1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

የጥቅምት 8 ቀን 2017 የዓለም ዜና

ነጋሽ መሐመድ
ዓርብ፣ ጥቅምት 8 2017

-የቀድሞዉ የኢትዮጵያ ገዢ ፓርቲ ከፍተኛ ባለሥልጣን፣ የሠላም ሚንስትር ደኤታና የኦሮሚያ ምክር ቤት እንደራሴ ታዬ ደንደዓ ሕገ ወጥ የጦር መሳሪያ ታጥቃዋል በሚል መከሰሳቸዉን ዉድቅ አደረጉት።ከአምና ታሕሳስ ጀምሮ ከሥልጣን ተነስተዉ የታሰሩት አቶ ታዬ ጦር መሳሪ መታጠቃቸዉን አልካዱም።መከሰሳቸዉን ግን አልተቀበሉትም።-----የዩናይትድ ስቴትሱ ፕሬዝደንት ጆ ባይደን የጀርመን ፌደራል ሪፐብሊክን ከፍተኛ ኒሻን ዛሬ ተሸለሙ።-የእስራኤል ጦር የሐማስን መሪ ያሕያ ሲንዋርን መግደሉን የፍልስጤሙ ደፈጣ ተዋጊ ቡድን አመነ።

https://p.dw.com/p/4lyCL

አዲስ አበባ-ጠቅላይ ሚንስትር ዐብይ አሕመድ አዳዲስ ሹመት ሰጡ

የኢትዮጵያ ጠቅላይ ሚንስትር ዐብይ አሕመድ ዛሬ ለሶስት ነባር ባለሥልጣናት የመስሪያ ቤት ለዉጥና አዳዲስ ሹመት ሰጥተዋል።የጠቅላይ ሚንስትሩ ፅሕፈት ቤት በማሕበራዊ መገናና ዘዴዎች እንዳስታወቀዉ እስከ ዛሬ ድረስ የፍትሕ ሚንስትር የነበሩት ዶክተር ጌድዮን ጢሞቲዮስ የዉጪ ጉዳይ ሚንስትር ሆነዋል።የኢትዮጵያ ኢንቨስትመት ኮሚሽነር የነበሩት ወይዘሮ ሐና አርዓያ ሥላሴ ዶክተር ጌዲዮንን ተክተዉ በፍትሕ ሚንስትርነት ተሾመዋል።እስካሁን የመንግሥት ኮሙኒኬሽን ሚንስትር ደ ኤታ በመሆን ሲሰሩ የነበሩት ሠላማዊት ካሳ ደግሞ የቱሪዝም ሚንትርነትን ተሾመዋል።የጠቅላይ ሚንስትሩ ፅሕፈት ቤት ለዝዉዉርና ሹመቱ የሰጠዉ ማብራሪያና ምክንያት የለም።

አዲስ አበባ-የቀድሞዉ ሚንስትር ደ ኤታ የፍርድ ቤት ዉሎ

የቀድሞዉ የኢትዮጵያ የሰላም ሚኒስትር ዴኤታ ታዬ ደንደዓ ፍቃድ የሌለው የጦር መሳሪያ በመታጠቃቸዉ መከሰሳቸዉን ካዱ።አቶ ታዬ ዛሬ አዲስ አበባ ላስቻለዉ ለፌዴራሉ ከፍተኛ ፍርድ ቤት ልደታ ምድብ ችሎት በሰጡት የእምነት ክሕደት ቃል የጦር መሳሪያ መታጠቃቸዉን አምነዉ፣መከሰሳቸዉን ግን አልተቀበሉትም።የቀድሞዉ ከፍተኛ ባለሥልጣን አንድ ሽጉጥ፣አንድ AK-47 ወይም ክላሺንኾቭ ጠመንጃ ከ60 ጥይቶች ጋር ታጥቀዉ እንደነበረ አምነዋል።ይሁንና ክሱን በተመለከተ “አብረን አመራር ስንሰጥ እንደነበር የሚያውቁ” ያሏቸዉን የቀድሞ አለቃቸውን ጨምሮ አምስት የአገሪቱ ከፍተኛ ባለስልጣናትን ምስክርነት ቆጥረዋል።ችሎቱም ትዕዛዝ እንደሚሰጥ አስታዉቋል።የኢትዮጵያ ገዢ ፓርቲ የብልፅግና ከፍተኛ ባለሥልጣንና የኦሮሚያ ክልላዊ ምክር ቤት እንደራሴ የነበሩት ታዬ ደንደዓ ጠቅላይ ሚንስትር ዓብይ አሕመድን ከተቹ በኋላ የታሰሩት አምና ታሕሳስ ነበር።አቶ ታዬ  ፍርድ ቤት ሳይቀርቡ “ለአራት ወራት ታፍኜ ቆይቻለሁ” በሚል ላቀረቡት አቤቱታ የኢትዮጵያ ሰብዓዊ መብት ኮሚሽን ጉዳዩን እንዲያጣራ ፍርድ ቤት አዝዟል።ፍርድ ቤቱ፣ አቶ ታዬ ጠበቃ እንደሚስፈልጋቸው አሳስቧል። ተከሳሹ ግን “ጠበቃ እንዳይቆምልኝ በማስፈራራት ከልክሏል” ያሉት የሐገሪቱ ብሔራዊ የመረጃና ደህንነት መስሪያ ቤት እንዲጠየቅ አቤት በማለታቸው ፍርድ ቤቱ ለዚህም ማብራሪያ እንዲሰጠኝ ትዕዛዝ አስተላልፋለሁ ብሏል፡፡ተከሳሹ በግል እንጂ መንግሥት ጠበቃ እንዲያቆምላቸዉ እንደማይፈልጉ አስታዉቀዋል።የአዲስ አበባዉ ወኪላችን ስዩም ጌቱ እንደዘገበዉ ችሎቱ የመከላከያ ምስክሮችን ቃል ለመስማትም  ለህዳር 9 ቀን 2017 ቀጥሯል።

ሐዋሳ-14 ሰዎች ባሕር ዉስጥ ሰጠሙ

በደቡብ ኢትዮጵያ ክልል ጋሞ ዞን መንገደኞችን አሳፍሮ ጫሞ ሐይቅ ላይ ይቀዝፍ የነበረ መለስተኛ ጀልባ ትናንት ማምሻ በመስጠሙ 14 ሰዎች የደረሰቡት አለመታወቁን  የዞኑ ፖሊስ መምሪያ አስታወቀ ፡፡ፖሊስ እንዳስታወቀዉ ጀልባዉ ሙዝ ጭኖ ከኮሬ ወደ አርባምንጭ ከተማ በመቅዘፍ ላይ ነበር።የጀልባው ከቀዛፊዉ ሌላ 15 የቀን ሰራተኞችን ከሙዝ ጋር አሳፍሮ ነበር።የዞኑ ፖሊስ የሕዝብ ግንኙነት ኃላፊ ኮማንደር ረታ ተክሉ እንዳሉት ጀልባዉ ካሳፈራቸዉ 16 ሰዎች ሁለቱ ጀሪካን ላይ ተንሳፍፈዉ በይሕወት ተርፈዋል።ሌሎቹ 14ቱ ግን እስከ ዛሬ ከቀትር በኋላ ድረስ አልተገኙም።የሐዋሳዉ ወኪላችን ሸዋንግዛዉ ወጋየሁ የጋሞ ዞን ኮሙኒኬሽንን ጠቅሶ እንደዘገበዉ ፖሊስ ፍለጋዉን ቀጥሎ ነዉ የዋለዉ።

 

በርሊን-ባይደን የጀርመንን ታላቅ ኒሻን ተሸለሙ

ጀርመንን በይፋ መጎብኘት ላይ የሚገኙት የዩናይትድ ስቴትስ ፕሬዝደንት ጆ ባይደን «የመልካም ሥራ ታላቅ የመስቀል ኒሻን» የተሰኘዉን የጀርመንን ከፍተኛ የክብር ኒሻን ተሸለሙ።ዛሬ ከቀትር በፊት በርሊን በሚገኘዉ በጀርመን ፕሬዝደንት ይፋ መኖሪያ ቤሌቩ ቤተመንግሥት በተደረገዉ የሽልማት ሥነሥራዓት የሁለቱ  ሃገራት ከፍተኛ ባለሥልጣናት ተገኝተዋል።የጀርመን ፕሬዝደንት ፍራንክ ቫልተር ሽታይንማየር ለአሜሪካዉ የክብር እንግዳቸዉ ሽልማቱን ሲሰጡ እንዳሉት ለአዉሮጳ ዩናይትድ ስቴትስ ምትክ የማይገኝላት ወዳጅ፣ የሰሜን አትላንቲክ ጦር ቃል ኪዳን ድርጅት (ኔቶ) ደግሞ ምትክ የማይገኝለት ትብብር ነዉ።ሽታይንማየር ፕሬዝደንት ጆ ባይደንን አዉሮጳ ለአደጋ በተጋለጥችበት ወቅት ልዩ ፖለቲካዊ መሪነታቸዉን ያስመከሩ በማለት አወድሰዋቸዋልም።

             

«ለአትላንቲክ ማዶ ለማዶ ወዳጅነት ፅናት፣ ለርካታ አስርታት  ላሳዩትን ቁርጠኝነት ሐገሬ እዉቅና ትሰጣለች። አዉሮጳ በጣም አደገኛ ሁኔታ ዉስጥ ባለችበት ወቅት አቻ የለሽ ፖለቲካ አመራርን  ዘለቂ የሞራል አገልግሎትን፣ ቅንነትና ፅናትን አሳይተዋል።የጀርመን ፌደራል ሪፐብሊክን የልዩ አገልግሎት የመልካም ሥራ ታላቅ ሽልማትን ሥሰጥዎ ታላቅ ክብር ይሰማኛል።ለዚሕም ክቡር ፕሬዝደንት፣ ዉድ ጆ ልበልና እንኳን ደስ አለሕ።»

በርሊን-የጆ ባይደን ምሥጋናና ዉይይት

ፕሬዝደንት ጆ ባይደን ሸላሚዎቻቸዉን አመስግነዉ፣ ጀርመንን አድንቀዉ ሩሲያን አዉግዘዋል።

«ጀርመን (ዜጎችዋ) የተሟላ ዋስትና ያለዉ ነፃ ሕይወት እንዲመሩ በማድረግ ረገድ ያሳችዉ ዉጤት ማንም ከሚጠብቀዉ በላይ ነዉ።የመላዉ አዉሮጳ ሕልምን ማሟላት ዘመናችንም ሥራ ነዉ።ይሕ ሥራ ፑቲን በዩክሬን ላይ የከፈቱት የጥቃት አዙሪት የመቀልበስን ያክል ቅድሚያ ሊሰጠዉ አይችልም።በመሸለሜ በድጋሚ አመሰግናለሁ።ሽልማቱ አይገባኝም ግን ሥቀበል ክብር ይሰማኛል።አሕ! አብረን መሥራታችንን መቀጠል ብንችል ኖሮ?»

ፕሬዝደንት ጆ ባይደን ዛሬዉኑ መጀመሪያ ከጀርመን መራሔ መንግሥት ኦላፍ ሾልስ፣ አከታትለዉ ከኦላፍ ሾልስ፣ ከፈረንሳይ ፕሬዝደንት ኢማኑኤል ማክሮና ከብሪታንያዉ ጠቅላይ ሚንስትር ኪር ስታርመር ጋር ይወያያሉ።ሥልጣን ሊለቁ 2 ወር ከ2 ሳምንት የቀራቸዉ የ81 ዓመቱ አዛዉንት ባይደን በጀርመን የሚያደርጉት ጉብኝት እንደ ፕሬዝደንት አዉሮጳን እንደመሰናበት የሚቆጠር ነዉ።

 

ዛ/ የተለያዩ-የሐማስ መሪ መገደል የምዕራባዉያን አፀፋ

የፍልስጤሙ ደፈጣ ተዋጊ ቡድን ሐማስ መሪዉ ያሕያ ሲንዋር መገደላቸዉን በይፋ አመነ።የእስራኤል፣ ጦር ጋዛ ሰርጥ ዉስጥ ሲንዋርን መግደሉን የሐገሪቱ ባለሥልጣናት ትናንት ማታ አስታዉቀዉ ነበር።እስራኤል፣ ዩናይትድ ስቴትስ፣ የአዉሮጳ ሕብረት፣ ብሪታንያና ተባባሪዎቻቸዉ ባሸባሪነት የፈረጁት ቡድን ዛሬ ባወጣዉ መግለጫ «ተሰዉዑ» ባለዉ በመሪዉ መገደል ማዘኑን አስታዉቆ፣ ለፍልስጤም ነፃነት ፍልሚያዉን ለመቀጠል ዝቷል።የእስራኤል መሪዎች የሲንዋርን መገደል እንደታላቅ ድል ቆጥረዉታል።የዩናይትድ ስቴትስና የጀርመን መሪዎች በበኩላቸዉ የሲንዋር መገደል ለሰላም ጠቃሚ ነዉ ብለዋል።

ቴሕራን-የሲንዋር መገ,ደል የኢራንና የአረቦች አፀፋ

የኢራን ዉጪ ጉዳይ ሚንስትር አባስ አርጋቺ በX ባሠራጩት መልዕክት ግን «ግድያዉ ፍልስጤሞች ነፃ ለመዉጣት የሚያደርጉትን ትግል ይበልጥ ያጠናክረዋል» ብለዋል።የሐማስ የፖለቲካ ክንፍ ምክትል መሪ ኻሊል አል ሐያ በበኩላቸዉ በጋዛ ላይ የሚፈፀመዉ ወረራ እስካል ቆመና የእስራኤል ጦር ከጋዛ እስካልወጣ ድረስ ሐማስ ያገታቸዉ ሰዎች አይለቀቁም።» ማለታቸዉን ሮይተርስ ዜና አገልግሎት ጠቅሷል።የፍልስጤም፣ የዮርዳኖስ፣ የሊባኖስ፣ የኢራንና የተለያዩ የአረብ ሐገራት ዜጎች የሲንዋርን መገደል ባደባባይ ሰልፍ አዉግዘዋል።ሐዘናቸዉን ገልጠዋልም።የ62 ዓመቱን ፍልስጤማዊ ፖለቲከኛን እስራኤል ከ20 ዓመታት በላይ አስራቸዉ ነበር።ሲንዋር የሐማስን የመሪነት ስልጣን የያዙት የቡድኑን የቀድሞ መሪ ኢስማኤል ሐንያን እስራኤል የዛሬ ሶስት ወር ግድም ቴሕራን-ኢራን  ዉስጥ ከገደለቻቸዉ በኋላ ነዉ።   

 

አቴንስ-የግሪክ የወደብ ሠራተኞች ወደ እስራኤል ጥይት እንዳይጓዝ አገዱ

የግሪክ የወደብ ሠራተኞች ማሕበራት ባልደረቦች ወደ እስራኤል የሚጓዝ ጥይት የጫኑ ኮንቴይነሮች መርከብ ላይ እንዳይጫኑ አገዱ።ሮይተር ዜና አገልግሎት «በደርዘን የሚቆጠሩ» ያላቸዉ የወደብ ሠራተኞች ኮንቴይነሮቹ እንዳይጓዙ ያገዱት የጋዛዉን ጦርነት በመቃወም ነዉ።21 ቶን የሚመዝነዉ ጥይት በማርሻል ደሰቶች ስም በተመዘገብ መርከብ ተጭኖ ከሰሜን ሜቅዶኒያ ፒሪዮስ በተባለዉ የግሪክ ወደብ በኩል ወደ እስራኤል እንዲጓዝ ታቅዶ ነበር።ሮይተር ዜና አገልግሎት አክሎ እንደዘገበዉ የግሪክ የወደብ ሠራተኞች ማሕበራት ጋዛ ዉስጥ ለሚደረገዉ ጦርነት ይዉላሉ ያሏቸዉ ጦር መሳሪያዎችና ጥይቶች በወደቡ በኩል ወደ እስራኤል እንዳያልፉ አባላቱ ይከለክሉ ዘንድ ጠይቆ ነበር።

 

 

 

ቀጣዩን ክፍል ዝለለዉ ስለዚሕ ዝግጅት

ስለዚሕ ዝግጅት

PODC-DW-Amharisch-News-DWcom

የዓለም ዜና

ዶይቼ ቬለ የዕለቱን ዋና ዋና የዜና ትንታኔዎች ከኢትዮጵያ እና ከመላው ዓለም በየቀኑ ያቀርባል። የኢትዮጵያ እና የአፍሪካ ፖለቲካዊ እና ኤኮኖሚያዊ ጉዳዮችን ጨምሮ የመላው ዓለምን ውሎ የተመለከቱ ጠቃሚ መረጃዎች በሰባቱም የሣምንቱ ቀናት ከምሽቱ አንድ ሰዓት ከዶይቼ ቬለ ያድምጡ።