1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

የደቡብ ብሄር ፣ ብሄረሰቦችና ህዝቦች ክልል በሁለት ክልላዊ መዋቅሮች ሊከፈል ነው ፡፡

ሰኞ፣ ሐምሌ 25 2014

የጠበቅነው የዎላይታ ክልላዊ መንግሥት ተብሎ የሚጠራ ፣ አስተዳደራዊ መቀመጫው ዎላይታ ሶዶ የሆነ ፤ ዎላይተኛ የሥራ ቋንቋ ያለው አደረጃጀት ነበር ፡፡ ይሁንእንጂ ውሳኔው የህዝቡን ፍላጎት ያልጠበቀና በሥማ በለው የተወሰነ ነው ›› ብለዋል፡፡

https://p.dw.com/p/4Ey5m
Äthiopien SNNPR Entscheidung über neu errichtete Zonen
ምስል Shewangizaw Wegayehu/DW

የደቡብ ክልል ለሁለት ሊፈል ነው ተባለ

ከጉራጌ ክልል በስተቀር በክልሉ የሚገኙ 10 የዞን እና 6 የልዩ ወረዳ ምክር ቤቶች ባካሄዷቸው ጉባኤዎች አሁን ያለውን የደቡብ ክልል በሁለት ክልላዊ መስተዳድር ለማዋቀር ያስችላል የተባለውን ውሳኔ አሳልፈዋል፡፡ 
የሀዋሳው ወኪላችን ሸዋንግዛው ወጋየሁ በምክር ቤቶቹ ውሳኔ ዙሪያ የዞኖቹን ነዋሪዎችና የማህበረሰብ አንቂዎችን አስተያየት ያሰባሰበበትን ዘገባ ልኮልናል፡፡

በደቡብ ክልል የሚገኙ 10 ዞኖችና 6 የልዩ ወረዳ መስተደድር ም/ቤቶች አሁን ያለውን የደቡብ ክልል በሁለት አስተዳደር ለማዋቀር የሚያስችለውን ውሳኔ ባሳለፍነው ቅዳሜና እሁድ ባካሄዷቸው ጉባኤዎች አጽድቀዋል፡፡ በም/ቤቶቹ ውሳኔ መሠረት የዎላይታ ፣ የኮንሶ ፣ የጋሞ ፣ የጎፋ ፣ የደቡብ ኦሞ ዞኖች ከአማሮ ፣ ከቡርጂ ፣ ከአሌ ፣ ከደራሼ እና ከባስኬቶ ልዩ ወረዳዎች ጋር በመሆን በአንድ ክልል የሚደራጁ ይሆናል፡፡ እንዲሁም የሃድያ ፣ የጉራጌ ፣ የስልጤ ፣ የሀላባ ፣ የከንባታ ጠንባሮ ዞኖችና የየም ልዩ ወረዳ ደግሞ ራሱን በቻለ ሌላኛው ክልላዊ መንግሥት ሥር እንዲሆኑ ያስችላል ነው የተባለው ፡፡
እስከአሁን አዲሱን አደረጃጀት ከጉራጌ ዞን በስተቀር የሁሉንም ም/ቤቶች ይሁንታ ያገኘ ሲሆን የጉራጌ ዞን ም/ቤት ጉባኤውን በመጥራት በጉዳዩ ላይ ይመክራል ተብሎ እየተጠበቀ ይገኛል፡፡
በክልል ለመደራጀት የበረታ ግፊት ሲካሄድባቸው በቆዩ ዞኖች የም/ቤቶቹን ውሳኔ ተከትሎ አዎንታዊም አሉታዊም አስተያየቶች እየተሰነዘሩ ይገኛሉ፡፡ ዶቼ ቬለ DW በውሳኔው ዙሪያ ያነጋገራቸው አንዳንድ የዎላይታ ዞን ነዋሪዎች ከሌሎች ሕዝቦች ጋር በመሆን የጋራ ክልል መመሥረቱን በበጎ እንደሚያዩት ተናግረዋል፡፡
‹‹ ዎላይታ ተጎራብቶ እየኖረ ከሚገኘው ሌላው ህዝብ ጋር የአደረጃጀት ጥያቄ ኖረውም አልኖረውም በጋብቻ የተሳሰረ ፤ በጋራ የሚገበያይ በመሆኑ በአንድ ክልል ሥር መተዳደሩ ችግር የለውም ፡፡ ውሳኔው ህዝብን በሚወክሉ ምክር ቤቶች የተሰጠ በመሆኑ ደስተኞች ነን  ›› ብለዋል አስተያየት ሰጪዎቹ ፡፡ 
በአንጻሩ በዚሁ ዞን ከሚገኙ ነዋሪዎች መካከል ዎላይታ ከሌሎች ጋር ከሚሆን ይልቅ ራሱን በቻለ ክልል ቢደራጅ የተሻለ ነው የሚል አስተያየቶችን ሰንዝረዋል፡፡ አስተያየት ሰጪዎቹ ‹‹ እኛ የጠበቅነው የዎላይታ ክልላዊ መንግሥት ተብሎ የሚጠራ ፣ አስተዳደራዊ መቀመጫው ዎላይታ ሶዶ የሆነ ፤ ዎላይተኛ የሥራ ቋንቋ ያለው አደረጃጀት ነበር ፡፡ ይሁንእንጂ  ውሳኔው የህዝቡን ፍላጎት  ያልጠበቀና በሥማ በለው የተወሰነ ነው ›› ብለዋል፡፡
ዶቼቬለ DW በውሳኔው ላይ አስተያየታቸውን የጠየቃቸው  የማህበረሰብ አንቂና የዎላይታ ብሄር አባል የሆኑት አቶ አንዱአለም ታደሰ በበኩላቸው የም/ቤቱ ውሳኔ የሕዝብ ፍላጎት ባይሆንም ዕድሉን ወደ በጎ ለመቀየር መሥራት ይገባል ይላሉ፡፡
የጋራ አደረጃጀቱ በተለይ በፌደራል መንግሥት ደረጃ የተሻለ ውክልናና የመደራደር አቅምን ለመፍጠር ፤ጠንካራ የኢኮኖሚ አቅም ለመገንባት ያግዛል የሚል እምነት እንዳላቸውም አቶ አንዱዓለም  ተናግረዋል ፡፡
በደቡብ ክልል የመደራጀት ጥያቄ ጎልቶ መታየት የጀመረው በአገሪቱ በ2010 ዓ.ም. የመጣውን ፖለቲካዊ ለውጥ ተከትሎ ነው ፡፡ የአደረጃጀት ጥያቄው በተለይ በአንዳንድ ዞኖች ባስከተለው ግርግር የሰው ህይወት መጥፋት ፣ ለፖለቲከኞችና አንቂዎች መታሰር ምክንያት እስከመሆን ደርሶ እንደነበር የታወሳል፡፡

Äthiopien SNNPR Entscheidung über neu errichtete Zonen
ምስል Shewangizaw Wegayehu/DW
Äthiopien SNNPR Entscheidung über neu errichtete Zonen
ምስል Shewangizaw Wegayehu/DW

ሽዋንግዛው ወግአየሁ
ዮሐንስ ገብረእግዚአብሔር
ኂሩት መለሰ