሳይ ፕሬዝዳንታዊ ምርጫዎች ታሪክ፣ ስልጣን የነበረ መሪ ደግሞ የተመረጠበት አጋጣሚ አልነበረም። ማክሮ ግን ይህ እድል ይገጥማቸዋል ተብሎ ላይታሰብ ይችላል። አይ ፒ ኤስ ኦ ኤስ የተባለው የህዝብ አስተያየት አጥኚ ድርጅት ምክትል ሃላፊና የፖለቲካ ተንታኝ ብሪስ ታይንቱርየር እንደሚሉት ግን ማክሮም ሆነ ለፔን የዛሬ አምስት ዓመት የነበራቸው ቁመናና አሁን ተቀይሯል። ውድድሩም ከከዚህ ቀደሙ ይለያል ።በርሳቸው አስተያየት ለፔንም ተለሳልሰዋል። ፔን ጋር ይገጥማሉ። ሁለቱ እንደገና የሚጋጠሙበት ይህ ውድድር ግን ፍጹም የተለየ ነው። ኢማኑኤል ማክሮ እንደ ከዚህ ቀደሙ የፖለቲካ ስርዓቱን አዲስ ለማድረግ ወይም  ለማሻሻል  የመጡ አዲስ እጩ አይደሉም። የበፊቱ ዓይነት ገጽታም ሆነ ተመሳሳይ አቋም የላቸውም።ማሪ ለፔን ደግሞ እንደበፊቱ ብዙ ትችት የሚያስነሱ አይደሉም። ለ ፔን ገጽታቸውን በማስተካከል ረገድ ሰርተዋል። ገጽታን በሚመለከት ማለቴ ነው። የፖለቲካ ፕሮግራማቸው ይዘት ግን  አልተቀየረም። ከከዚህ ቀደሙ በተሻለ ከፈረንሳውያን ጋር ይበልጥ መቀራረብ ፈጥረዋል። እንደቀድሞው ማስፈራታቸው ቀንሷል። ስልጣን ለማግኘት የፍልሰትን ጥያቄና ብሄረተኝነን ማስቀደምን ወደ ጎን አድርገውታል።»
በዘንድሮው የፈረንሳይ ምርጫ የዩክሬኑ ጦርነት፣ የኮሮና ወረርሽኝ በጤና ስርዓቱ ላይ ያሳደር ጫና እንዲሁም የሀገሪቱ ኤኮኖሚ ይዞታ መራጮች ትኩረት ከተሰጣቸው ጉዳዮች ውስጥ ዋነኛዎቹ ናቸው።በምርጫ ዘመቻ ወቅትም እጩ ተወዳዳሪዎች እየናረ የሄደውን የኃይልና የምግብ ዋጋ ለመቀነስ መወሰድ ባለባቸው እርምጃዎች ላይ አትኩረው ነበር።  በዛሬ 12 ቀኑ ምርጫ ድሉ የማን ይሆናል የሚለውን ከወዲሁ መገመት አዳግቷል። ህዝቡ ድምጹን ለፔን  እንዳይሰጥ የሚወተውቱት የማክሮን ወይስ የአውሮጳ ኅብረት እንደ ጦር የሚፈራቸው የለፔን? አብረን የምናየውና የምንሰማው ይሆናል።    
ኂሩት መለሰ

Frankreich | Erste Runde der Präsidentschaftswahlen 2022 | Marine Le Pen und Emmanuel Macron
ምስል JB Autissier/PanoramiC/IMAGO
Frankreich | Erste Runde der Präsidentschaftswahlen 2022 | Marine Le Pen
ምስል Thomas Samson/AFP
Frankreich, Präsident Emmanuel Macron Wahlkampf in Paris
ምስል Ludovic Marin/REUTERS

ማንተጋፍቶት ስለሺ