1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

የደቡብ ሕዝበ ውሳኔ ውጤት ምን ገጠመው?

ማክሰኞ፣ የካቲት 14 2015

የኢትዮጵያ ብሄራዊ ምርጫ ቦርድ ባወጣው የጊዜ ሠሌዳ መሠረት በደቡብ ክልል የተካሄደው የህዝበ ውሳኔ ወጤት ባለፍው ረቡዕ መገለጽ ነበረበት ፡፡ ይሁን እንጂ ቦርዱ ውጤቱ ከሦስት ቀናት በኋላ ነበር ይፋ የሆነዉ፡፡ ህዝበ ውሳኔው ከተካሄደባቸው ዞኖችና ልዩ ወረዳዎች መካከል ከዎላይታ ዞን በስተቀር የሁሉንም የድምፅ ቆጠራ ውጤት ቦርዱ አስታውቋል።

https://p.dw.com/p/4NnT0
Logo Äthiopiens Nationale Wahlbehörde
ምስል Ethiopian National Election Board

ቦርዱ “ ከባድ “ ሲል የገለጸው የአሠራር ጥሰት መፈፀሙን ጠቁሟል

የኢትዮጵያ ብሄራዊ ምርጫ ቦርድ ባወጣው የጊዜ ሠሌዳ መሠረት በደቡብ ክልል የተካሄደው የህዝበ ውሳኔው የምርጫ ወጤት ባለፍው ረቡዕ የካቲት 8 2015 ዓም መገለጽ ነበረበት ፡፡ ይሁንእንጂ ቦርዱ የድምፅ ቆጠራውን  ውጤት ከሦስት ቀናት በኋላ ነበር ባለፋው ቅዳሜ ይፋ ያደረገው ፡፡ ህዝበ ውሳኔው ከተካሄደባቸው ዞኖችና ልዩ ወረዳዎች መካከል ከዎላይታ ዞን በስተቀር የሁሉንም  የድምፅ ቆጠራ ውጤት ቦርዱ አስታውቋል።

በቦርዱ መግለጫ መሠረት ውጤታቸው የተገለጸባቸው አካባቢዎች  የጋሞ ፣ የጎፋ ፣ የጌዴ ፣ ኮንሶና የደቡብ ኦሞ ዞኖችና እንዲሁም  የአማሮ ፣ የቡርጂ ፣ የደራሼ፣ የአሌ እና የባስኬቶ ልዩ ወረዳዎች ናቸው ፡፡በእነኝህ ዞኖችና ወረዳዎች “ በጋራ ክልል መደራጀትን እደግፋለሁ “ የሚለው አማራጭ አብላጫ ድምፅ ማግኘቱን የቦርዱ ኀሃዛዊ የቆጠራ ውጤት ያመለክታል፡፡

በጋሞ ከ733 ሺህ መራጮች መካከል 583 ሺህ ያህሉ ፣  በጎፋ  ከ352 ሺህ መራጮች መካከል 243 ሺህ ያህሉ ፣  በጌዴኦ ከ412 ሺህ መራጮች መካከል 241 ሺህ ያህሉ ፣  በደቡብ አሞ  ከ372 ሺህ መራጮች መካከል 256 ሺህ ያህሉ ፤ በኮንሶ ከ130 ሺህ መራጮች መካከል 101 ሺህ ያህሉ ፤ በአማሮ ከ117 ሺህ መራጮች መካከል 90 ሺህ  ያህሉ ፣  በቡርጂ ከ42 ሺህ መራጮች መካከል 28 ሺህ ያህሉ ፤ በደራሼ ከ71 ሺህ መራጮች መካከል 51 ሺህ ያህሉ ፤  በአሌ  ከ41 ሺህ መራጮች መካከል  22 ሺህ  ያህሉ ፤ በባስኬቶ   ከ41 ሺህ መራጮች መካከል  27 ሺህ መራጮች ያህሉ “ በጋራ መደራጀትን እደግፋለሁ “የሚለውን ለሚወክለው  የእርግብ ምልክት ድምጻቸውን መስጠታቸውን ቦርዱ አስታውቋል፡፡

Logo der nationalen Wahlbehörde von Äthiopien
የኢትዮጵያ ምርጫ ቦርድ በደቡብክልል አቅርቧቸው የነበሩ የምርጫ መለያዎች ከማኅደራችን

በአንጻሩ በጋሞ 9 ሺህ 682 ፣  በጎፋ  12 ሺህ 306  ፣  በጌዴኦ 46 ሺህ 749 ፣ በደቡብ አሞ  5 ሺህ 364 ፤ በኮንሶ 1 ሺህ 890  ፤ በአማሮ 216 ፣ በባስኬቶ   1 ሺህ 133  ፤ በቡርጂ 765 ፤ በደራሼ 453 ፤  በአሌ 412 መራጮች “ በጋራ መደራጀትን አልደግፍም “ የሚለውን ለሚወክለው  የጎጆ ቤት ምልክት ድምጻቸውን መስጠታቸውን ቦርዱ ጨምሮ ገልጿል፡፡ 

አወዛጋቢው የዎላይታ ሕዝበ ውሳኔ  

የኢትዮጵያ ብሄራዊ ምርጫ ቦርድ በደቡብ ሕዝበ ውሳኔ የአምስት ዞኖችና የአምስት ልዩ ወረዳዎችን የድምፅ ቆጠራ ውጤት ቢገልፅም በወላይታ ዞን ላይ የውጤቱን ህጋዊነት ለማረጋገጥ መቸገሩን አስታውቋል፡፡ በዞኑ በመራጮች መዝገብና በድምፅ መስጫ ዕለት ጥቂት በማይባሉ የምርጫ ጣቢያዎች ላይ ቦርዱ “ ከባድ “ ሲል የገለጸው የአሠራር ጥሰት መፈፀሙን በመግለጫው ጠቁሟል፡፡ 

ከተፈፀሙት የህግ ጥሰቶች መካከል በድምፅ መስጫ ዕለት የተሰጡ ድምፆች ቀደምሲል በጣቢያው ከተመዘገበው መራጭ ቁጥር በላይ ሆኖ መገኘት ፤ ብዛት ያላቸው የድምፅ መስጫ ወረቀቶች በአንድ ላይ ተጣጥፈው በሳጥን ውስጥ መገኘታቸው ፤ ድምፅ ለመስጠት ለተሰለፉ መራጮች የአካባቢው አስተዳደር አካላት ጊዜያዊ የመታወቂያ ወረቀት ማደል የሚሉት ይገኙባቸዋል፡፡

አሁን ላይ በዞኑ ተፈፅሟል የተባለውን የምርጫ ህግ ጥሰት ስፋትና መጠን ለማወቅ ምርመራ መጀመሩን የጠቀሰው ቦርዱ በምርመራው ውጤት መሠረትም የመጨረሻ ውሳኔ እንደሚሰጥ አስታውቋል።

በጉዳዩ ላይ ገለልተኛ የምርጫ ታዛቢዎችና የፖለቲካ ፓርቲዎች ምን አሉ? 

ለህግ ጥሰት ተዳርጓል በተባለው የዎላይታ ዞን የህዝበ ውሳኔ  ሂደት በቅርበት እየተከታተሉ የሚገኙ አካላት የየበኩላቸውን ሀሳብ አያንፀባረቁ ይገኛሉ ፡፡ በተለይም በምርጫ ታዛቢነት ሲሳተፉ የነበሩ የሲቪል ማህበራት እና ሂደቱን ከጅመሩ ሲተቹ የቆዩ የፖለቲካ ፓርቲዎች በቦርዱ መግለጫ ዙሪያ አዎንታዊም አሉታዊም አስተያየቶችን  አየሰነዘሩ ይገኛሉ ፡፡

Äthiopien Nationale Wahlbehörde hat zehn Wahllokale in den Zonen Wolaita und Gofa geschlossen
የኢትዮጵያ ምርጫ ቦርድ የምርጫ መቀስቀሻ ጽሑፍ ከማኅደራችንምስል Shewangizaw Wegayehu/DW

አቶ አበራ ኀ/ማሪያም በህዝበ ውሳኔው በምርጫ ታዛቢነት የተሳተፈውና የኢትዮጵያ ሲቪል ማህበራት ለምርጫ በመባል የሚታወቀው ድርጅት ዋና ዳይሬክተር ናቸው ፡፡ አቶ አበራ ድርጅታቸው በህዝበ ውሳኔው የመራጮች ምዝገባና በድምፅ መስጫ ቀን ታይተዋል ያላቸውን የህግ ጥሰቶች ለቦርዱ ሪፖርት ማድረጉን ይናገራሉ ፡፡ አሁን ላይ ቦርዱ የወሰደው እርምጃ አግባብነት ያለው የሚል አምነት እንዳላቸው  የሚናገሩት አቶ አበራ “ ቦርዱ በህግ ጥሰቱ ላይ ጊዜ ወስዶ መመርመሩ አግባብነት ያለው አካሄድ ነው ፡፡  ጥርጣሬ በተነሳባቸው ጣቢያዎች ላይ ተጨማሪ ምርመራ ማድረጉ የቦርዱን ጥንካሬ የሚያመለክት ነው ፡፡ ምርመራው የምርጫ  ውጤቱን በከፊል  ለመቀበል አሊያም  ሙሉ በሙሉ ሰርዞ በድጋሚ ለማካሄድ የሚያበቃው ውሳኔ ላይ ለመድረስ ያስችለዋል “ ብለዋል ፡፡

አቶ ጎበዜ ጎአ በዎላይታ ዞን የሚንቀሳቀሰው የዎላይታ ህዝቦች ዴሞክራሲያዊ ግንባር ሊቀመንበር ናቸው ፡፡ በምርጫ ቦርድ መግለጫ ዙሪያ የእርስዎና የድርጅትዎ አቋም ምንድ ነው በሚል በዶቼ ቬለ የተጠየቁት  አቶ ጎበዜ ህዝበ ውሳኔው ከመነሻው የህገ መንግሥት ጥሰት ያለበት ነው ሲሉ መልሰዋል፡፡ ህዝበ ውሳኔው አማራጭ ሀሳቦችን ያላካተተና በርካታ ጉድለቶች እንዳሉበት የጠቀሱት ሊቀመንበሩ “ ድርጅታችን በተደጋጋሚ ሲያወጣቸው በነበሩ መግለጫዎች ምርጫው የአንድ ወገን ጫና እንዳለበት ሥንገልፅ ነው የቆየው ፡፡ አሁንም የምርጫ ቦርድ የጀመረውን ምርመራ በቅርበት እየተከታተልን እንገኛለን ፡፡ ድርጅታችን በቀጣይ ቀናት በጉዳዩ ዙሪያ ዝርዝር መግለጫዎችን የሚያወጣ ይሆናል “ ብለዋል፡፡

ሸዋንግዛዉ ወጋየሁ

አዜብ ታደሰ

ኂሩት መለሰ