የዓለም ፕሬስ ፎቶ ሽልማት 2017
የቱርካዊዉ ፎቶግራፍ ቀራጭ የቡራን ኦዝቢሊክ ፎቶ የዓመቱ ምርጥ የዓለም ፕሬስ ፎቶ ሆኖ ተመርጦአል። ፎቶዉ በአንካራ ቱርኩ በነበሩት የሩስያ አምባሳደር ላይ ግድያ እንደተፈፀመ የተነሳ ፎቶ ነዉ። ፎቶዉ በአሸናፊነት ለመረጡት ዳኞች ልክ እንደ አንድ «ከባድ ፈንጂ» አይነት ነዉ።
"የአንካራዉ ግድያ "
ታሕሳስ 10፤ 2009 ዓ.ም ቱርክ አንካራ ከተማ በአንድ የፎቶ ኤግዚቢሽን መክፈቻ ሥነ-ስርዓት ላይ የተገኙት የሩስያ አምባሳደር አንድሪ ካርሎቭ በአንድ የቱርክ ፖሊስ መገደላቸዉን የሚያሳየዉ ፎቶ የዓመቱ ምርጥ የዓለም ፕሬስ ፎቶ ተብሎ ሽልማትን አግኝቶአል። ፎቶዉ"ያለንበትን ዘመን የጥላቻ መንፈስ " ገላጭ ነዉ ሲሉ ፎቶዉን በአሸናፊነት የመረጡት ዳኞች ተናግረዋል። በቱርካዊዉ በቡራን ኦዝቢሊክ ከተቀረፀዉ ከዚህ ፎቶ ሌላ በአምስተርዳም ሆላንድ የሚገኙት የፎቶ ሽልማት ዳኞች በዓመት ዉስጥ የተነሱ ሌሎች ፎቶዎችም አልዋቸዉ።
በዘረኝነት ላይ ተቃውሞ
ይህ የዮናታን ባህማን ፎቶ የቅርብ ጊዜ ክስተት በሚል የፎቶ ሽልማት መዘርዝር ስር ዓለም ያየዉ ፎቶ ነዉ። በዚህ ፎቶ ላይ የ 28 ዓመትዋ የሰብዓዊ መብት ተሟጋች አሜሪካዊት ኢሻ ኢቫንስ ሐምሌ 2፤ 2008 ዓ.ም ሉዝያና ባታን ሩዥ ከተማ ዉስጥ በተካሄደ የተቃዉሞ ሰልፍ ተቃዉሞዉን ለመበተን ታጥቀዉ የተዘጋጁትን ፖሊሶች ብቻዋን ስትገጥም ይታያል። ባለፈዉ የጎርጎረሳዊ 2016 ዓ.ም ዉስጥ የዩኤስ አሜሪካ ፖሊሶች ይፈፅማሉ የተባለዉን የዘረኝነት የኃይል ጥቃትን በመቃወም ከፍተኛ ተቃዉሞ ታይቷል።
እስር በስድት
ይህ የዳንኤል ኢተር ፎቶ የዓመቱ ምርጥ ፎቶ በመባል ሦስተኛ ደረጃን ያገኘ ነዉ። ፎቶግራፉ ላይ ሁለት የናይጄርያ ስደተኛ ልጃገረዶች በጎርጎረሳዊ 2016 ዓ.ም በሊቢያ ዉስጥ በሚገኝ በአንድ የሴት ስደተኞች መጠለያ ጣብያ ዉስጥ ሳሉ የተነሳ ነዉ። በሊቢያ የስደተኞች መጠለያ ጣብያ እጅግ አስከፊና አደገኛ ነዉ። ከመጠለያዉ ያመለጡ አንዳንድ ሴቶች እንደተናገሩት በመጠለያ ጣብያዉ ከፍተኛ ጥቃትና የፆታ ብዝበዛ ይፈፀማል። ከዚህ ሌላ በመጠለያ ጣብያዉ ከፍተኛ የዉኃና የምግብ እጥረት አለ።
"ኪዩባ በለዉጥ ጉዳና"
«ኪዩባ በለዉጥ ጉዳና» የኒዮርክ ታይምስ ጋዜጣ ፎቶግራፍ አንሺ ቶማስ ሙኒታ ያነሳዉን ፎቶ የሰጠዉ ስያሜ ነዉ። ይህ ፎቶ የእለት ኑሮ በተሰኘዉ የሽልማት ዘርፍ አንደኛ ቦታን አግኝቶአል። ደመናማና ጭጋጋማ ሆኖ በዋለዉ ሕዳር 24፤ 2009 ዓ.ም ማለዳ ጠዋት የኪዮባ አብዮት ወጣት ወታደሮች ሃገሪቱን ሲዞር የነበረዉን የሟቹን የኪዩባ ፕሬዚዳንት ፊደል ካስትሮን አስክሪን መድረስ ሲጠባበቁ ይታያል። በሚቀጥለዉ ቀን የኪዩባዉ አብዮታዊ መሪ ፊደል ካስትሮ አስክሬናቸዉ ተቃጥሎ የኪዩባ ሁለተኛ ትልቅ ከተማ በሆነችዉ በሳንትያጎ ዴ ኪዩባ ዉስጥ ተቀብሯል።
የፖሊስ ጥቃት በሰሜናዊ ዳኮታ
በዚህ ፎቶ ላይ አንድ ሰዉ ፊት ሲታጠብ ይታያል። በሰሜናዊ ዳኮታ ኅዳር 2007 ዓ.ም የነዳጅ ዘይት ማስተላለፍያ መሰራትን በመቃወም በተጠራ የተቃዉሞ ሰልፍ ፖሊስ የሚለበልብ አስለቃሽ ጢስን በመጠቀም ጥቃት አድርሷል። በአባር ባራክማን የተቀረፀዉ ይህ ፎቶ ወቅታዊና ታሪካዊ ጉዳዮች በሚል የፎቶግራፍ ሽልማት ዘርፍ የመጀመርያ ቦታን አግኝቷል።
ለብቻ የተተዉት
አንዲት የ11 ዓመት ናይጀሪያዊት ልጃገረድ ከትንሽ ወንድሟ አጠገብ ሆና ታለቅሳለች። በሜዲተራንያን ባህር ሊቢያ ባህር ዳርቻ አቅራብያ ለረጅም ሰዓታት በአንድ የጎማ ጀልባ ላይ ሲቀዝፍ የበረዉ ይህ ጀልባ እዝያዉ ሊቢያ ባህር ዳርቻ በአንድ አዳኝ ቡድን ከመስመጥ ተርፈዋል። ይህ በሳንቲ ፓሲኦስ የተቀረፀ ፎቶ በአጠቃላይ የዜና ዘርፍ ሽልማት ረድፍ ሁለተኛ ደረጃን ይዟል።
ፈጣኑ ሰዉ
በዓለማችን ፈጣኑ ሰዉ ነዉ። ጃማይካዊዉ ኡሴን ቦልት በሪዮ ዴዤኔሮ በተካሄደዉ የኦሎምፒክ ጨዋታ ላይ በተወዳደረበት ሁሉ አሸንፎአል። በፎቶግራፉ ላይ እንደሚታየዉ ኡሴን ቦልት በ 100 ሜትር የግማሽ ማጣርያ ዉድድር ላይ ሳለ ለፎቶግራፍ አንሽዉ ለካይ ኦሊቨር ፈገግታዉን እያሳየ ነበር። ይህ ፎቶ ስፖርት በተሰኘዉ የሽልማት ዘርፍ የሦስተኛ ደረጃን አግኝቷል።
የተጨናነቀዉ እስር ቤት
ይህ የኖኤል ሴሊስ ፎቶ በፊሊፒን ኩየንዞን ከተማ ዉስጥ የሚገኘዉ እስር ቤት ምን ያህል አሳሳቢ ደረጃ ላይ መድረሱን ቁልጭ አድርጎ የሚያሳይ ነዉ። ለ 800 እስረኞች የታቀደዉ ይህ እስር ቤት 3800 ሰዎች ታስረዉበታል። የተጨናነቀዉን እስር ቤት የሚያሳየዉ ይህ ፎቶ ጠቅላላ ዜና በተሰኘዉ ፎቶ ሽልማት ዘርፍ ሦስተኛ ደረጃን አግኝቷል።
አድካሚዉ ጉዞ
ሁለት ወንዶች አንዲት ሴትን ወንዝ ያሻግራሉ። ይህ ፎቶ በበጎርጎረሳዉያኑ 2016 ዓ.ም መጋቢት ወር ስደተኞችን ለመከላከል መቂዶንያ ድንበር ላይ የተሰራዉን አጥር ተከትሎ ስደተኞች ሌላ አማራጭን በመፈለግ ወንዝን ሲሻገሩ የሚያሳይ ነዉ። ፎቶግራፍ አንሽዉ ቫዲም ጌሄርዳ ከግሪክ ወደ መቂዶንያ ያለዉን የስደተኞች አድካሚ ጉዞ በፎቶግራፉ ቀርጾ ወቅታዊ ክስተቶች በተሰኘዉ የፎቶ ሽልማት ዘርፍ ፎቶዉ ሁለተኛ ቦታን አግኝቷል።
ጦርነት በዩክሬይን
በቫለሪ ሜሊንኮቭ የተቀረፀዉ ይህ ፎቶ የዩክሪይኗ የገጠር መንደር ሉአንስካያ በአዉሮፕላን የቦንብ ድብደባ ከደረሰባት በኋላ ሲቪል ነዋሪዎች በእሳት ከጋየዉ መኖርያ ቤታቸዉ ሸሽተዉ ሲወጡ ያሳል። ይህን ፎቶ የሩስያዉ የመገናኛ ብዙኃን ኩባንያ «ሩስያ ሲቮድንያ» «የዩክሪይን ጥቁር ቀን» ሲል ሸልሞታአል።