የዘገየው ፀረ ኤቦላ ርዳታ
ረቡዕ፣ ጥር 20 2007በኤቦላ የተጠቃው ይኸው አካባቢ በዚሁ ሰበብ በኤኮኖሚው ላይ የደረሰበትን ጉዳት ለመቀነስ፣ እንዲሁም፣ ወደፊት ወረርሽኙ ከመከሰቱ በፊት አካባቢው ራሱን ለመከላከል ዝግጁ የሚሆንበትን ሁኔታ ለማመቻቸት የሚያስችለው ለረጅም ጊዜ የሚዘልቅ ርዳታ ያስፈልገዋል።
በአዳጊ ሀገራት የሚገኙት ሕፃናትን ጤንነት በተሻለ ዘዴ ለመጠበቅ የሚያስችሉ ክትባቶች ምርት ከፍ እንዲል ዘመቻ የጀመረው በምሕፃሩ ጋቪ በመባል የሚታወቀው ዓለም አቀፍ ህብረት ትናንት በበርሊን ያካሄደው ጉባዔ የተሳካ ውጤት እንዳስገኘለት ተገለጸ። በጉባዔው የተሳተፉት ሀገራት እና ከ15 ዓመት በፊት በዳቦስ፣ ስዊትዘርላንድ ለቋቋመው ህብረት ዓላማ ማሳኪያ በሚቀጥሉት አምስት ዓመታት 7,5 ቢልዮን ዩኤስ ዶላር ርዳታ ለመስጠት ቃል ገብተውለታል። ጀርመንም በዚሁ ጊዜ ለህብረቱ 600 ሚልዮን ዩሮ እንደምትሰጥ አስታውቃለች። ለክትባቱ ርዳታ ለመስጠት በወቅቱ የታየው ይህ ዓይነቱ ተነሳሽነት ግንበኤቦላ ወረርሽኝ አስተላላፊ ተኀዋሲ የሚያዘው ሰው ቁጥር እየቀነሰ በሄደባት ምዕራብ አፍሪቃ አኳያ እጅግ እንደዘገየ ነው የተነገረው። ሁኔታውን ወደ ሲየራ ልዮን በመሄድ በቅርብ የተከታተሉት ድንበር የማይገድበው የሀኪሞች ድርጅት፣ የጀርመን ቅርንጫፍ የቀድሞ ዋና ስራ አስኪያጅ ሀኪም ፍራንክ ደርነር እንዳስረዱት፣ የርዳታው መዘግየት ክትባቱን የመሞከሩን ሂደት አዳጋች አድርጎታል።
« ዓለም አቀፉ ማህበረሰብ በኤቦላ ወረርሽኝ አኳያ ተገቢውን ምላሽ እስኪሰጥ ድረስ ብዙ ጊዜ ነበር የወሰደበት። ይህ በፖለቲካው ዘርፍ በታየው ቸልተኝነት ሰበብ ብቻ ሳይሆን፣ ይህን የመሰለ ወረርሽኝን ለመታገል የሚያስፈልገው ተሞክሮ ያለው የሰው ኃይል ተጓድሎም በመገኘቱ ጭምር ነው። »
ከዚህ በተጨማሪ፣ እንደ ፍራንክ ደርነር ገለጻ፣ ወረርሽኙ የተከሰተባቸው የጊኒ፣ ላይቤሪያ እና ሲየራ ልዮን ደካማ መሠረተ ልማትም ሌላ እክል የደቀነ ሌላ ችግር ነው።
« ግልጽ መሆን ያለበት ጉዳይ የምንናገረው በዓለም እጅግ ችላ ስለተባሉ እና ረጅም የርስ በርስ ጦርነት ስለተካሄደባቸው ሀገራት የጤና ጥበቃ አውታር ነው። የነዚህ ሀገራት የጤና ጥበቃ አውታር ገና የኤቦላ ወረርሽኝ ከመከሰቱ በፊትም በጣም የተዳከመ ነው። እንዲያውም፣ ወረርሽኙ የሶስቱን ሀገራት የጤና ጥበቃ አውታር ይበልጡን ጎድቶታል፣ የሌለ ያህል ይቆጠራል ለማለት ይቻላል። »
በዓለም አቀፍ የጤና ጥበቃ ድርጅት ዘገባ መሠረት፣ በወረርሽኙ አስተላላፊ ተኀዋሲ እስካሁን 8,700 ሰዎች ሞተዋል። 22,000 ደግሞ በተኀዋሲው ሳይያዙ አልቀሩም ተብለው ተጠርጥረዋል። ወረርሽኙ በሀገራቱ የግብርና ዘርፍ እና በኤኮኖሚ ላይ ከፍተኛ ጉዳት ማድረሱን የዓለም ባንክ የምዕራብ አፍሪቃ ጉዳይ ተከታታይ ቬራ ሶንግዌ አስታውቀዋል።
« ከጠቅላላ ምርታቸው ወደ ሁለት ከመቶ የሚጠጋው ቀንሶዋል። የዋጋ ግሽበቱ እስከ ሶስት፣ አራት ከመቶ ከፍ ብሎዋል። በላይቤሪያ የማዕድን ዘርፍ 20,000 ሰው ስራውን አጥቶዋል። ተቋማት እየዘጉ ነው። በኤቦላ ያልተጎዱ ጋምቢያን የመሳሰሉ ሀገራት እንኳን የቱሪስቱ ቁጥር ከ40 እስከ 60 ከመቶ ቀንሶዋል። ይህ ትልቅ ክስረት ነው። የኤቦላ ተፅዕኖ ደቡብ አፍሪቃን እና ኬንያንም እንደነካ ተመልክተናል።
ሁኔታዎች እስኪሻሻሉ ድረስ ገና ብዙ ወራት እንደሚያስፈልግ የዓለም ጤና ጥበቃ ድርጅት ፕሬዚደንት ማርግሬት ቻንግ በመግለፅ ወደፊት ኤቦላን የመሳሰሉ ወረርሽኞችን በተሻለ መንገድ ለመቋቋም ሀገራት ትብብራቸውን ማጠናከር እንደሚኖርባቸው አሳስበዋል፣ ይህ ብቻውን በቂ እንዳልሆነ የገለጹት ፍራንክ ደርነር በወረርሽኙ በሚጠቁ ሀገራት ውስጥ በሚገባ የሚሰራ የተጠናከረ፣ በቂ ተሞክሮ ያላቸው ባለሙያዎች የሚያጠቃልል የጤና ጥበቃ አውታር ሊኖር እንደሚገባ አስታውቀዋል። የዓለም ባንክ ባልደረባ ቬራ ሶንግዌ ደግሞ በወረርሽኙ የተጠቁት የምዕራብ አፍሪቃ ሀገራት ስር ነቀል መዋቅራዊ ለውጥ ማድረግ እንደሚኖርባቸው ነው ያመለከቱት።
ፊሊፕ ዛንድነር/አርያም ተክሌ
ነጋሽ መሀመድ