1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

የዓረና ትግራይ ለጦርነቱ ውጤት ወቀሳ

ቅዳሜ፣ ጥቅምት 10 2016

የዓረና ትግራይ ሊቀመንበር አቶ ዓምዶም ገብረስላሴ፥ ጦርነቱ ከሀገሪቱ አልፎ ቀጠናው የበጠበጠ መሆኑ የገለፁ ሲሆን ማስቀረት የሚቻል ጦርነት በገዢዎች እብሪት የከፋ ሁኔታ ፈጥሯል ብለዋል።

https://p.dw.com/p/4Xr7r
አቶ ዓንዶም ገብረስላሴ የዓረና ትግራይ ሊቀመንበር
አቶ ዓንዶም ገብረስላሴ የዓረና ትግራይ ሊቀመንበርምስል Million Haileselassie/DW

ለጦርነቱ ውጤት የዓረና ወቀሳ

በትግራይ በተካሄደው ጦርነት ለደረሰው እልቂት ተጠያቂዎች ሀገሪቱ እያስተዳደረ ያለው ብልፅግና ፓርቲ እና ህወሓት ናቸው ሲል ተቃዋሚው ዓረና ትግራይ ለሉአላዊነት እና ለዴሞክራሲ ፓርቲ ከሰሰ። ዓረና ባለፈው ጦርነት ለደረሰ ጉዳት ተጠያቂነት ካልተረጋገጠ፣ ለመጪው ግዜ አደጋ ነው ብሏል። ዓረና በኢትዮጵያ የተለያዩ አካባቢዎች እየታዩ ያሉ ግጭቶች እንዲቆሙ እና ሁሉን አካታች ሰላማዊ የፖለቲካ መድረክ እንዲከፈትም ጥሪ አቅርቧል።

ከወቅታዊ ጉዳዮች ጋር በተያያዘ በትግራይ በተቃዋሚነት የሚንቀሳቀሰው ዓረና ትግራይ ለሉአላዊነት እና ዴሞክራሲ ባወጣው መግለጫ፥ በትግራይ የተደረገው ጦርነት በታሪክ ታይቶ የማይታወቅ እልቂት ያስከተለ፣ በህዝብ ላይ ከፍተኛ መከራ የፈጠረ፣ ኋላቀር እና የወደቀ የፖለቲካ አመራር የፈጠረው ደም አፋሳሽ ጦርነት መሆኑ አስታውቋል። ጦርነቱ 'ጀኖሳይዳዊ' "ብሎ የጠራው ተቃዋሚው ዓረና ትግራይ ለሉአላዊነት እና ዴሞክራሲ፥ ይህ እንዳይሆን ለማድረግ፣ የነበሩ ልዩነቶችበሰላማዊ መንገድ የመፍታት በርካታ ዕድሎች እና የተለያዩ ጥሪዎች ወደጎን በመግፋትም በአሁኑ ወቅት ሀገሪቱ እያስተዳደረ ያለው ገዢው ብልፅግና ፓርቲ እንዲሁም ትግራይን የሚገዛው ህዝባዊ ወያነ ሓርነት ትግራይ ህወሓትን ወቅሷል።

የዓረና ትግራይ ፓርቲ አርማ
የዓረና ትግራይ ፓርቲ አርማምስል DW/M. Haileselassie

የትግራይ ወጣቶች የተቃጣን ጥቃት ለመመከት፣ በህዝብ ላይ ይደርሱ የነበሩ በደሎች ለመከላከል፣ የትግራይ ከልላዊ አንድነት ለመመለስ ያደረጉት ትግል "ተፈጥሮአዊ ራስን የመከላከል" መብት ነው ብሎ የገለፀው ዓረና ትግራይ፥ ብቁ ወታደራዊ እና ፖለቲካዊ አመራር ባለማግኘቱ የሚፈለገው ድል ባያስመዘግብም፥ የትግራይ ወጣቶች መስዋእትነት ለፍትህ የተከፈለ በመሆኑ እስከወድያኛው በክብር የሚዘከር ነው ሲል ገልጿታል።

ያነጋገርናቸው የዓረና ትግራይ  ሊቀመንበር አቶ ዓምዶም ገብረስላሴ፥  ጦርነቱ ከሀገሪቱ አልፎ ቀጠናው የበጠበጠ መሆኑ የገለፁ ሲሆን ማስቀረት የሚቻል ጦርነት በገዢዎች እብሪት የከፋ ሁኔታ ፈጥሯል ብለዋል።

በቅርቡ በትግራይ ለደረሰው የበርካታ ወጣቶች እና አጠቃላይ እልቂት ተጠያቂነት ካልሰፈነ፣ ለቀጣይ ጥፋት አመቺ ሁኔታ መፍጠር መሆኑ አቶ ዓምዶም ጨምረው ገልጸዋል።

ከዚህ በተጨማሪ ዓረና፣ በአማራ ክልል ይሁን ሌላው የኢትዮጵያ ክፍል ያሉ ጦርነቶች በሰላማዊ መንገድ መቋጫ እንዲያገኙ ጥሪ አቅርቧል። በዚህ የዓረና ትግራይ መግለጫ ላይ ከህወሓት ከፍተኛ አመራሮች እና ከፌደራሉ መንግስት ባለስልጣናት ምላሽ ለማግኘት በስልክ ሙከራ ብናደርግም ለግዜው አልተሳካም።

ሚልዮን ሃይለስላሴ

ዮሃንስ ገብረእግዚአብሄር