1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

የጋራ ብልጽግና አባል ሃገራት ጉባኤ

ቅዳሜ፣ ሰኔ 18 2014

በዚህ ሳንምንት ሁለት ትላልቅ ጉባኤዎች በአፍሪቃ ተካሂደዋል። የጋራ ብልጽግና አባል ሃገራት ጉባኤ በሩዋንዳ፤ የቻይና እና የአፍሪቃው ቀንድ ሃገራት የጸጥታ ፣ አስተዳደር እና ልማትን የሚመለከተው ጉባኤ ደግሞ በአዲስ አበባ።

https://p.dw.com/p/4DDT8
Ruanda Kigali |  2022 Commonwealth Heads Of Government Meeting
ምስል Luke Dray/Getty Images

ትኩረት በአፍሪቃ

የጋራ ብልጽግና የተባለው ስብስብ 54 አባል ሃገራት ያካተተ ሲሆን አብዛኞቹ ቀድሞ የብሪታንያ ቅኝ ግዛቶች ነበሩ። በጉባኤው 19ኙን የአፍሪቃ ሃገራት ጨምሮ የእስያ እና አሜሪካ ሃገራትም ይገኙበታል።  ስብስቡ በኮቪድ 19 ወረርሽኝ ምክንያት በጎርጎሪዮሳዊው 2020 ዓም ጉባኤው በመስተጓጎሉ ከአራት ዓመታት ወዲህ ኪጋሊ ሩዋንዳ ላይ ሲሰበሰብ የመጀመሪያው ነው። በዚህ ሳምንት ሰኞ ዕለት የተጀመረው እና እሑድ ዕለት እንደሚጠናቀቅ የሚጠበቀው የጋራ ብልጽግናው ጉባኤ የሴቶችን የመሪነት ሚና ማጠናከር፣ በጋራ ብልጽግናው አባል ሃገራት መካከል ያለውን የንግድ ትስስር ማስፋፋት እና ወደመሪነት ለሚመጡ ወጣቶች ድጋፍ ማድረግ የሚሉት የሚያተኩርባቸው ዋነኛ ነጥቦች እንደሆኑ ተገልጿል። ጉባኤውን የሚከታተለው የዶቼ ቬለ የእንግሊዝኛው ክፍል ባልደረባ አይዛክ ሙጋቤ ካነጋገራቸው ወጣቶች አንዷ መድረኩ እንደሷ ላሉት ምን ማለት እንደሆነ ስትናገር፤

Ruanda Kigali | Commonwealth Gipfeltreffen CHOGM
ምስል SIMON WOHLFAHRT/AFP

«ለወጣቶች ሕዝባችንን ስለሚያሳስቡት የተለያዩ ጉዳዮች ማለትም በንግድ ባለቤትነት፣ በሥራ ዕድል፣ ወጣቶችን በመሪዎች ደረጃ ለውሳኔ ስለማሳተፍ ወይም ደግሞ በትምህርት እና በጤና እንዲሁም ስለወጣቶች ደህንነት ራሳችንን ለመግለጽ እንድንችል ዕድል የሚሰጥ ነው። »

ትላለች። በአንጻሩ ደግሞ ጉባኤው «የምዕራቡ ዓለም ተወዳጅ አምባገነን» ለሚባሉት የሩዋንዳ ፕሬዝደንት ፖል ካጋሜ ደረጃቸውን ከፍ ለማድረግ እና ሀገራቸውንም በውጭው ዓለም ዘንድ ይበልጥ ለማስተዋወቅ ምቹ አጋጣሚ እንደሚሆንላቸው የሚናገሩም አሉ። ሩዋንዳ የመንግሥት ተቺዎች እና ሃሳባቸውን የሚገልጹ ዜጎች ላይ በምታሳርፈው ጫና በየጊዜው በመብት ተሟጋቾች ትወቀሳለች የሚሉ ወገኖች በበኩላቸው የጋራ ብልጽግናውን ጉባኤ ማስተናገድ አልነበረባትም ባይ ናቸው። ብሪታንያዊቱ ደራሲ እና የቀድሞ ጋዜጠኛ ሚሻኤላ ሮንግ ጉባኤው ሩዋንዳ ላይ መካሄድ አልነበረበትም ያለችበትን ምክንያት ገልጻለች።

Boris Johnson UK und  Paul Kagame Ruanda
ኮሪስ ጆንሰን እና ፖል ካጋሜምስል Dan Kitwood/ASSOCIATED PRESS/picture alliance

«እኔ ከጻፍኳቸው የአፍሪቃ መሪዎች ሁሉ ፖል ካጋሜ ስለ ገጽታ ጠቃሚነት የተሻለ ያውቃሉ። ዋና ከተማዋን ከአመድ ተነስቶ ከፍ ለማለት የዓለም አቀፍ ማስታወቂያ ሰሌዳዎች መለያ ማድረግ ከቻሉ ረዥም ዓመት ሆኗል። እነዚህን ከፍ አድርጎ የማሳየት ድሉ ደግሞ ለዓለም የትኩረት ገበያው ያቀረቡት ዝርዝር አካል ነው። ይኽ የገጽታ ግንባታ ገበያ ነው የብሪታንያውን ወግ አጥባቂ መንግሥት ጥገኝነት ፈላጊዎችን የሚልክበት ትክክለኛ ቦታ እንደሆነ ያሳመነው። ነገር ግን ይኽን የተዋበ ድንጋይ ብታነሳው ከስሩ የተደበቀውን ጉድ ታያለህ።»

ኪጋሊ በጎርጎሪዮሳዊው 2021 ዓ,ም ከ3,500 የሚበልጡ ጋዜጠኞች፣ ዲፕሎማቶች እና የውጪ ሃገራት ፖለቲከኞችን ስልኮች ፔጋሰስ በተባለው የስለላ የኮምፕዩተር ፕሮግራም አማካኝነት በመጥለፍ ተከሳለች። ይኽ የስለላ ፕሮግራም የሚጠልፈውን ሰው ስልክ የግል ብቻ የሆኑ መረጃዎችን ሳይቀር እንደሚያወጣ ነው የተገለጸው። ሚሻኤላ ሮንግ ለዓለም አቀፍ የመብት ደንቦች አትገዛም የምትላት ሩዋንዳ ከአምስት ሺህ የሚልቁትን የጉባኤውን ተሳታፊዎች የግል መብቶች የሚጥሱ ተግባራት ሊፈጸሙ ይችላሉ ስትል አስጠንቅቃለች።

Ruanda Kigali | Commonwealth  Gipfeltreffen CHOGM
ከጉባኤው ተሳታፊዎች በከፊልምስል Luke Dray/Getty Images

«የጉባኤው ተሳታፊች ሩዋንዳ ውስጥ በሚቆዩበት ጊዜ በተንቀሳቃሹ ስልካቸው የሆድ የሆዳቸውን እንዳያወሩ ምክር ይሰጣቸዋል። ምክንያቱም የፔጋሰስ ሶፍትዌር ተጠቃሚ የሆመችው ሩዋንዳ ለጉብኝት የሚመጡ ሚኒስትሮችም ሆኑ የሃገራት መሪዎች ላይም ተመሳሳይ ድርጊት ትፈጽማለች። ከዚህ በፊት ማስታወሻ ደብተሮቻቸው እና ላፕቶፖቻቸው የገቡበት ያልታወቀ ጋዜጠኞች እና የሌሎች ሃገራት ባለሥልጣናትን በማሰብም በሆቴል ክፍሎቻቸው ምንም አይነት ነገር ላለመተው ጥንቃቄ ያደርጋሉ። »

Ruanda | Flüchtlingskrise
ምስል Victoria Jones/empics/picture alliance

ይኽን መሰሉ መረጃ እያለ ሩዋንዳ ይኽን የጋራ ብልጽግና አባል ሃገራትን ጉባኤ እንድታስተናግድ መወሰኑ የተሳሳተ ምልክት ያስተላልፋልም ባይ ናት ሮንግ። ምንም እንኳን ሩዋንዳ ከደሃዎቹ የአፍሪቃ ሃገራት አንዷ ብትኾንም ኪጋሊ የመጣ እንግዳ እንዴት የሚለምን ሰው የለም ብሎ ሊገረም ይችላል። ነገሩ ወዲህ ነው ትላለች እንግሊዛዊቱ ደራሲ እና የቀድሞ ጋዜጠኛ። ኪጋሊ የትኛውንም ዓለም አቀፍ ጉባኤ የምታስተናግድ ከሆነ የኔ ቢጤዎቹ ለስልጠና በሚል ማዕከል እንዲሰበሰቡ እንደሚደረግ ሂውማን ራይትስ ዎች ይፋ ያደረጉንም አንስታለች።

የጋራ ብልጽግና አባል ሃገራት ጉባኤ በሚካሄድበት በዚህ ወቅት ሩዋንዳ ከጎረቤቷ ዴሞክራቲክ ሪፑብሊክ ኮንጎ ጋር M23 የተባለውን ታጣቂ ቡድን ትደግፋለች በሚል የተፈጠረው ውጥረት የጸጥታ ስጋት ባስከተለበት ወቅት ነው። ሩዋንዳ ባለፈው ግንቦት ወር ከባድ ጥቃት ያደረሰውን ይኽን ቡድን እንደማትደግፍ በተደጋጋሚ  አስተባብላለች። እንዲያም ሆኖ ባለፈው ሳምንት በሩዋንዳ እና ኮንጎ የጸጥታ ኃይሎች መካከል ድንበር ላይ ግጭት ከተፈጠረ በኋላ በሁለቱ ሃገራት ውጥረቱ ተባብሷል። የሩዋንዳ መንግሥት ቃል አቀባይ ዮላንዴ ማኮሎ ግን የጋራ ብልጽግና ጉባኤው ተሳታፊዎች የሚያሰጋቸው ነገር የለም ነው ያሉት። ድንበር ላይ የተፈጠረው ድንገተኛ አጋጣሚ መሆኑን በማመልከትም ተገቢው ምርመራ እየተካሄደ መሆኑን ገልጸው እንግዶቹ ዋና ከተማ ኪጋሌ ውስጥም ሆነ በየትኛውም የሀገሪቱ ክፍል ደህንነታቸው የተረጋገጠ እንደሆነ ለዶቼ ቬለ ገልጸዋል።

Ruanda Kigali | Commonwealth Gipfeltreffen CHOGM
ከጉባኤው ተሳታፊዎች በከፊልምስል SIMON WOHLFAHRT/AFP

ኪጋሌ ሩዋንዳ በሳምንቱ መባቻ የተጀመረው ጉባኤ ከትናንት ዓርብ ጀምሮ ደግሞ የጋራ ብርልጽግና አባል ሃገራት መሪዎች በስብሰባው ታድመዋል። የብሪታኒያው ጠቅላይ ሚኒስትር ቦሪስ ጆንሰን፣ የናይጀሪያው ሙሀማዱ ቡሀሪ፣ የዩጋንዳው ዩዌሪ ሙሴቪኒ፣ የካናዳው ጀስቲን ቱሩዶ፣ የሕንድ ጠቅላይ ሚኒስትር እና የውጭ ጉዳይ ሚኒስትርን ጨምሮ 26 የስብስቡ አባል ሃገራት መሪዎች መገኘታቸው ተገልጿል። መሪዎቹ የወቅቱን የዓለማችንን ዋነኛ መነጋገሪያ አጀንዳዎች  የአየር ንብረት ለውጥ፣ ድህነት እና የምግብ እጥረት ቀውስ ላይ ይነጋገራሉ። ከዚህም ሌላ የሻከረው የሩዋንዳ ኮንጎ ግንኙነት፣ የዩክሬን ጦርነት እንዲሁም ድህነት መሪዎቹ የሚወያዩባቸው ጉዳዮች ናቸው። ይኽ በእንዲህ እንዳለም የጋራ ብልጽግና በሚል የእንግሊዝ ቅኝ ግዛት ሃገራት የተሰባሰቡበት ሕብረት የበላይ የብሪታኒያዋ ንግሥት ኤልዛቤት በልጃቸው በልዑል ቻርለስ እንዲተኩ የዛሬ አራት ዓመት አባል ሃገራት ተስማምተው ነበር። ሆኖም ዘንድሮ ሩዋንዳ ላይ ከተሰባሰቡት አንዳንዶቹ በዚህ ውሳኔ ደስተኞች እንዳልሆኑ አመላክተዋል። የብሪታኒያዋ ንግሥት የዚህን ስብስብ የበላይ ኃላፊነት የተረከቡት ከአባታቸው ነበር። በዚህ አካሄድ ደግሞ ለልጃቸው ማውረስ ይጠበቅባቸዋል። ይኽን ከማይደግፉት አንዱ የብራዚሉ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር አካሄዱ ዳግም ሊቃኝ ይገባይ ነው የሚሉት። ብራዚል የእንግሊዝ ቅኝ ተገዢ ከነበሩ ከ12ቱ የካሪቢያን ሃገራት አንዷ ስትሆን በዚህ አካባቢ ከቅኝ ግዛት ነጻ ከወጡ በኋላ ከብሪታንያ ጋር ያላቸው ግንኙነት ጥያቄ ላይ ወድቋል።

ትኩረት ሳቢው የአፍሪቃው ቀንድ

China Djibouti Militärbasis
የቻይና ወታደራዊ ጣቢያ በጅቡቲምስል picture alliance/AP/Xinhua News Agencyvia/W. Dengfeng

ቻይና በአፍሪቃው ቀንድ አካባቢ በጸጥታው ጉዳይ የበኩሌን ሚና መጫወት እንደምትሻ ባሳለፍነው ሳምንት ውስጥ አዲስ አበባ ላይ ባካሄደችው ጉባኤ በጉልህ አሳይታለች። ለሁለት ቀናት የዘለቀው የጸጥታ፣ አስተዳደር እና ልማትን የተመለከተው የአፍሪቃ ቻይና ጉባኤ በአይነቱ የመጀመሪያ ነው። እርምጃውም በግጭት እና በጸጥታ ስጋት በሚታወቀው አካባቢ ቻይና የበኩሏን ተጽዕኖ የማድረግ አቅምዋን ለማሳየት ያለመ ነው ተብሏል። በአፍሪቃው ቀንድ የሚገኙት አብዛኞቹ ሃገራት በውስጣቸው በየራሳቸው ጉዳይ ፖለቲካው መረጋጋት የራቃቸው ከመሆናቸው በተጨማሪ በጉርብትና ደረጃም ችግሮች በየጊዜው አያጣቸውም። የአካባቢው ሃገራት ያልተረጋጋ የጸጥታ ይዞታ ደግሞ ቀይ ባሕርን ይዞ በሕንድ ውቅያኖስም ሆነ በአደን ባሕረ ሰላጤ ላይ ንግዳቸውን ለሚያንቀሳቅሱት ልዕለ ኃያል ሃገራት የስጋት ምንጭ መሆኑ በዘመናት ውስጥ የታየ ነው። ያላቸውን ጥቅም ለማስጠበቅ በሚልም በአካባቢው የባሕር አካላት ላይ ጥቂት የማይባሉ ምዕራባውያኑ ሃገራት የጦር ኃይል ሰፈሮችን አቋቁመዋል። ቻይናም ጅቡቲ ላይ ከገነባችው ወደብ በተጨማሪ የጦር ሰፈሯንም ተከትላለች። እንደ ሳውድ አረቢያ፣ ኢራን እንዲሁም አረብ ኤሜሬት ያሉት የአረብ ሃገራትም ተሰልፈዋል። ቤጂንግ ባለፈው የካቲት ወር ነበር ለአፍሪቃው ቀንድ የራሷን ልዩ መልእክተኛ መሰየሟን ይፋ ያደረገችው። በወቅቱ የቻይና የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር በኤርትራ፣ ኬንያ እንዲሁም ኮሞሮስ ጉብኝት አድርገው እንደነበር ይታወሳል። በአፍሪቃው ቀንድ የቻይና ልዩ መልእክተኛ ሹይ ቢንግ ሀገራቸው በአካባቢው የጸጥታ ጉዳይ የራሷን ሚና ለመጫወት መዘጋጀቷን አመልክተዋል። ቻይና በኢትዮጵያ ፌደራል መንግሥት እና ምክር ቤት በአሸባሪነት በፈረጀው ህወሃት መካከል የአደራዳሪነት ሚና ልትጫወት እንደምትችል ቢነገርም፣ እሳቸው ግን  በተቀናቃኝ ኃይሎችም ሆነ ሃገራት መካከል ቻይና የማደራደር ሚና እንድትጫወት ከተፈለገ እነዚህ ወገኖች አስቀድመው ይኹንታቸውን ማሳወቅ አለባቸው ነው ያሉት። ልዩ ልዑኩ በጉባኤው ላይ ባደረጉት ንግግር ሀገራቸው ቻይና የአፍሪቃው ቀን አካባቢ ሃገራት በመተባበር እና የፖለቲካ ብልሀት ልዩነቶቻቸውን መፍታት ይችላሉ ብላ እንደምታምን ገልጸዋል።

Deutsche Marine im Hafen von Djibouti
የጀርመን የባሕር ኃይል በጅቡቲምስል AP

«ከታሪክ የተማርነው የአፍሪቃው ቀንድ የማናቸውም ሀገር የግል ጓሮ መሆን እንደሌለበት ነው» ያሉት ሾይ ቢንግ፤ «ይልቁንም የአካባቢው ሃገራት ሕዝቦች የራሳቸው ዕጣ ፈንታ ኃላፊዎች መሆን አለባቸው።» በማለትን የሀገራቸውን አቋም አመላክተዋል።

Bundesmarine in Wilhelmshaven
የጀርመን የባሕር ኃይል በአፍሪቃው ቀንድምስል AP

 ቻይና በዚህ ሳምንት ስልታዊ ተፈላጊነት ባለው የአፍሪቃው ቀንድ ጉዳይ ከአካባቢው ሃገራት ጋር ያካሄደው ስብሰባ የምዕራባውያኑን ሃገራት ትኩረት ምን ያህል እንደሳበም ብሪታንያ የራሷን ልዩ መልእክተኛ በዚሁ ሳምንት መሰየሟ አመላካች ነው። ሎንደን በአረብ  በአፍሪቃ እና በተለያዩ ሃገራት በልዩ ልዩ ደረጃዎች ያገለገሉትን ሳራ ሞንትጎመሪን ለአፍሪቃው ቀንድ እና ለቀይ ባሕር አካባቢ ልዩ መልእክተኛ አድርጋ ሰይማለች። ልዩ መልዕክተኛዋ በባሕረ ሰላጤው ሃገራት የጸጥታ ጉዳይ ያላቸው የሥራ ልምድ ትኩረታቸው የቀይ ባሕር አካባቢ ላይ እንደሚሆን ያመላክታል ነው የሚሉት የምሥራቅ አፍሪቃ የደህንነት ጉዳይ ተቋም ተንታኝ ቤን ሁንተር። የብሪታንያ መንግሥት ለአካባቢው የራሱን ልዩ መልእክተኛ የሰየመው ከሰብአዊ ጉዳይ አንስቶ ቀውሱ በአካባቢው እየተባባሰ በመሄዱ እና ዩናይትድ ኪንግደም ደግሞ ባሕረ ሰላጤውን ተሻግሮ ከቀይ ባሕር አካባቢ ጋር ወሳኝ ቁርኝት ስላለኝ ነው ብሏል። ዩናይትድ ስቴትስ በበኩሏ በአጭር ጊዜያት ውስጥ ለሦስተኛ ጊዜ ለአፍሪቃው ቀንድ የተለያዩ ከፍተኛ ዲፕሎማቶቿን በመለዋወጥ ሰይማለች።

Äthiopien Addis Abeba Stadtansicht
ምስል Seyoum Getu/DW

የቻይና በዚህ ወቅት ወደ አፍሪቃው ቀንድ አካባቢ ማተኮር ባካባቢው የሚታዩ ውዝግቦችን ለማርገብ ከመፈለግ ባሻገር በየሃገራቱ ለመሰረተ ልማት ያፈሰሰችውን መዋዕለ ነዋይ ደህንነት ለመጠበቅ ነው የሚሉ አሉ።

በተለይ ጉባኤው ቀሪው ዓለም በዩክሬን ሩሲያ ጦርነት ትኩረቱ በተያዘበት በዚህ ወቅት መካሄዱ ቻይና የራሷን ኃይል እና ጉድኝት አፍሪቃ ላይ ልታጠናክር ፈልጋነው የሚል ጥርጣሬ አስነስቷል። ከዚህ በፊት ከተካሄዱ ጉባኤዎች ይኽኛው በምን ይለያል በሚል ጥርጣሬዎች እንዳሉ እናውቃለን ያሉት የኢትዮጵያ ጠቅላይ ሚኒስትር የጸጥታ ጉዳይ አማካሪ አምባሳደር ሬድዋን ሁሴንም ውጤቱንም ሆነ ተግባራዊ ርምጃዎቹን የጉዳዩ ባለቤቶች የማረጋገጥ ኃላፊነት እንዳለባቸው አመልክተዋል። የጉባኤው አነሳሾች፣ መሪዎችም ሆኑ የሚከታተሉት የአፍሪቃው ቀንድ ሃገራት መሆናቸውን ያመለከቱት የደህንነት አማካሪው የቻይና ሚና በሚፈለግ ጊዜ ድጋፍ ማድረግ ነው ብለዋል።

ሸዋዬ ለገሠ