1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

የሐምሌ 5 ቀን 2016 የዓለም ዜና

Yohannes Gebreegziabherሰኞ፣ ነሐሴ 6 2016

https://p.dw.com/p/4jM35

በትግራይ የፖለቲካ ልዩነቶች ወደ አለመረጋጋት እንዲያመሩ እንደማይፈቀድ ሌተናል ጀነራል ታደሰ ወረደ አስጠነቀቁ።

በትግራይ የፖለቲካ ልዩነቶች ወደ አለመረጋጋት እንዲያመሩ እንደማይፈቀድ የትግራይ ጊዚያዊ መስተዳድር ምክትል ፕረዚደንት ሌተናል ጀነራል ታደሰ ወረደ አስጠነቀቁ።
ጀነራሉ ከጥቂት ሰዓታት በፊት ለክልሉ መገናኛ ብዙሃን በሰጡት ጋዜጣዊ መግለጫ በፖለቲካዊ ልዩነት ምክንያት በትግራይ አለመረጋጋት እንዲፈጠር የሚያደርጉ እንቅስቃሴዎች የትግራይ ጸጥታ ሃይሎች እንደማይታገሱ አስጠንቅቀዋል።
ፖለቲካዊ ልዩነቶች በውይይት እንዲፈቱ እንደሚጠበቅ የገለጹት ጀነራል ታደሰ ወረደ ላልተወሰነ ጊዜ አንዱን በመደገፍም ይሁን በመቃወም ሰላማዊ ሰልፍ ማድረግ ለጊዜው እንደተከለከለ ገልጸዋል።
ህወሓት ከምርጫ ቦርድ ዕውቅና ውጭ ጉባኤ ለማካሄድ ዝግጅቶች እያደረገ እንደሆነ ለማወቅ ተችሏል። የህወሓት ሊቀመንበር ዶክተር ደብረፅዮን ገብረሚካኤል ዛሬ ለሀገር ውስጥ እና ውጭ መገናኛ ብዙሐን በሰጡት መግለጫ፥ ህወሓት በቅርቡ ጠቅላላ ጉባኤው እንደሚያካሂድ ተናግረዋል። ጉባኤው የሚደረግበት ቁርጥ ያለ ቀን ግን አላስቀመጡም። 
በአንጻሩ በተለያዩ የትግራይ አካባቢዎች የሚኖሩ በርካታ ጉባኤተኞች በህወሓት በውስጡና ከፌደራል መንግስት ጋር ያለውን አለመስማማት ዕልባት ሳያገኝ በጉባኤው አንሳተፍም እያሉ እንደሆነ ለማወቅ ተችሏል።

የትግራይ ተቃዋሚ ፓርቲዎች በአውሮጳ

የሁለት የትግራይ ተቃዋሚ ፓርቲ ከፍተኛ አመራሮች በተለያዩ የአውሮጳ ከተሞች ከትግራይ ማሕበረሰብ አባላት ጋር ተወያዩ። የዓረና ትግራይ ሊቀመንበር አቶ ዓምዶም ገብረስላሴና የባይቶና ሊቀመንበር አቶ ክብሮም በርሀ ቀደም ሲል በአምስተርዳም ከሚገኙ የትግራይ ማሕበረሰብ አባላትና ከሃገሪቱ የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ባለስልጣናት ጋር መወያየታቸውን ለዶይቼቨለ ተናግረዋል።
በትላንትናው ዕለትም በጀርመን ፍራንክፈርት ከተማ ከሚገኙ የትግራይ ማሕበረሰብ አባላት መወያየታቸውን የገለጹት አቶ ዓምዶም ገብረስላሴ በሕወሓት ካድሬዎች ስብሰባው እንዳይሳካ ጥረት ቢደረገም ውጤታማ ስብሰባ አከናውነናል ብለዋል።

የትግራይ የዳያስፖራ ማሕበረሰብ የሚያዘጋጁዋው መድረኮች በአንድ ፓርቲ ሥር የሚከናወኑ ስለነበር እንደዚህ አይነት ዕድሎች ማግኘት ከባድ እንደነበር የገለጹት የባይቶና ሊቀመንበር አቶ ክብሮም በርሀ በበኩላቸው መድረኮቹ አማራጭ ሐሳቦቻችንን ለማሕበረሰቡ ለማቅረብ ዕድል የፈጠሩ ነበር ብለዋል።

በአውሮጳና አሜሪካ የሚገኙ ማሕበረሰቡ የሚሰባሰብባቸውን ማሕበራት የሚመሩ ጥቂት መሪዎች ከገለልተኝነት ይልቅ የአንድ ፓርቲ አገልጋይ የመሆን ዝንባሌ እንደሚታይባቸው የወቀሱት ሁለቱም የተቃዋሚ ፓርቲ መሪዎች፤ በሰፊው የዳያስፖራ ማሕበረሰብ ዘንድ ግን ይህ ተቀባይነት እንደሌለው መገንዘባቸውን አክለዋል።
ሁለቱም የፓርቲው አመራር አባላት በሌሎች የአውሮጳ ከተሞች ተዘዋውረው ከትግራይ ተወላጆች ጋር ለመነጋገር ዕቅድ እንዳላቸውም አስረድተዋል።

የሱዳንና የአሜሪካ ምክክር ያለውጤት ተበተነ

በአሜሪካና በሱዳን የሉአላዊ ምክርቤት ሉኡካን በሳውዲ አረቢያ ሲካሄድ የነበረው የሰላም ምክክር ያለውጤት ተበተነ። በሁለቱም ወገን እነማን በድርድሩ እንደተሳተፉ ግን የተገለጸ ነገር የለም።
15 ወራትን ያስቆጠረው የሱዳን የእርስ በእርስ ጦርነት ለማብቃት በሚችልበት አጀንዳ ላይ ለመወያየት በጀነራል አልቡርሃን የሚመራው  የሱዳን ሉአላዊ ምክርቤት የልኡካን ቡድኑን ወደ ጅዳ ትላንት የገባ ሲሆን ይህን ምክክር ተንተርሶ የፊታችን ዕሮብ ሁለቱም ተፋላሚ ኃይሎችን ለማነጋገር ዕቅድ ተይዞ ነበር። ይሁንና ምክክሩ ያለውጤት መበተኑን ሮይተርስ ዘግቧል።
በሱዳን ሉአላዊ ምክርቤት ፕረዚደንት ጀነራል አልቡርሃን እና በፈጥኖ ደራሽ ሃይሎች አዛዣ ጀነራል ሐምዳን ዳጋሎ መካከል በሚካሄደው ጦርነት በሚልዮን የሚቆጠር ሰላማዊ ሕዝብ እንደተፈናቀለ አልያም አገር ጥሎ እንደተሰደደ፤ እንዲሁም በሺዎች የሚቆቸሩ ሱዳናውያን መሞት መቁሰላቸውን የተባበሩት መንግስታት ድርጅት ያወጣው ሪፖርት ያመላክታል።

እስራኤል በካንዩኑስ የሚገኙ ስደተተኞች አካባቢውን ለቀው እንዲወጡ አዘዘች

እስራኤል በደቡብ ጋዛ በካንዩኑስ የሚገኙ በአስር ሺዎች የሚቆጠሩ ተፈናቃዮች አካባቢውን ለቀው እንዲወጡ አሳሰበች። የእስራኤል ጦር፤ ተፈናቃዮቹ አካባቢውን ለቀው እንዲወጡ ያሳሰብኩት አካባቢው ሐማስ ለወታደራዊ ስምሪትና ሮኬቶችን ለማስወንጨፍ እየተጠቀመበት ስለሆነ ከእስራኤል ታንኮች በሚሰጠው አጸፋዊ ምላሽ ጉዳት እንዳይደርስባቸው ነው ብሏል።
ትላንት የእስራኤል የጦር ጀቶች በካንዩኑስ በሚገኘው ስደተኞች ይኖሩበት በነበረው ትምህርት ቤት ላይ በፈጸሙት ድብደባ ቢያንስ 90 ፍልስጤማውያን ተገድለዋል። ይህ በትምህርት ቤት ላይ የተፈጸመው ጥቃት ዓለምአቀፍ ውግዘት ቢያስከትልም እስራኤል ግን ጥቃቷን አጠናክራ ለመቀጠል ያስችላት ዘንድ ነዋሪዎች አካባቢውን ለቀው እንዲወጡ እያሳሰሰበች ነው ተብሏል።
ሮይተርስ የዜና ወኪል እንደዘገበው ወደእያንዳንዳቸው የነዋሪዎች ተንቀሳቃሽ ስልክ "ያለችሁበት ቦታ የጦርነት ቀጠና ስለሆነ  የሰብአዊነት ዞን ወደተባለው ስፍራ በአስቸኳይ ለቃችሁ ውጡ" የሚል የጽሑፍና የድምጽ መልእክት እንዲደርሳቸው እየተደረገ ነው።
በተባበሩት መንግስታት ድርጅት የፍልስጤም ስደተኞች መርጃ ድርጅት በበኩሉ "የጋዛ ነዋሪዎች ተከበዋል የትም መሄድ አይችሉም" ሲል ቅሬታውን ገልጿል።
የእስራኤል ሰራዊት በበኩሉ በአለፉት 24 ሰዓታት በአካባቢው 30 የሐማስ ወታደራዊ ዒላማዎች ባላቸው ላይ ጥቃት መሰንዘሩንና የተለያዩ ወታደራዊ መሰረተ ልማቶችን ማውደሙን ገልጿል።

ሒዝቦላህ በእስራኤል ላይ የድሮን ጥቃት መፈጸሙን

በኢራን ይደገፋል የሚባለው ሒዝቦላህ በእስራኤል ወታደራዊ የስልጠና ማዕከል ላይ የድሮን ጥቃት መፈጸሙን አስታወቀ። ጥቃቱ በእስራኤል ለተገደለው አባላቸው የበቀል አጸፋዊ እርምጃ መሆኑንንም ገልጿል።
ሒዝቦላህ በመግለጫው በሰሜን እስራኤል የሚገኘውን የማሐቫ ወታደራዊ ማሰልጠኛ ተቋም ላይ የድሮን መንጋዎችን ተጠቅሞ ጥቃት እንደፈጸመና በሰው ላይ ጉዳት ማድረሳቸውን ማረጋገጡን አክሏል።
ጥቃቱም እስራኤል በሊባኖስ የሲዶን ከተማ ለገደለችው የሐማስ አባል ሳማር አል ሐጂ የበቀል አጸፋዊ ምልሽ ነው ብሏል።
የእስራኤል ሰራዊት በበኩሉ ከሊባኖስ የተሰማሩ ድሮኖች በእስራኤል የድንበር አካባቢ ሰማይ ላይ ማንዣበባቸውን ከነዚህም አንዷን መትቶ መጣሉንና ሌሎቹም መከስከሳቸውን ገልጿል። ሌሎቹ እንዴት እንደተከሰከሱ መግለጫው ባይጠቅስም ድሮኖቹ በሰው ሕይወት ያደረሱት ጉዳት የለም ሌላ ምንነቱ ያልተጠቀሰ ጉዳት ግን አድርሷል ማለቱን የዘገበው የጀርመን ዜና አገልግሎት (DPA) ነው።

ዩክሬይን በሺዎች የሚቆጠር ጦሯን የሩስያ ግዛት ወደሆነችው ኩርስክ ዞን ማሰማራቷን አስታወቀች።

ዩክሬይን በሺዎች የሚቆጠር ጦሯን የሩስያ ግዛት ወደሆነችው ኩርስክ ዞን ማሰማራቷን አስታወቀች። ይህን ያደረገችው የሩስያ ጦር የማጥቃት አቅሙን ለማዳከምና ወታደራዊ ይዞታዋን ለማስፋት እንደሆነ አስታውቃለች።
አንድ ስማቸውን ያልተጠቀሰው የዩክሬይን ባለስልጣን ለአዣንስ ፍራንስ ፕረስ "የወታደራዊ ዘመቻው አላማ "ጠላት" ያሏትን የሩስያ ወታደራዊ ይዞታን በመያዝ የማጥቃት አቅሟን ለማዳከም ጥቃት እየፈጸምን ነው" ብሏል።
ለብዙ ጊዚያት ስለወታደራዊ ዘመቻው ሳይናገሩ የቆዩት የዩክሬይን ፕሬዚደንት ቭሎደሚር ዘለንስኪ "ዩክሬይን ጦርነቱን ወደ ወራሪዋ ሩስያ ድንበር እየገችፋው ነው" ሲሉ ተደምጧል።
ሩስያ በበኩሏ ወደ 1,000 የሚሆኑ የዩክሬይን ወታደሮች ድንበር ጥሰው ወረራ መፈጸማቸውን አስታውቃለች።
አንድ ሌላ የዩክሬይን ባለስልጣን በበኩላቸው ሐገራቸው ሩስያን የመውረር ፍላጎት እንደሌላትና ዓለምአቀፍ ሕጎችን እንደምታከብር ገልጸዋል።
ባለስልጣኑ ዩክሬይን የሩስያን ድንበር ጥሳ ጥቃት መፈጸሟ የሰራዊቱና የሕዝቡን ሞራል ከፍ እንዳደረገውና ይህ ወታደራዊ ዘመቻ እያጠቃን ወደፊት የመገስገስ አቅም እንዳለን ማሳያ ነው ብሏል።
ዩክሬይ ካለፈው ማክሰኞ ጀምሮ የሩስያን ድንበር ጥሳ በመግባት በኩርስክ ዞን የሚገኙ አካባቢዎችን መቆጣጠሯን ይታወቃል። ይህን ወታደራዊ ስምሪትን ተከትሎ ሩስያ ተጠባባቂ ጦሯን ለመጥራት ተገዳለች።
የዩክሬይን ፕሬዚደንት ዘለንስኪ ሰሞኑን የአሜሪካ የተራቀቁ F16 የተባሉ ተዋጊ ጀቶች በእጃቸው መግባታቸውንና ይህም የመከላከልና የማጥቃት አቅማቸውን እንደሚያጠናክር መግለጻቸውን ይታወሳል።

ዮሃንስ ገብረእግዚአብሄር

ልደት አበበ
 

 

ቀጣዩን ክፍል ዝለለዉ ስለዚሕ ዝግጅት

ስለዚሕ ዝግጅት

PODC-DW-Amharisch-News-DWcom

የዓለም ዜና

ዶይቼ ቬለ የዕለቱን ዋና ዋና የዜና ትንታኔዎች ከኢትዮጵያ እና ከመላው ዓለም በየቀኑ ያቀርባል። የኢትዮጵያ እና የአፍሪካ ፖለቲካዊ እና ኤኮኖሚያዊ ጉዳዮችን ጨምሮ የመላው ዓለምን ውሎ የተመለከቱ ጠቃሚ መረጃዎች በሰባቱም የሣምንቱ ቀናት ከምሽቱ አንድ ሰዓት ከዶይቼ ቬለ ያድምጡ።