1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

የጥቅምት 1 ቀን 2017 ዓ/ም የዓለም ዜና

Tamirat Geletaዓርብ፣ ጥቅምት 1 2017

https://p.dw.com/p/4lhVq

ግብጽ የሰላም አስከባሪ ኃይል ለማሰማራት ያቀረበችውን ሃሳብ መቀበሏን ሶማሊያ አስታወቀች ።

ሶማሊያ የግብጽን ጥያቄ መቀበሏን ያስታወቀችው የግብጽ ፣ ሶማሊያ እና ኤርትራ ፕሬዚዳንቶች ትናንት ሐሙስ አስመራ ውስጥ ተገናኝተው ከመከሩ በኋላ ነው።

የሶማሊያ ባለስልጣናት በመሪዎቹ ውይይት ማብቂያ ላይ በሰጡት መግለጫ አሁን በሶማሊያ የተሰማራው የአፍሪቃ ሰላም አስከባሪ ኃይል የፊታችን ታህሳስ መጨረሻ ተልዕኮውን ሲያጠናቅቅ ግብጽ የሰላም አስከባሪ ኃይሏን ሶማሊያ ውስጥ ለማሰማራት ያቀረበችውን ጥያቄ መንግስታቸው በደስታ መቀበሉን ተናግረዋል።

ከኢትዮጵያ ጋር ዲፕሎማሲያዊ እሰጥ አገባ ውስጥ የገቡት የሶስቱ ሃገራት መሪዎቹ ከውይይታቸው በኋላ የሶስትዮሽ ግንኙነታቸውን ለማጠናከር መስማማታቸውን አሶሽየትድ ፕረስ ዘግቧል።

ሀገራቱ በስምምነታቸው ከተካተቱ ሃሳቦች በተለይ የሁሉም ሀገራት ሉዓላዊነት እና የግዛት አንድነት እንዲከበር እና በውስጥ ጉዳዮቻቸው ውስጥ ጣልቃ እንዳይገባ ለመከላከል የሚያስችለው አንዱ ነው ።

 በተጨማሪም የሶማሊያ ብሄራዊ ጦር ሰራዊት ሽብርተኝነትን በሁሉም መልኩ በብቃት እንዲዋጋ እና የሶማሊያን የመሬት እና የባህር ድንበሮች ጥበቃን የሚያካትት እና የግዛት አንድነት እንዲጠበቅ ለማድረግ ስምምነት ላይ ተደርሷል።

ግብጽ ፣ ሶማሊያ እና ኤርትራ ያደረጉት ስምምነት  በተለይ ሶስቱም በተናጥል ከኢትዮጵያ ጋር የተፈጠረባቸው የዲፕሎማሲ መሻከር ውጤት  ሳይሆን እንዳልቀረ ነው ዘገባው ያመለከተው። ሶማሊያ ፤ ኢትዮጵያ ከሶማሌ ላንድ ጋር የደረሰችው የመግባቢያ ስምምነት የግዛት አንድነቴን የጣሰ ነው ስትል ትከሳለች። ግብጽ በበኩሏ ኢትዮጵያ በአባይ ወንዝ ላይ የገነባችው ታላቁ የህዳሴ ግድብ ከስምምነት ውጭ የተፈጸመ እና ብሄራዊ ጥቅሜን የነካ ነው ትላለች ።

ኤርትራ ምንም እንኳ ፊት ለፊት መንግስት ለመንግስት በይፋ መካሰስ ባይሰማም  የኢትዮጵያ መንግስት ከትግራይ ኃይሎች ጋር ከደረሰው የሰላም ስምምነት በኋላ የነበረው ዲፕሎማሲያዊ ግንኙነት ሻክሮ የአየር በረራ እና የቴሌኮሙኒኬሽን ግንኙነቱ እስከመቋረጥ አድርሶታል።

 

በአማራ ክልል ደቡብ ወሎ ዞን ውስጥ የሚገኙ ሁለት የግል ባንኮች ላይ ከ65 ሚሊዮን ብር በላይ ዝርፊያ ተፈጸመ

ጸደይ እና አቢሲኒያ አምባሰል ግሸን ቅርንጫፎች የታጠቁ ኃይሎች ኃይሎች በተቀናጀ ሁኔታ ተፈጸመብን ባሉት ዝርፊያ በድምሩ 67 ሚሊዮን ብር ማጣታቸውን አስታውቀዋል።

ባንኮቹ ትናንት ሐሙስ መስከረም 30 ቀን በሰጡት መግለጫ እንዳሉት ዘረፋው የተፈጸመባቸው ባለፈው ቅዳሜ መስከረም 25 ቀን 2017 ዓ/ም ነው።

የአቢሲኒያ ባንክ የግሸን ደብረ ከርቤ ቅርንጫፍ ኦፕሬሽን ሥራ አሥኪያጅ ዘውዱ ቀና እንደገለጹት በመስከረም 25 2017 ከቀኑ 11:30 ሰዓት አካባቢ  ስራ ላይ እንዳሉ በታጣቁ ሰዎች መታገታቸውን ተናግረዋል።  

«ስራ ላይ እያለን ከቀኑ 11 ሰዓት ተኩል ነበረ ፤ የታጠቁ ኃይሎች ቢሯችን መጡና እያንዳንዳችን ባለህበት ተቀምጥ ብለው መጀመሪያ ስልካችንን ነጠቁን ። እንዳትንቀሳቀሱ እንዳትናገሩ በማለት አስቀመጡን ። ከማናጀሩ በስተቀር ውጡ ብለው ሁሉንም ሰው ወስደው እዚያ ቤት ዘጉባቸው ፤  ከዚያም እኔን ካዝናውን ትከፍታለህ የሚል ጥያቄ ተነሳብኝ»

 ባንኩ በዕለቱ ለንግሥ በዓሉ የመጡ በርካታ ተገልጋዮችን ሲያገለግል መቆየቱን የገለጹት ኃላፊው በታጣቂዎቹ ከ63 ሚሊዮን ብር በላይ ዝርፊያ እንደተፈጸመበት ተናግረዋል።

በተመሳሳይ ቀን እኩለ ሌሊት ገደማ 5:30 ላይ በታጣቂዎች ታግተው ባንካቸው መዘረፉን  የፀደይ ባንክ የግሸን ደብረ ከርቤ ሥራ አሥኪያጅ አማረ ማሞ ተናግረዋል።

«የቀን ስራችንን ሰርተን ከገባን በኋላ ከሌሊቱ አምስት ሰዓት ተኩል ላይ ነው ድርጊቱ የተፈጸመው ። ከምኖርበት ቤቴ መጥተው ነው ግልጽ ባልሆነ መንገድ ፊታቸውንም ጸጉራቸውንም ማሳየት ያልፈለጉ ጭምብል እና ሽርጥ በመልበስ ከመኖሪያ ቤቴ አስገድደው የወሰዱበት ሁኔታ ነው ያለው »

ዝርፊያው የተፈጸመበት የደቡብ ወሎ ዞን አምባሰል ወረዳ በመንግስት የጸጥታ ኃይሎች እና በፋኖ ታጣቂዎች መካከል ውጊያ ከሚደረግባቸው አካባቢዎች ተጠቃሽ ነው ።

 

በደቡብ ሱዳን ጎርፍ ባስከተለው ቀውስ ከ240 በላይ የሚሆኑን ከቤት ንብረታቸው ተፈናቀሉ ።

የተባበሩት መንግስታት ድርጅት እንዳለው  ከ890 ሺ በላይ የሚሆኑት በጎርፉ ተጎድተዋል። ደቡብ ሱዳን በአስርት ዓመታት ውስጥ አይታው የማታውቀው የጎርፍ መጥለቅ አደጋ እንደገጠማት ዓለማቀፍ የተረድዖ ድርጅቶች አስታዉቀዋል።

የጎርፍ መጥለቅለቁ በመላው ሀገሪቱ ዜጎችን ማፈናቀል መቀጠሉን የተባበሩት መንግስታት ድርጅት የሰብአዊ ጉዳዮች ማስተባበሪያ ፅህፈት ቤት ኦቻ ገልጿል። በዚህም አስራ አምስት የርዳታ ማቅረቢያ መንገዶች ማስተጓጎሉን ዖቻ ጠቅሷል።

የዓለም ባንክ ባለፈው መስከረም 21 ቀን አውጥቶ በነበረው መግለጫ የጎርፍ አደጋ በደቡብ ሱዳን ለወትሮም የነበረውን «ከፍተኛ የምግብ ዋስትና ችግር፣ የኢኮኖሚ ማሽቆልቆል፣ ቀጥሎ የሚደረገውን ግጭትእና የበሽታ ወረርሽኝ ያስከተለውን አሳሳቢ ሰብዓዊ ሁኔታ እያባባሰ ነው» ብሏል።

 

 

ከጃፓኑ የኒኩልየር ቦምብ ጥቃት በተረፉ ሰ,ዎች የተቋቋመው የጃፓን የጸረ ኒኩልየር የጦር መሳሪያ ድርጅት የዘንድሮውን የዓለም የሰላም ኖቤል ሽልማት አሸነፈ

ኒሆን ሂዳንክዮ የተሰኘው ድርጅት የኒኩልየር የጦር መሳሪያ የታጠቁ ሃገራት መሳሪያውን እንዳይጠቀሙ አጥብቆ ይቀሰቅሳል።

የድርጅቱ መስራቾች ዛሬ ኖርዌይ ኦስሎ ውስጥ በተከናወነ ደማቅ ስነስረዓት የዓመቱ የሰላም ኖቤል ሽልማታቸውን በይፋ ተቀብለዋል። የኖርዌይ የኖቤል ኮሚቴ ባወጣው መግለጫ ፤ሂባኩሻ አለም ከኑክሌር የጦር መሳሪያ ነጻ የሆነች ዓለምን ለማሳየት ላደረጉት ጥረት ….እና የኑክሌር ጦር መሳሪያ ድጋሚ ጥቅም ላይ መዋል እንደሌለበት ምስክር ስለሆኑ የኖቤል የሰላም ሽልማት አግኝተዋል» ብሏል።

ከሄሮሽማ እና ናጋሳኪ የኑክሌር ቦምብ ጥቃት የተረፉ ሰዎች የመሰረቱት ይኸው  ድርጅት « የማይታሰበውን እንድናስብ እንዲሁም በተወሰነ መልኩ በኑክሌር የጦር የደረሰውን ከባድ ጥቃት እንድናውቅ ረድቶናል» ሲል የኖቤል ኮሚቴው ገልጿል።

የኖቤል ኮሚቴ ሊቀመንበር ጆርገን ዋትን በስነ ስረዓቱ ላይ የሃገራትን ስም ሳይጠቅሱ ባስተላለፉት መልዕክት  «የኒኩልየር የጦር መሳሪያ የታጠቁ ሃገራት በመሳሪያው ስለመጠቀም ማሰብ የለባቸውም » ብለዋል።

በየዓመቱ በተለያዩ መስኮች የተሻለ ስራ ለሰሩ ሰዎች ዓለማቀፍ እውቅና እና ሽልማት የሚሰጠው የኖቤል ሽልማት ኮሚቴ ለተሸላሚዎች ከሚሰጠው ዕውቅና በተጨማሪ 1 ሚሊዮን ዶላር ገደማ የገንዘብ ሽልማት ያበረክታል።

 

እስራኤል ቤሩት ውስጥ በፈጸመችው የአየር ጥቃት 22 ሰዎች መገደላቸውን ሊባኖስ አስታወቀች።

ትናንት ምሽት በተፈጸመው በዚሁ ጥቃት 117 ሰዎች መቁሰላቸውን የሊባኖስ የጤና ሚኒስቴር አስታዉቋል። ጥቃቱ የቀድሞ የሄዝቦላ መሪ ሀሰን ናስረላ አማች እና የቡድኑ የደህንነት ኃላፊ በሆኑት ዋፊቅ ሳፋ ላይ ሳያነጣጥር እንዳልቀረ የፈረንሳይ ዜና አገልግሎት ዘገባ ያመለክታል።

ጥቃቱ በመዲናዪቱ ቤሩት ለጥቂት ቀናት ከቆየ ፋታ በኋላ የተፈጸመ ነው ተብሎለታል። ነገር ግን ኢላማ የተደረገው ዋፊቅ ከጥቃቱ ሳያመልጥ  እንዳልቀረ ነው የተገለጸው።

ጥቃቱን ተከትሎ የሊባኖሱ የሞግዚት አስተዳደር ጠቅላይ ሚንስትር እስራኤል እና ሄዝቦላ አስቸኳይ የተኩስ አቁም እንዲያደርጉ ጥሪ አቅርበዋል። ጠቅላይ ሚንስትር ናጂብ ሚካቲ በጥሪአቸው እስራኤል  « የሲቪሊያዉያን የመኖሪያ አካባቢን ዒላማ ማድረግ እንድታቆም « ጥሪ አቅርበዋል።   ሚካቲ  በሀገሪቱ ቴሌቪዥን በተላለፈ መልዕክታቸው እስራኤል በተባበሩት መንግስታት ሰላም አስከባሪ ኃይል ላይ የተፈጸመውን ጥቃት አውግዘዋል።

በእስራኤል እና ሊባኖስ ድንበር ላይ በደረሰ ፍንዳታ ሁለት የሰላም አስከባሪ ኃይሎች ከቆሰሉ በኋላ የሰላም አስከባሪ ኃይሉ ለጥቃት መጋለጡን ተከትሎ አየርላንድን ጨምሮ ሃገራት ተቃዉሟቸውን አስምተዋል።

 

እስራኤል በየዮርዳኖስ ወንዝ ምዕራባዊ ዳርቻ ኑር ሻምስ የስደተኞች መጠለያ በተፈጸመችው ጥቃት እስላማዊ ጅሃድ የተባለው የፍልስጥኤማዉያን ታጣቂ ቡድን አዛዥ መግደሏን አስታወቀች።       የእስራኤል መከላከያ እንዳለው
የእስራኤል አውሮፕላኖች በሰሜናዊቷ የቱልካረም ከተማ አቅራቢያ በሚገኘው የስደተኞች መጠለያ ላይ ባደረሰው ጥቃት የታጣቂ ቡድኑን መሪ መሐመድ አብዱላህን ጨምሮ አብሮት የነበረ «አሸባሪን» ገድያለሁ ብሏል።

መሐመድ አብዱላህ ባለፈው የነሐሴ ወር የተገደለው እና የታጣቂ ቡድኑ መሪ የነበረውን መሐመድ ጃበርን ተክቶ ቡድኑን ይመራ የነበረ ሰው እንደ ነበረ የእስራኤል መከላከያን ጠቅሶ የጀርመን ዜና ምንጭ ዲ ፒ ኤ ዘግቧል።

የፍልስጤኤም ጤና ሚኒስቴር «መሃመድ ኢያድ መሀመድ አብዱላህ የተባለ የ20 አመት ወጣት እና አዋድ ጀሚል ሳቅር ኦማር የተባለ የ31 አመት ሰው በአየር ጥቃቱ መገደላቸውን » አረጋግጧል።

የሐማስ አጋር የሆነው የፍልስጥኤማዉያን ታጣቂ ቡድን እስላማዊ ጅሃድ በዮርዳኖስ ወንዝ ምዕራባዊ ዳርቻ እና ጋዛ ውስጥ ከእስራኤል ኃይል ጋር በመዋጋት ላይ ይገኛል።

 

ታምራት ዲንሳ

ኂሩት መለሰ

 

 

 

ቀጣዩን ክፍል ዝለለዉ ስለዚሕ ዝግጅት

ስለዚሕ ዝግጅት

PODC-DW-Amharisch-News-DWcom

የዓለም ዜና

ዶይቼ ቬለ የዕለቱን ዋና ዋና የዜና ትንታኔዎች ከኢትዮጵያ እና ከመላው ዓለም በየቀኑ ያቀርባል። የኢትዮጵያ እና የአፍሪካ ፖለቲካዊ እና ኤኮኖሚያዊ ጉዳዮችን ጨምሮ የመላው ዓለምን ውሎ የተመለከቱ ጠቃሚ መረጃዎች በሰባቱም የሣምንቱ ቀናት ከምሽቱ አንድ ሰዓት ከዶይቼ ቬለ ያድምጡ።