1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

የጥቅምት 25 ቀን 2016 የዓለም ዜና

Eshete Bekeleእሑድ፣ ጥቅምት 25 2016

https://p.dw.com/p/4YQZv

በሶማሌ ክልል በደረሰ የጎርፍ አደጋ የ20 ሰዎች ሕይወት ማለፉን የክልሉ መንግሥት አስታወቀ 

በሶማሌ ክልል በደረሰ የጎርፍ አደጋ የ20 ሰዎች ሕይወት ማለፉን የክልሉ መንግሥት አስታወቀ። በአደጋው ከ12 ሺሕ በላይ አባወራዎች መፈናቀላቸውን በሶማሌ ክልል አደጋ ሥጋት ሥራ አመራር ቢሮ የቅድመ-ማስጠንቀቂያ አስተባባሪ በሺር አረፕ መናገራቸውን የክልሉ ኮምዩንኬሽን ቢሮ ትላንት ቅዳሜ ባወጣው መግለጫ አስታውቋል። በመግለጫው መሠረት በሶማሌ ክልል እየጣለ የሚገኘው ከባድ ዝናብ ያስከተለው ጎርፍ በእንስሳት ሐብት፣ በሰብል እና በንብረት ላይ ጉዳት አድርሷል። 

ከሶማሌ ክልል በተጨማሪ በኦሮሚያ ክልል የሚገኙት የጉጂ እና ቦረና አካባቢዎች እንዲሁም የደቡብ ኢትዮጵያ እና የደቡብ ምዕራብ የአገሪቱ ክፍሎች እስከ 350 ሚሊ ሜትር የደረሰ ዝናብ ባለፈው ወር እንደነበር የኢትዮጵያ ሜትሮሎጂ ኢንስቲትዩት አስታውቋል። 

እየጣለ በሚገኘው የበጋ ዝናብ ሳቢያ በደቡብ ኦሞ ዞን የሚገኘው የዳሰነች ወንዝ ሞልቶ ከ60 ሺሕ በላይ ሰዎች ማፈናቀሉን የአካባቢው ባለሥልጣናት አስታውቀዋል። ከባድ ዝናብ ጎርፍ ያስከተለባቸው አካባቢዎች ባለፉት ዓመታት ከፍተኛ ድርቅ የተጫናቸው ነበሩ። 

ዶክተር ጥላሁን እስማኤል የኢትዮጵያ ሴኪዩሪቲስ ኤክስቼንጅ ዋና ሥራ አስፈጻሚ ሆነው ተሾሙ 

በተያዘው ዓመት ሥራ ይጀምራል ተብሎ የሚጠበቀው የኢትዮጵያ ሴኪዩሪቲስ ኤክስቼንጅ ዋና ሥራ አስፈጻሚ ተሾመለት። የካፒታል ገበያውን ምሥረታ ሲያስተባብሩ የቆዩት ዶክተር ጥላሁን እስማኤል ዋና ሥራ አስፈጻሚ ሆነው ተሾመዋል። 

በዓለም አቀፉ የገንዘብ ድርጅት ከፍተኛ ኤኮኖሚስት ሆነው ያገለገሉት የባንክ ባለሙያው ሕላዌ ታደሰ በሊቀ-መንበርነት የሚመሩት የኢትዮጵያ ሴኪዩሪቲስ ኤክስቼንጅ ሥራ አስፈጻሚ ቦርድ የዶክተር ጥላሁንን ሹመት ትላንት ቅዳሜ አጽድቋል። 

ዶክተር ጥላሁን በዓለም ባንክ ሥር በሚገኘው ዓለም አቀፉ የፋይናንስ ኮርፖሬሽን (IFC) ከስድስት ዓመታት በላይ ሠርተዋል። የሕግ ምሩቅ የሆኑት ጥላሁን በጀርመኗ ሙኒክ ከተማ በሚገኘው ማክስ ፕላንክ ኢንስቲትዩት በተመራማሪነት፣ በአዲስ አበባ እና ሐረማያ ዩኒቨርሲቲዎች በመምህርነት ሠርተዋል። 

ዶክተር ጥላሁን በዋና ሥራ አስፈጻሚነት እንዲመሩት የተሾሙበት ካፒታል ገበያ በመንግሥት እና የግሉ ዘርፍ ሽርክና የሚቋቋም ነው። መንግሥት በኢትዮጵያ ኢንቨስትመንት ሆልዲንግስ በኩል 25 በመቶ ድርሻ ሲኖረው የተቀረው ለግሉ ዘርፍ የሚሸጥ ነው። የአክሲዮን ሽያጩ ባለፈው ግንቦት 2015 በይፋ ተጀምሯል።

የጋና ገዢ ፓርቲ በመጪው ፕሬዝዳንታዊ ምርጫ የሚያቀርባቸውን እጩ መረጠ 

በጋና ሥልጣን ላይ የሚገኘው አዲስ የአርበኞች ፓርቲ (NPP) ምክትል ፕሬዝደንት ሆነው በመሥራት ላይ የሚገኙት ማሐሙዱ ባዉሚያ በሚቀጥለው ዓመት ለሚካሔደው ምርጫ እጩ አድርጎ መረጠ። የገዢው ፓርቲ እጩ ሆነው የተመረጡት የ60 ዓመቱ ኤኮኖሚስት ከዚህ ቀደም የጋና ብሔራዊ ባንክ ገዥ ሆነው ሰርተዋል። 

ባዉሚያ የጋና ሕገ መንግሥት በሚፈቅደው መሠረት ለስምንት ዓመታት በፕሬዝደንትነት ሰርተው ከአንድ ዓመት ገደማ በኋላ ሥልጣን የሚለቁት የፕሬዝደንት ናና አኩፎ አዶ ምክትል ናቸው። 

ምክትል ፕሬዝደንቱ ገዢው ፓርቲ እጩውን ለመምረጥ ባካሔደው የመጀመሪያ ዙር ምርጫ ቀዳሚ ሆነው ሲያጠናቅቁ በሁለተኛው ዙር 61 በመቶ ድምጽ አግኝተዋል። ውጤቱ ይፋ ከተደረገ በኋላ ባሰሙት ንግግር ፕሬዝደንት ሆነው ቢመረጡ ቀውስ የበረታበትን የጋና ምጣኔ ሐብት መልሰው ለመገንባት ቃል ገብተዋል።  በነዳጅ ዘይት እና በካካዋ ምርቷ የምትታወቀው ጋና ከገጠማት ኤኮኖሚ ቀውስ ለማገገም ከዓለም አቀፉ የገንዘብ ድርጅት 3 ቢሊዮን ዶላር ለመበደር ተገዳለች። 

የፍልስጤም ፕሬዝደንት እስራኤል ለተኩስ አቁም እንድትስማማ አሜሪካ ግፊት እንድታደርግ ጠየቁ

በእስራኤል እና በሐማስ መካከል “አስቸኳይ የተኩስ አቁም” እንዲደረግ የፍልስጤም ፕሬዝደንት መሐመድ አባስ ለአሜሪካው ውጭ ጉዳይ ሚኒስትር አንቶኒ ብሊንከን ጥያቄ አቀረቡ። አባስ ጥያቄውን ያቀረቡት ውጭ ጉዳይ ሚኒስትሩ በእስራኤል ቁጥጥር ሥር በሚገኘው ዌስት ባንክ ዛሬ እሁድ ድንገተኛ ጉብኝት ባደረጉበት ወቅት ነው።

አባስ እስራኤል ትፈጽማቸዋለች ያሏቸውን ወንጀሎች አሜሪካ በአፋጣኝ እንድታስቆም ለብሊንከን ጥሪ ማቅረባቸውን ሬውተርስ ዘግቧል። ከአንድ ሰዓት ያነሰ ጊዜ በወሰደው ስብሰባ አባስ “የፍልስጤም ሕዝባችን በጋዛ ዓለም አቀፍ ሕግጋት ተጥሰው በእስራኤል እየደረሰበት ያለውን የዘር ማጥፋት ጦርነት የሚገልጹ ቃላት የሉም” ሲሉ ለአሜሪካው ውጭ ጉዳይ ሚኒስትር መናገራቸውን የፍልስጤም ዜና አገልግሎት ዘግቧል። 

አባስ እና ብሊንከን ስብሰባቸው ከተጠናቀቀ በኋላ የጋራ መግለጫ እንኳ ሳይሰጡ ቀርተዋል። የቃጣር፣፣ ሳዑዲ አረቢያ፣ ዮርዳኖስ እና የተባበሩት አረብ ኤሚሬቶች የውጭ ጉዳይ ሚኒስትሮች ትላንት ቅዳሜ ከብሊንከን ተገናኝተው እስራኤል የተኩስ አቁም ለማድረግ እንድትስማማ ግፊት እንዲያደርጉ ተመሳሳይ ጥያቄ አቅርበው ነበር። ብሊንከን ግን የተኩስ አቁም ሐማስ እንደገና ተደራጅቶ ጥቃት እንዲፈጽም ያስችለዋል በሚል ሐሳቡን ውድቅ አድርገዋል።  እስራኤል የምትወስደው ወታደራዊ እርምጃ በሰላማዊ ሰዎች ላይ ሳይሆን በሐማስ ላይ ብቻ ያነጣጠረ እንደሆነ ገልጻለች። የፍልስጤም እስላማቂ ታጣቂዎች ሰላማዊ ሰዎችን እንደከለላ ይጠቀማሉ ስትል እስራኤል ትከሳለች። 

በመጪው ሰኞ አንድ ወር የሚሞላው የእስራኤል እና የሐማስ ጦርነት ከተቀሰቀሰ ወዲህ በጋዛ ሰርጥ በትንሹ 9 ሺሕ 770 ሰዎች መገደላቸውን የጋዛ የጤና ሚኒስቴር አስታውቋል። ከሟቾቹ መካከል ቢያንስ 4,800 ሕጻናት እንደሚገኙበት ሐማስ የሚያስተዳድረው የጋዛ የጤና ሚኒስቴር ዛሬ እሁድ ገልጿል። ሐማስ መስከረም 26 ቀን 2016 በፈጸመው ጥቃት 1 ሺሕ 400 ሰዎች መገደላቸውን የእስራኤል ባለሥልጣናት አስታውቀዋል። 

የሐምቡርግ አውሮፕላን ማረፊያን ለአስራ ስምንት ሰዓታት ከሥራ ውጪ ያደረገው የአጋች ታጋች ድራማ አበቃ 

የሐምቡርግ አውሮፕላን ማረፊያን ላለፉት አስራ ስምንት ሰዓታት ከሥራ ውጪ ያደረገው የአጋች ታጋች ድራማ ማብቃቱን ፖሊስ አስታወቀ። በማሳደግ መብት ውዝግብ ምክንያት የገዛ ልጁን አገተ የተባለው የ35 ዓመት ጎልማሳ “ያለ ተቃውሞ” እጅ ሰጥቶ በቁጥጥር ሥር ውሏል። ፖሊስ ታግታ የቆየችው ልጅ ጉዳት እንዳልደረሰባት አስታውቋል። 

ተጠርጣሪው መኪናውን እያሽከረከረ ወደ ሐምቡርግ አውሮፕላን ማረፊያ የገባው ትላንት ቅዳሜ ከምሽቱ አንድ ሰዓት ገደማ ነበር። ተሽከርካሪውን ከቱርክ አየር መንገድ አውሮፕላን ሥር ያቆመው ተጠርጣሪ ሁለት ጊዜ ወደ ሰማይ መተኮሱን ተቀጣጣይ ጠርሙሶች ከተሽከርካሪው አውጥቶ መወርወሩን ፖሊስ አስታውቋል። 

የጀርመን ባለሥልጣናት ጉዳዩ ከማሳደግ መብት ውዝግብ ጋር የተያያዘ እንደሆነ ያምናሉ። በልጅቷ አስተዳደግ ረገድ በተሰጠ ውሳኔ ያልተስማማው ተጠርጣሪ ወደ ቱርክ ይዞ ለመሔድ ፍላጎት እንደነበረው የሐምቡርግ ፖሊስ ቃል አቀባይ ተናግረዋል።

ለአስራ ስምንት ሰዓት በዘለቀው የአጋች ታጋች ድራማ የሐምቡርግ አውሮፕላን ማረፊያ አገልግሎት መስጠት አቁሞ ቆይቷል። በዚህም ምክንያት ከ100 በላይ በረራዎች ሲሰረዙ በርካቶች አቅጣጫቸውን እንዲቀይሩ ተደርጓል።  

ተጠርጣሪው በቁጥጥር ሥር ውሎ ድራማው ሲያበቃ በኩነቱ አንድም ሰው እንዳልተጎዳ የሐምቡርግ ከተማ ከንቲባ ገልጸዋል። አውሮፕላን ማረፊያው በፍጥነት ሥራ ለማስጀመር ዝግጅት እየተደረገ እንደሚገኝ ፖሊስ አስታውቋል።

ቀጣዩን ክፍል ዝለለዉ ስለዚሕ ዝግጅት

ስለዚሕ ዝግጅት

PODC-DW-Amharisch-News-DWcom

የዓለም ዜና

ዶይቼ ቬለ የዕለቱን ዋና ዋና የዜና ትንታኔዎች ከኢትዮጵያ እና ከመላው ዓለም በየቀኑ ያቀርባል። የኢትዮጵያ እና የአፍሪካ ፖለቲካዊ እና ኤኮኖሚያዊ ጉዳዮችን ጨምሮ የመላው ዓለምን ውሎ የተመለከቱ ጠቃሚ መረጃዎች በሰባቱም የሣምንቱ ቀናት ከምሽቱ አንድ ሰዓት ከዶይቼ ቬለ ያድምጡ።