1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

የዘንድሮ ኢሬቻ በዓል አከባበርና ዝግጅቱ

ሥዩም ጌቱ
ሐሙስ፣ መስከረም 16 2017

የዘንድሮ 2017 ዓ.ም የኢሬቻ በዓል መስከረም 25 እና መስከረም 26 ይከበራል ሲል የኦሮሞ አባገዳዎች ህብረት አስታወቀ፡፡ አዲስ አበባ የሚከበረው ኢሬቻ ሆራ-ፊንፊኔ ቅዳሜ መስከረም 25 እንዲሁም ቢሾፍቱ የሚከበረው ኢሬቻ-ሆራ-አርሰዲ በማግስቱ እሁድ መስከረም 26 ቀን 2017 ኣ.ም. እንደሚከበር ህብረቱ አስታውቋል፡፡

https://p.dw.com/p/4l7Qj
ኤሪቻ አከባበር
ኤሪቻ አከባበር ምስል Seyoum Getu/DW

የኢሪቻ አከባበር ዝግጅት

የዘንድሮ ኢሬቻ በዓል አከባበርና ትኩረቱ

የዘንድሮ 2017 ዓ.ም የኢሬቻ በዓል መስከረም 25 እና መስከረም 26 ይከበራል ሲል የኦሮሞ አባገዳዎች ህብረት አስታወቀ፡፡ ዛሬ በዓሉ የሚከበርበት ቀንን የቆረጠው ህብረቱ አዲስ አበባ የሚከበረው ኢሬቻ ሆራ-ፊንፊኔ ቅዳሜ መስከረም 25 እንዲሁም ቢሾፍቱ የሚከበረው ኢሬቻ-ሆራ-አርሰዲ በማግስቱ እሁድ መስከረም 26 ቀን 2017 ኣ.ም. እንደሚከበር አስታውቋል፡፡ ከኢሬቻ አከባበር ጋር አንድነት እና ሰላም ጉልቶ የሚቀርብ ጥሪ ነው ተብሎለታልም፡፡ የኦሮሞ አባገዳዎች ህብረት ዛሬ በኦሮሚያ በዋናነት የሚከበሩትን የኢሬቻ አከባበር ቀናትን ስቆርጥ፤ በዓሉ ከኦሮሚያ ክልል ውጪ በቤንሻንጉል ክልል ጥቅምት 03 እንዲሁም በጋምቤላ ክልል ጥቅምት 10 ቀን 2017 ዓ.ም. እንደሚከበርም ይፋ አድርጓል፡፡

ከዚያም ባሻገር እስከ ጥቅምት 30 ድረስ ኢሬቻ በተለያዩ አከባቢዎች ስርዓቱን አሟልቶ እንደሚከበርም ህብረቱ አመልክቷል፡፡ ይህ በተለያዩ አከባቢዎች በተለያዩ ጊዜያት የሚከበረው የኢሬቻ በዓል ላይ ከውጪና ከአገር ውስጥ የሚሳተፉ ወገኖች የበዓሉን ወግ ጠብቆ በፍቅርና በአንድነት እንዲከበርም ተጠይቋል፡፡

ኢሬቻን እንደ ትልቅ የባህል ፌስቲቫል

የኦሮሞ አባገዳዎች ህብረት ዋና ጸኃፊና የቱለማ አባገዳ ጎበና ሆላ ይህንኑን አስመልክተው ለዶይቼ ቬለ በሰጡት አስተያየት በያመቱ በሚሊየኖች ተሳትፎ የሚከበረው የኢሬቻ በዓል አከባበር እያደገና እየተወደደ እንደመጣ አስረድተዋል፡፡ “በኢሬቻ አከባበር ላይ የኢትዮጵያ ብሔር ብሔረሰብ ጭምር እያሳደገ ያየመጣው ግንዛቤ ተወዳጅነቱን ከፍ እያደረገ መጥቷል፡፡ ይህ ደግሞ በያመቱ በአደባባይ በትልቅ ስነስርዓት የሚከበረውን ዓመታዊ የበዓሉን አከባበር ከፍተኛ ድደምቀት እየሰጠው መጥቷል፡፡ እናም የዘንድሮም ከባለፉት ዓመታት በላቀ የአገር ውስጥ እና ከአገር ውጪ የሚመጡ በርካታ የኦሮሞ ህዝብ ብሎም ብሔርብሄረሰብ እና የውጪ ዜጎች ተሳትፎ እንደሚከበር ከግንዛቤ ውስጥ ገብቶ ነው ዝግጅት እየተደረገበት ያለው፡፡ በዚህ በዓል ከአገር ውጪ የሚመጡ የጎብኚዎችም ቁጥር ይልቃል ብለን እንጠብቃለን” ብለዋል፡፡

ከዘንድሮ የኢሬቻ በዓል አከባበር ጋር ተያይዞ እየተደረገ ያለው ዝግጅት ከወዲሁ መጀመሩን የኦሮሚያ ክልል መንግስትም ደጋግሞ አንስቷል፡፡ በተለይም የክልሉ ርዕሰ መስተዳድር አቶ ሽመልስ አብዲሳ የዘንድሮ ኢሬቻ የእርቅና የሰላም ማምጫ ምክንያትም እንዲሆን በሚል በውጪ ላሉትም የኦሮሞ ህዝብ አስቀድሞ የተሳትፎ አድርጉ ጥሪ አቅርበው ነበር፡፡

ኤሪቻ
ኤሪቻ ምስል Seyoum Getu/DW

እሬቻ እና ሰላም

አባገዳ ጎበና ሆላም እንደሚሉት የኢሬቻ ስርዓትም ሆነ የገዳ ስርዓት በጥቅሉ ለሰላም የሚሰጠው ስፍራ ጉልህ መሆኑን ያስረዳሉ፡፡ “እኔ እንደቱለማ አባገዳ በትረ ስልጣኑን ከያዝኩበት የመጀመሪያዋ እለት ጀምሮ ሰላም የሚለው ቃል ከምላሰ ጠፍቶ አያውቅም፡፡ ሁሌም የሚያሳስበን የኦሮሞ ሰላምና አንድነት ነውናይህንኑን ሳስተጋባ ቆይቻለሁ፡፡ ኦሮሞ በሰላም ጥላ ስር በፖለቲካ እና ኢኮኖሚ እንዲገነባ ሁሌም ነው የምናሳስበው፡፡ ሰላም ለሰው ልጅ ህይወት ነው ብለንም ነው እኛ የምንረዳው፡፡ ለዛ ነው እንደ አባገዳ ሁሌም ሰላም እያልን ስለሰላም የምንጣራው፡፡ እናም ከሰላም ተስፋ አንቆርጥም፤ አሁንም ደጋግመን ሰላም ይሁን እያልን ነው፡፡ ከጦርነት የሚገኝ ትርፍ አመድ ብቻ ነው፡፡ ከሰላም ግን እድገት ልምላሜ ይገኛል ነው እኛ የምንለው፡፡ ለሃይማኖት አባቶች እና ለአገር ሽማግሌዎችም በዚህ ላይ እናተኩር የሚል ጥሪ ነው የምናቀርበው” ነው ያሉት፡፡

አባገዳ ጎበና ሆላ ኢሬቻ ሰላምንና አንድነትን ከማስፈን አኳያ ጉልህ ድርሻ እንዳለውም ሲያስረዱ፤ “በገዳ ስርዓት ስር በርካታ ነገሮች አሉ፡፡ ኢሬቻ አንዱ ነው፡፡ የኦሮሞ ህዝብ ማህበራዊና ፖለቲካዊ አገር በቀል እውቀት የሆነው የገዳ ስርዓት በተባበሩት መንግስታት የትምህርት፣ ሳይንስ እና ባህል ድርጅት ዩኔስኮ የማይዳሰስ ቅርስ ሆኖ ከ2008 ወዲህ እንደተመዘገበ ሁሉ ኢሬቻም በዚያው እራሱን ችሎ እንዲመዘገብ እየጣርን ነው፡፡ ኢሬቻ ያለው ውበት፤ የኦሮሞ ህዝብ ከጎረቤቱ እና ከብሔር ብሔረሰብ ጋር በሰላም እንዲኖር እንዲከባበር ያለው እሴት ጎልቶ ሊወሳለት የሚገባው ነው፡፡ እናም ጎረቤት አገራትንም ጭምር የሚያገናኘው ኢሬቻ የሰላም አንድነት ማሳያ ነው” ሲሉም አስተያየታቸውን ደምድመዋል፡፡ በኢሬቻ አከባበር ከእርቅ፣ ከፍቅር እና ከምስጋና በተቃርኖ መሄድ እንደማይገባም የአባገዳዎች ህብረት ዛሬ ባስተላለፉት መልእክት ገልጸዋል፡፡

 

ሥዩም ጌቱ

አዜብ ታደሰ

ታምራት ዲንሳ