1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

የደቡብ ክልል ሕዝበ ውሳኔ ውጤት በፌዴሬሽን ም/ቤት ጸደቀ

ረቡዕ፣ ሰኔ 28 2015

የኢፌዴሪ የፌዴሬሽን ምክር ቤት በደቡብ ክልል ስድስት ዞኖችና አምስት ልዩ ወረዳዎች በአንድ ያጋራ ክልል ለመደራጀት ያካሄዱትን የህዝበ ውሳኔ ውጤት አጸደቀ። በምክር ቤቱ የህዝበ ውሳኔ ውጤት መሠረት ስድስቱ ዞኖች እና አምስቱ ልዩ ወረዳዎች ከደቡብ ክልል በመነጠል ለፌዴራል ሪፐብሊኩ 12ኛ የሆነ አዲስ ክልላዊ መንግሥት የሚመሠርቱ ይሆናል።

https://p.dw.com/p/4TSGO
Logo Äthiopiens Nationale Wahlbehörde
ምስል Ethiopian National Election Board

«ሁለት ፓርቲዎች ተቃውመዋል»

የኢፌዴሪ የፌዴሬሽን ምክር ቤት በደቡብ ክልል ስድስት ዞኖችና አምስት ልዩ ወረዳዎች በአንድ ያጋራ ክልል ለመደራጀት ያካሄዱትን የህዝበ ውሳኔ ውጤት አጸደቀ። በምክር ቤቱ የህዝበ ውሳኔ ውጤት መሠረት ስድስቱ ዞኖች እና አምስቱ ልዩ ወረዳዎች ከደቡብ ክልል በመነጠል ለፌዴራል ሪፐብሊኩ 12ኛ የሆነ አዲስ ክልላዊ መንግሥት የሚመሠርቱ ይሆናል። በዎላይታ ዞን የሚንቀሳቀሱ የዎላይታ ብሔራዊ ንቅናቄ እና የዎላይታ ህዝቦች ዴሞክራሲያዊ ግንባር የተባሉ ተቃዋሚ ፓርቲዎች ለህዝበ ውሳኔው ሂደትም ሆነ ውጤት እውቅና እንደማይሰጡ ገልጸዋል። 

የኢፌዴሪ የፌዴሬሽን ምክር ቤት በደቡብ ክልል ስድስት ዞኖችና አምስት ልዩ ወረዳዎች በአንድ ያጋራ ክልል ለመደራጀት ያካሄዱትን የህዝበ ውሳኔ ውጤት አጸደቀ። ምክር ቤቱ ውጤቱን ያጸደቀው ዛሬ ባካሄደው ስድስተኛ የፓርላማ ዘመን ሁለተኛ መደበኛ ስብሰባው ነው። የብሔራዊ ምርጫ ቦርድ ምክትል ሰብሳቢ አቶ ውብእሸት አየለ በዞኖቹና በልዩ ወረዳዎቹ የተካሄደውን የህዝበ ውሳኔ ውጤት ለምክር ቤቱ በንባብ አቅርበዋል። በህዝበ ውሳኔው 2 ሚሊየን 396 ሺህ መራጮች በጋራ ክልል መደራጀትን የደገፉ ሲሆን 120,268 ያህሉ ደግሞ የጋራ አደረጃጀቱን በመቃውም ድምፅ መስጠታቸውን ቦርዱ በሪፖርቱ አመልክቷል፡፡ በህዝበ ውሳኔው በአተገባበር ሂደት አጋጠሙ ያሏቸውን ችግሮችም በሪፖርታቸው የጠቀሱት ምክትል ሰብሳቢው «በአንዳንድ አካባቢዎች የወረዳ አመራሮች በምርጫ አስፈጻሚዎች ላይ ጫና ያደርጉ ነበር። እንዲሁም ዕድሜያቸው ከ18 ዓመት በታች የሆኑ ነዋሪዎች በምርጫው ተሳትፈው ተገኝተዋል» ብለዋል።

Die nationale Wahlbehörde Äthiopiens hat mit der Veröffentlichung der vorläufigen Ergebnisse des Wolaita-Referendums begonnen
ምስል Shewangizaw Wegayehu/DW

የቦርዱን የህዝበ ውሳኔ አፈጻጸም ያዳመጠው የፌዴሬሽን ምክር ቤት በበኩሉ በቀረበው ሪፖርት ላይ ከተወያየ በኋላ የህዝበ ውሳኔውን ውጤት በሙሉ ደምፅ ተቀብሎ አጽድቆታል። በዚህም መሠረት ላለፉት 30 ዓመታት ገደማ በደቡብ ክልል ሥር ሲተዳደሩ የቆዩት  የዎላይታ ፣ የጋሞ ፣ የጎፋ ፤ የኮንሶ ፣ የደቡብ ኦሞ ፣ የጌዲኦ ዞኖችና አንዲሁም የአማሮ ፣ ቡርጂ ፣ ደራሼ ፣ አሌ እና ባስኬቶ ልዩ ወረዳዎች የፌዴራል ሪፐብሊኩ 12ኛ ክልል ሆነው እንዲደራጁ ምክር ቤቱ ውሳኔ አሳልፏል። በአንጻሩ የሃድያ፣ የከንባታ ጠንባሮ፣ የሀላባ፣ ሥልጤ፣ የጉራጌ ዞኖችና እና የየም ልዩ ወረዳ ራሳቸውን መልሰው በማደራጀት በነባሩ ክልል እንዲቀጥሉ ሲል ምክር ቤቱ ወስኗል። የኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ ያካሄደውን ህዝበ ውሳኔ በዎላይታ ዞን የሚንቀሳቀሱ የዎላይታ ብሔራዊ ንቅናቄ እና የዎላይታ ህዝቦች ዴሞክራሲያዊ ግንባር የተባሉ ተቃዋሚ ፓርቲዎች ለህዝበ ውሳኔው ሂደትም ሆነ ውጤት እውቅና እንደማይሰጡ እየገለጹ ይገኛሉ። በዛሬ የፌዴሬሽን ምክር ቤት ውሳኔውን በተመለከተ በዶቼ ቬለ አስተያየታቸውን የተጠየቁት የዎላይታ ብሔራዊ ንቅናቄ ሊቀመንበር አቶ አማኑኤል ሞጊሶ «ፓርቲያቸው ውሳኔውን የማይቀበልበትን ምክንያት ሲያብራሩ» ህዝበ ውሳኔው በዓለም አቀፍ ደረጃ የተቀመጡ መሥፈርቶችን የሚያሟላ አይደለም። በዞኑ መምረጥ ከሚችለው 30 በመቶ ያህሉ እንኳን ያልተሳተፈበት ህዝበ ውሳኔ ነው። በተጨማሪም የዎላይታ ህዝብ ራሱን በቻለ ክልል መደራጀት የሚለውን አማራጭ ድምጽ የነገፈ ነው» ብለዋል። ሁለቱ ተቃዋሚ ፓርቲዎች የፌዴሬሽን ምክር ቤት ኢ ሕገመንግሥታዊ በሆነ መንገድ  ፈጽሞታል ያሉትን ህዝበ ውሳኔ ውድቅ ለማስደረግ ጉዳዩን ወደ ፍርድ ቤት መውሰዳቸውንም ነው አቶ አማኑኤል የተናገሩት። በፓርቲዎቹ ክስ የተመሰረተባቸው የፌዴሬሽን ምክር ቤትም ሆነ ገዢው የብልፅግና ፓርቲ እስካሁን በጉዳዩ ላይ የሰጡት ምላሽ የለም።

ሸዋንግዛው ወጋየሁ

ሸዋዬ ለገሠ

ኂሩት መለሰ