1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

የረቡዕ ሐምሌ 10 ቀን፤ 2016 ዓ.ም የዓለም ዜና

ረቡዕ፣ ሐምሌ 10 2016

https://p.dw.com/p/4iR1G

አርዕስተ ዜና

*ሕዝባዊ ወያኔ ሓርነት ትግራይ (ሕወሓት)በ50 ዓመት ታሪኩ አጋጥሞት በማያውቅ ፈተና ውስጥ እንዳለ ዐሳወቀ ። ሕወሓት በከፍተኛ አመራሩ ለ11 ቀናት ያደረገውን ስብሰባ ካጠናቀቀ በኋላ ትናንት ባሰራጨው መግለጫ፦ ቡድናዊነት፣ ፀረ ዴሞክራሲ አመለካከቶች እና ሕዝበኝነት ፈተናዎቹ እንደሆኑ አመልክቷል ።

*መዓከላዊ ሶማሊያ ውስጥ ታጣቂዎች ባደረሱት ጥቃት ቢያንስ አምስት ሰዎች ተገደሉ ።  የአካባቢ ተወላጅ ታጣቂዎቹ የተሽከርካሪ አጀብ ላይ በሰነዘሩት ድንገተኛ ጥቃት ከባድ ጦር መሣሪያዎችን ጭምር ማርከዋል ።

*የዩናይትድ ስቴትስ ፕሬዝዳንት ጆ ባይደን ለፕሬዚዳንታዊ ምርጫ እጩ መሆን አለመሆናቸውን ለመወሰን ፓርቲያቸው ድምፅ እንደሚሰጥ ይፋ አደረገ ።

ዜናው በዝርዝር

መቐሌ፥ ሕወሓት በ50 ዓመት ታሪኩ ብርቱው ፈተና ውስጥ እንዳለ ዐሳወቀ

ሕዝባዊ ወያኔ ሓርነት ትግራይ (ሕወሓት)በ50 ዓመት ታሪኩ አጋጥሞት በማያውቅ ፈተና ውስጥ እንዳለ ዐሳወቀ ። ሕወሓት በከፍተኛ አመራሩ ለ11 ቀናት ያደረገውን ስብሰባ ካጠናቀቀ በኋላ ትናንት ባሰራጨው መግለጫ፦ ቡድናዊነት፣ ፀረ ዴሞክራሲ አመለካከቶች እና ሕዝበኝነት ፈተናዎቹ እንደሆኑ አመልክቷል ። ሕወሓት በመግለጫው በ50 ዓመት ታሪኩ እንደ አሁኑ ዓይነት ፈተና ገጥሞት እንደማያውቅ ጠቁሟል ። እነዚህ የተባሉት ፈተናዎች ፓርቲው በሚገባው ደረጃ እንዳይንቀሳቀስ እንዳደረጉ እና ወደ መፍረስ አደጋም ሲመሩ የነበሩ መሆናቸውን አውስቷል ። በዓመቱ በተደጋጋሚ ረዥም ስብሰባዎች ተጠምዶ የቆየው ሕወሓት በትናንቱ መግለጫውም ወደ ሌላ ስብሰባ ወይም ጉባኤ ለማምራት ዝግጅት ላይ መሆኑን ገልጧል ። በተያዘው ሐምሌ ወር ውስጥም 14ኛ መደበኛ ጉባኤውን ለማድረግ ውሳኔ ማስተላለፉም ዐሳውቋል ። አስተያየታቸውን ለዶይቸ ቬለ ከሰጡ ነዋሪዎች መካከል አንዱ እንዲህ ብለዋል ።

«ዓመቱን ሙሉ ስብሰባ ውስጥ  ነበር እና አሁንም ጭራሽ ሌላ ስብሰባ በዓመት ወደ ሁለት መቶ ምናምን ቀን ስብሰባ ውስጥ ነበሩ ። እና ሥራቸው ምንድን ነው? ሥራቸው ስብሰባ ነው እስከሚባል ድረስ ነው የደረሱት ። አሁን ያለኝ ግንዛቤ፦ ሕዝብን ማገልገል የሚፈልጉ ሳይሆን የግላቸውን ሥልጣን ለማራዘም  እንዴት ሕዝቡን እየጎዱ፣ ሕዝብን እያስቸገሩ እንዴት መቆየት እንዳለባቸው እየሠሩ ነው ያሉት ብዬ የማስበው ። »

በዚህ ጉዳይ ከሕወሓት ተጨማሪ ማብራሪያ ለማግኘት የመቐሌው ወኪላችን ሚሊዮን ኃይለ ሥላሴ ያደረገው ጥረት አልሰመረም ። ተጨማሪ ዘገባ በዜና መጽሄት ይኖረናል ።

4 ኢትዮጵያውያንን ጨምሮ 9 ሰዎች አንድ የኬንያ የወርቅ ማውጫ ተደርምሶባቸው ሞቱ 

ኬንያና ኢትዮጵያ ድንበር ላይ የሚገኝ አንድ የወርቅ ማውጫ ተደርምሶ ስራ ላይ ከነበሩት ሰዎች ኢትዮጵያውያንን ጨምሮ ቢያንስ አምስቱ ሞቱ። ሌሎች ቁጥራቸው ያልተገለፀ ሰዎችም ቆሰሉ። ሂሎ የተባለው የወርቅ ማውጫ በአካባቢው ነዋሪዎች መካከል በቦታው የይገባኛል ጥያቄ በተነሳ ግጭት ሰበብ የሰዎች ሕይወት ከጠፋ በኋላ ስፍራው ባለፈው መጋቢት ወር ቢዘጋም ማዕድን ቆፋሪዎች ወርቅ ፍለጋውን ቀጥለው ነበር።  ባለፈው ሰኞ ምሽት አንድ ሺህ የሚሆኑ ሰዎች አካባቢውን በኃይል በመውረር በተከለከለው ስፍራ ቁፋሮ ማካሄዳቸውን  አንድ የአካባቢው ከፍተኛ ባለሥልጣን ተናግረዋል። ቁጥራቸው ከፀጥታ ኃይሎች የሚበልጠው እነዚሁ ሰዎች የሚቆፍሩበት ስፍራ ተደርምሶ ቢያንስ አምስት ሰዎች በአፈሩ ውስጥ ተቀብረዋል።  አንድ የአካባቢው አዛውንት ከስፍራው 9 አስክሬኖች ሲወጡ ማየታቸውን ተናግረዋል። ከ9ኙ አምስቱ ኬንያውያን አራቱ ደግሞ ኢትዮጵያውያን መሆናቸውን ተናግረዋል። ባለፈው ግንቦት ወርም በሂሎ  የወርቅ ማውጫ በተመሳሳይ ሁኔታ አምስት ሰዎች ሕይወታቸው አልፏል ።

ሞቃዲሾ፥ሶማሊያ ውስጥ ታጣቂዎች የተሽከርካሪ አጀብ አጠቁ

ማዕከላዊ ሶማሊያ ውስጥ ታጣቂዎች ባደረሱት ጥቃት ቢያንስ አምስት ሰዎች ተገደሉ ።  ታጣቂዎቹ የተሽከርካሪ አጀብ ላይ በሰነዘሩት ድንገተኛ ጥቃት ከባድ ጦር መሣሪያዎችን ማርከዋል ። የተሽከርካሪው አጀብ በፀጥታ ኃይላት አጀብ ሰኞ ዕለት አቡድዋቅ የተባለችው ከተማ ውስጥ ነው ድንገተኛ ጥቃት የደረሰበት ። በርካታ የአካባቢው ተወላጅ የሆኑ ታጣቂዎች  ከፀጥታ ኃይላቱ አይለው ከባድ ጦር መሣሪያውን መውረሳቸውን አራት የዐይን ምስክሮች ለሮይተርስ የዜና ምንጭ ተናግረዋል ። ከባድ አውቶማቲክ ጦር መሣሪያዎቹ፤ ጸረ-አየር መቃወሚያዎቹ እንዲሁም ባዙቃዎቹ ምንጫቸው ከኢትዮጵያ ነው ሲሉም የዐይን እማኞቹ አክለው መናገራቸውን የዜና ምንጩ ዘግቧል ።  ሶማሊያ ላይ የተጣለው የጦር መሣሪያ ማእቀብ ከዐሥርተ ዓመታት ወዲህ የተነሳው ከሰባት ወራት በፊት ነበር ።

ቤርሊን፥ በጀርመን የአውሮፕላን ማረፊያዎች የተጠናከረ የፀጥታ ጥበቃ ተግባራዊ ሊሆን ነው

የጀርመን ካቢኔ በአውሮፕላን ማረፊያዎች የፀጥታ ጥበቃን ጥብቅ ለማድረግ ዛሬ ወሰነ። ካቢኔው ይህን ውሳኔ ያሳለፈው ጽንፈኛ የአካባቢ ጥበቃ ተሟጋቾችና ሌሎች በአውሮፕላን ማረፊያዎች ውስጥ አደገኛ ርምጃዎችን እንዳይወስዱ ለመከላከል ነው። የጀርመን የመጓጓዣሚኒስትር ፎልከር ቪሲንግ፦ ሕጉ መጥበቁ በአውሮፕላን ማረፊያዎች የአክቲቪስቶችን እንቅስቃሴ ለማስቆምና ብዙ ሰዎች በሚጓዙበት በዚህ ወቅት ላይ ጉዞ እንዳይሰተጓጎል  ያደርጋል የሚል ተስፋ እንዳላቸው ተናግረዋል። የታቀደው የሕግ ማሻሻያ ስራ ላይ እንዲውል የጀርመን የህዝብ እንደራሴዎች ምክር ቤት ወይም ቡንደስታግ መስማማት አለበት ። በህጉ መሠረት ለአብነት ያህል፦ የሽቦ አጥሮችን የሚቆርጥ እና ከዚያም የአውሮፕላን ማረፊያና መንደርደሪያዎችን የሚዘጋ ማንኛውም ሰው ወደፊት እስከ ሁለት ዓመት የሚደርስ እሥራት ወይም የገንዘብ ቅጣት ይጠብቀዋል። ድርጊቱን የፈጸመ ብቻ ሳይሆን የሞከረም እንዲሁ ይቀጣል። ከዚህ ቀደም በዚህ ጥፋት ተጠያቂ የሚባሉ በገንዘብ ብቻ ነበር የሚቀጡት። የአካባቢ ጥበቃ ተሟጋቾች ጥቂት ለማይባሉ ጊዜያት ይህን ያልተፈቀደ ርምጃ በሙይንሽን እና ቤርሊንን ጨምሮ በሌሎች የጀርመን አየር ማረፊያዎች ውስጥ ወስደዋል።

ዋሽንግቶን፥የዶናልድ ትራምፕ የጥበቃ ሁኔታ ላይ ምርመራ መከፈቱ ተገለጠ

የዩናይትድ ስቴትስ የቀድሞው ፕሬዚደንት ዶናልድ ትራምፕ ላይ የግድያ ሙከራ ሲፈጸም የነበረው የጥበቃ ሁኔታ ላይ ምርመራ መከፈቱ ተገለጠ ። የዩናይትድ ስቴትስ የሀገር ውስጥ ደሕንነት ጽ/ቤት ዋና መርማሪ ምርመራው መከፈቱን ዛሬ ዐሳውቀዋል ። ምርመራው፦ ፔንሲልቫኒያ ከተማ ውስጥ ዶናልድ ትራምፕ የምርጫ ቅስቀሳ ንግግር በሚያሰሙበት ወቅት የግድያ ሙከራ ያደረገው ወጣትን በተመለከተ በጥበቃዎች የነበረው አጸፌታ ላይ ያተኩራል ተብሏል ። ቶማስ ማቲው ኩሩክስ የተባለው የ20 ዓመት ወጣት ተኳሽ ዶናልድ ትራምፕ ከነበሩበት መድረክ 135 ሜትር ርቀት ላይ  ሆኖ ተኩስ መክፈት መቻሉ እጅግ አነጋግሯል ። የዩናይትድ የቀድሞ አቃቤ ሕግ፤ ፈቃዳቸው የተነጠቀው ጠበቃ ሩዲ ጊዩሊያኒ የጥበቃ አካላቱ ብቃት ላይ ጥያቄ አንስተው አጣጥለዋል ።

«የጥበቃ አካላት አጸፌታ መመለሳቸው የተለመደ ነው ። የዩናይትድ ስቴትስ አቃቤ ሕግ በነበርሁበት ወቅት በሰዎች ጥቆማ ከበርካታ ሰዎች መካከል የጥበቃ አካላት የተጠቆመውን ሰው ጨፍድደው ይዘው በቁጥጥር ስር ሲያውሉ  ዐውቃለሁ ። ያ ግን  ወዲያው አጸፋ የሚመልሱ ብቃት ያላቸው

በቅዳሜው ጥቃት አንድ በአካባቢው የነበረ ታዳሚ ሲገደል ሌሎች ሁለት ሰዎች ደግሞ በጽኑእ መቁሰላቸው ይታወቃል።  የቀድሞው ፕሬዚደንት  የቀኝ ጆሮዋቸው ውጫዊ ክፍል በጥይት ተበስቶ ለደረሰባቸው ቀላል ጉዳት  ወዲያውኑ ህክምና አግኝተው ወደ ሥራቸው ተመልሰዋል ።  ጥቃቱ ከመድረሱ ቀደም ብሎ ዶናልድ ትራምፕ ላይ ከኢራን በኩል የግድያ ሙከራ ሊፈጸም ይችላል በሚል ሥጋት ጥበቃው ተጠናክሮ ነበር ። የቅዳሜው የግድያ ሙከራ እና ከኢራን በኩል የነበረው ሥጋት ግንኙነት ይኑረው አይኑረው ዐይታወቅም ። 7,800 አባላት ያሉት የዩናይትድ ስቴትስ ደህንነት(ሴክሬት ሠርቪስ)ለፕሬዚደንቶች፤ ምክትል ፕሬዚደንቶች፤ ቤተሰቦቻቸው፤ ለቀድሞ ፕሬዚደንቶች የትዳር አጋሮቻቸው እና ከ16 ዓመት በታች ለሆኑ ልጆቻቸው ጥበቃ የማድረግ ኃላፊነት አለባቸው ።

ኒውዮርክ፦ጆ ባይደን ለፕሬዚዳንታዊ ምርጫ እጩ ስለመሆናቸው ድምፅ ሊሰጥ ነው

የዩናይትድ ስቴትስ ፕሬዝዳንት ጆ ባይደን ለፕሬዚዳንታዊ ምርጫ እጩ መሆን አለመሆናቸውን ለመወሰን ፓርቲያቸው ድምፅ እንደሚሰጥ ይፋ አደረገ ። የዴሞክራቲክ ፓርቲ ሥራ አስፈፃሚ ኮሚቴ በነሐሴ ወር መጀመሪያ ላይ ጆ ባይደን በእርግጥም ፓርቲውን ወክለው ለፕሬዚዳንታዊ ምርጫ እጩ ስለመሆናቸው ለማወቅ በበይነመረብ ድምፅ ለመስጠት ወስኗል ።  የፓርቲው አመራር የፕሬዚደንታዊ ምርጫ በጥቅምት 26 ቀን፣ 2017 ዓ.ም በመላ ዩናይትድ ስቴትስ ሲከናወን  ጆ ባይደንት በሁሉም የሀገሪቱ ክፍል በሚገኙ የድምጽ መስጫ ወረቀቶች ላይ መኖራቸውን ማረጋገጥ እንደሚፈልጉ አስረድተዋል ። እርጅና ተጫጭኗቸው የመዘንጋት ችግር የገጠማቸው የ81 ዓመቱ አዛውንት ፕሬዚደንት ጆ ባይደን የአእምሮ ብቃት ላይ አንዳንድ የፓርቲው አባላት ጥርጣሬ እንዳላቸው ይፋ አድርገዋል ። ፕሬዚደንቱ ከእጩ ፕሬዚደንት ተወዳዳሪነታቸው ራሳቸውን እንዲያገሉም ጫና በማሳደር ላይ ናቸው ። ይህ በእንዲህ እንዳለ ከሰሞኑ የግድያ ሙከራ የተቃጣባቸው ዶናልድ ትራምፕ የሪፐብሊካኖች እጩ ሆነው መቅረባቸው ይታወቃል ።

ቀጣዩን ክፍል ዝለለዉ ስለዚሕ ዝግጅት

ስለዚሕ ዝግጅት

PODC-DW-Amharisch-News-DWcom

የዓለም ዜና

ዶይቼ ቬለ የዕለቱን ዋና ዋና የዜና ትንታኔዎች ከኢትዮጵያ እና ከመላው ዓለም በየቀኑ ያቀርባል። የኢትዮጵያ እና የአፍሪካ ፖለቲካዊ እና ኤኮኖሚያዊ ጉዳዮችን ጨምሮ የመላው ዓለምን ውሎ የተመለከቱ ጠቃሚ መረጃዎች በሰባቱም የሣምንቱ ቀናት ከምሽቱ አንድ ሰዓት ከዶይቼ ቬለ ያድምጡ።