የጉራፈርዳ ተፈናቃዮች ሮሮ
ዓርብ፣ መስከረም 14 2014ማስታወቂያ
በደቡብ ክልል ጉራፈርዳ ወረዳ በግጭት የተፈናቀሉ ነዋሪዎች መንግስት ወደ ቀድሞ ቀዬቸው ለመመለስ የገባውን ቃል ገቢራዊ ባለማደረጉ ለችግር ተዳርገናል አሉ። ከአስራ አምስት ሺህ በላይ የሚሆኑት እነኘሁ ተፈናቃዮች እስከአሁን ሲቀርብልን የነበረው የሰብአዊ የምግብ ድጋፍ ካለፉት ሶስት ወራት ወዲህ በመቋረጡ ከነቤተሰቦቻችን በረሀብ ውስጥ እንገኛለን ብለዋል።«ወይ ድጋፍ አላገኘን ወይ ወደ መንደራችን አልተመለስን እንዲሁ በመከራ ውስጥ እንገኛለን »ያሉት ነዋሪዎቹ መንግስት ለጥያቄያቸው ምላሽ እንዲሰጣቸው ጠይቀዋል።
አሁንም በከፊል ያልተመለሱ ተፈናቃዮች መኖራቸውን ያረጋገጡት የወረዳው የስራ ሃላፊዎች በበኩላቸው በአካባቢው ከሚገኙ የማህበረሰብ ክፍሎች ጋር ባህላዊ የእርቅ ሥረዓቶችን በማድረግ ነዋሪዎቹን ወደ ቀደመ መንደራቸው የመመለሱ ስራ ግን በማከናወን ላይ እንደሚገኝ ተናግረዋል። ለተፈናቃዮቹ የሰብአዊ የምግብ ድጋፍ ማቅረብ ያልተቻለው ወረዳው ለሚመለከታቸው የዞንና የክልል መስተዳደር ያቀረበው የድጋፍ ጥያቄ እስከሁን ምላሽ ባለማግኘቱ ነው ብለዋል።
ሸዋንግዛዉ ወጋየሁ
አዜብ ታደሰ
ማንተጋፍቶት ስለሺ