የጋናው ፕሬዝዳንት አረፉ
ማክሰኞ፣ ሐምሌ 17 2004የጋና ፕሬዝዳንት ጆን ኤቫንስ አታ ሚልስ ዛሬ በድንገት አረፉ። የ68 ዓመቱ ፕሬዝዳንት ሚልስ ሲታከሙ በነበረበት ወታደራዊ ሆስፒታል ዛሬ ማረፋቸውን መንግሥት ባወጣው መግለጫ አስታውቋል። መንግሥት እንዳለው ፕሬዝዳንቱ ዛሬ ከሰአት በኋላ ህክምና እንዲደርግላቸው በገቡበት በ37 ተኛው ወታደራዊ ሆስፒታል በመታከም ላይ ሳሉ በጥቂት ሰዓታት ውስጥ ነው ህይወታቸው ያለፈው። ቀደም ሲል ትናንት ምሽት ህመም እንደተሰማቸው ፕሬዝዳንቱ መናገራቸውን ስማቸው እንዲጠቀስ ያልፈለጉ ረዳታቸው
አስታውቀዋል። ፕሬዝዳንት ሚልስ ከጥቂት ሳምንታት በፊት ዩናይትድ ስቴትስ ዉስጥ ታክመው ነበር። ዛሬ ግን የፕሬዝዳንቱን ሞት በልባዊና ጥልቅ ሃዘን እናስታውቃለን ሲል መንግሥት በመግለጫው ማስታወቁ ተዘግቧል። ሚልስ እጎአ በ2008 መጨረሻ ላይ በተካሄደ ፕሬዝዳንታዊ ምርጫ በጠባብ ሉዩነት አሸንፈው በ2009 ዓም መጀመሪያ ላይ ነበር የቀድሞው ፕሬዝዳንት ጆን ኩፎርን በመተካት የጋና ፕሬዝዳትነት ሆነው ሥልጣን የያዙት። ፕሬዝዳንት ሚልስ በሚቀጥለው ዓመት በታህሳስ ወር ለሚካሄደው ፕሬዝዳንታዊ ምርጫ በገዥው የብሔራዊ ዲሞክራሲያዊ ምክር ቤት በእጩ ፕሬዝዳንትት ተሰይመው ነበር።
የጋናው ምክትል ፕሬዝዳንት ጆን ድራማኒ ማሃማ ዛሬ ማምሻውን ለፕሬዝዳንትነት ቃለ መሃላ እንደሚፈፅሙ ሮይተርስ ከመዲናይቱ አክራ ዘግቧል። በጋና ህገ መንግሥት መሠረት ማሃማ ታህሳስ ወር በሚካሄደው ምርጫ የሃገሪቱ ፕሬዝዳንት እስኪወሰን ድረስ የሚልስን የሥልጣን ዘመን እስኪጠናቀቅ ሃገሪቱን ይመራሉ።
ሂሩት መለሰ
ሸዋዬ ለገሠ