1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

የዓለማቀፉ ቀይ መስቀል ማህበር ኮሚቴ እርዳታ በሰሜን ኢትዮጵያ

ሐሙስ፣ ግንቦት 11 2014

የድርጅቱ ቃል አቀባይ ዳኒኤል ሲድለር ለዶይቼ ቬለ እንደገለጹት ወደ ትግራይ የተላኩ የመድሃኒት አቅርቦቶች በ13 የጤና ጥበቃ ማዕከላት 65 ሺህ ታካሚዎችን ማከም የሚችሉና በአራት ሆስፒታሎች ከ6 ሺህ በላይ የስኳር ታማሚዎችን ለዓመት ሊያገለግል የሚችል ነው ብለዋል፡፡

https://p.dw.com/p/4BZOB
ምስል International Committee of the Red Cross/AP/picture alliance

የዓለማቀፉ ቀይ መስቀል ማህበር ርዳታ በሰሜን ኢትዮጵያ

በሰሜን ኢትዮጵያ ለድፍን አንድ ዓመት ከመንፈቅ ተባብሶ የቆየው ጦርነት ውድመት ካስከተለባቸውና ክፉኛ ካጠቃቸው ዘርፎች የጤናው መሠረተ ልማት ተጠቃሽ ነው፡፡ የጤና መሰረተ ልማቶች ጥቃቱ ከጤና ጥበቃ ተቋማት በተጨማሪ አገልግሎቱን የሚሰጡትም ላይ ማነጣጠሩ ትልቁ የሰብዓዊ ድጋፍ ትኩረት ሆኖም ሰንብቷል፡፡  

በተያዘው ዓመት ወደ ትግራይ ብቻ 55 በረራዎችን እና አራት መድሃኒት የጫኑ ተሸከርካሪዎችን ወደ ትግራይ ማስገባቱን የሚገልፀው የዓለማቀፉ ቀይ መስቀል ማህበር (ICRC) በአነስተኛ የጤና ተቋማት ከ65 ሺህ ሰዎች በላይ ተደራሽ ማድረጉን እና ከ6,600 በላይ የስኳር ታማሚዎች በሽሬ ፣  ሰመማ እና ሽራሮ ሆስፒታሎች ለአንድ ዓመት ያህል የሚገለገሉበት መድሃኒት ማድረሱን አስታውቋል፡፡ እንደ ኢንሱሊን፣ ሄሞዲያሊሲስ፣ ኦክሲቶሲን እና ሌሎች ህይወት አድን መድኃኒቶችም በጤና ሚኒስቴር መቅረቡን ድርጅቱ አመልክቷል፡፡ 

የዓለማቀፉ ቀይ መስቀል ማህበር (ICRC) ኢትዮጵያ ቢሮ ቃል አቀባይ ዳኒኤል ሲድለር በተለይም በዶቼ ቬለ ተጠይቀው በኢሜይል በላኩት መረጃ እንዳስረዱትም፤ በመቀሌ, አዲግራት, አድዋ, አክሱም እና ሽሬ በቀረበው የውሃ ማጣሪያ እና መልሶ ጥገና ስራ የአከባቢው ማህበረሰብ ንፁህ የመጠጥ ውሃ እንዲያገኙ ለማድረግ ተችሏል፡፡ የንጹህ ውሃ አቅርቦቱ በተለይም በመቀሌው አይደር ሆስፒታል የተኙ ከ500 በላይ እለታዊ ታካሚዎች ንጹህ የመጠጥ ውሃ እንዲያገኙ አስችሏል ነው ያሉት፡፡ መልሶ ጥገና የተደረገለት የሽሬ ሆስፒታልም በየእለቱ ከ100 በላይ ታካሚዎችን እያገለገለ መሆኑን እና በአከባቢው በተገነባው የውሃ ፕሮጀክት ከ40 ሺህ በላይ ሰዎች ተጠቃሚ እንዲሆኑ ማስቻሉንም ማህበሩ ጠቁሟል፡፡  

ICRC በማብራሪያው በቆቦ ከተማ፣ በትግራይ ማዕከላዊ ዞን ጭላ ከተማ እና በሶማሊ ክልል የውሃ ጄነሬተር እና ውሃ ማጣሪያ መድሃኒቶች ማቅረቡንም ጠቃቅሷል፡፡ እንደ ቃል አቀባዩ ዳኒኤል ሰድለር የጽሁፍ ማብራሪያ በትግራይ 19 የመጀመሪያ ደረጃ ጤና ማዕከላት 20 ሺህ ህሙማን ለአንድ ወር ያህል የሚጠቀሙበት የመጀመሪያ ደረጃ የህክምና ቁሳቁሶች መቅረቡንም አትተዋል፡፡  

ከህክምና እና የውሃ አቅርቦቱ ጎን ለጎን ICRC መሰረታዊ የቤት ውስጥ መገልገያ እቃዎችን ለ15 ሺህ ሰዎች ማበርከቱንና ከ20,000 በላይ ለሚሆኑ አርሶ አደሮች ዘር ማቅረቡንም አስታውቀዋል፡፡ 

Äthiopien Rotes Kreuz  Flagge
ምስል Solomon Muchie

ማህበሩ ከኢትዮጵያ ቀይ መስቀል ማህበር ጋር በመቀናጀት የጦርነት ሰለባ ማህበረሰብን በአገር ውስጥ እና በተለያዩ አከባቢ ተፈናቅለው ከሚገኙ ቤተሰቦቻቸው ጋር በነጻ የስልክ አገልግሎት በማግኘት ከሚወዱዋቸው ጋር እንዲገናኙ እየሰራ መሆኑንም አንስተዋል፡፡ 

በጦርነቱ ሳቢያ ለጾታዊ ጥቃት የተዳረጉም በማገገሚያ ማዕከላት የህክምና እና መድሃኒት አቅርቦት እንዲያገኙ ጥረት መደረጉን ICRC አመልክቷል፡፡ ይሁንና በዚህ ረገድ በትግራይ የተዳረሱ አገልግሎቶች ውስን እንደ መሆናቸው በአየርና በየብስ የሚጓጓዘው የመድሃኒት አቅርቦቱ ይቀጥላል ነው የተባለው፡፡ 

ማህበሩ ከኢትዮጵያ ቀይ መስቀል ማህበር ጋር በመሆን ከትግራይ ውጭም በአማራ፣ አፋር፣ ኦሮሚያ እና ሶማሌ ክልሎችም ተመሳሳይ የህይወት አድን እና ማገገም ስራዎች ላ እየሰራ መሆኑን ጠቁሟል፡፡  

በእርዳታ አቅርቦቱ ላይ ስለሚገጥማቸው ፈተናዎች የተጠየቁት የዓለማቀፉ ቀይ መስቀል ማህበር ቃል አቀባይ ዳኒኤል ሰድለር የእርዳታ ማጓጓዣውን ማቀናጀት ጊዜ የሚወስድ ተግባርና የፀጥታ እና ደህንነት ሁኔታ ወሳኙን ሚና የሚጫወቱ መሆኑን ጠቁመው፤ ከፌዴራል እና የክልል መንግስታት ግን አስፈላጊው ትብብር እየተደረገላቸው መሆኑን ገልጸዋል፤ በጽሁፍ በላኩልን ምላሽ፡፡ 

በግጭት ውስጥ ካሉ ተፋላሚ አካላት ትብብር ውጭ የሚደረግ የእርዳታ አቅርቦት ከመርህ ውጭ ነው ያሉት ቃል አቀባዩ፤ በአይደር ሆስፒታል እና መቀሌ ዩኒቨርሲቲ የቀረቡ የኬሞቴራፒ መድሃኒት አቅርቦቶች በጤና ሚኒስቴር እውቅና የተከናወነ መሆኑን የቅንጅታዊ ስራው አንዱ ማሳያ ነው ብለዋል፡፡ 

Pressebild Red Cross, Rotes Kreuz | Äthiopien Tigray, Hilfe
ምስል ICRC

በትግራይ ከሚስተዋለው ችግር አንጻር የቀረበው ድጋፍ አንስተኛ ነው ያሉት የማህበሩ ቃል አቀባይ ተፋላሚ ሃይላት ልነቶቻቸውን በውይይት በመፍታት ሊደርስ የሚችለውን አደጋ እንዲቀንሱም ጠይቀዋል፡፡ ከምንም በላይ ደግሞ በጦርነቱ ወቅትም ሆነ ከጦርነት ውጭ የሰላማዊ ዜጎች ጥበቃ ላይ ትኩረት እንዲያደርጉ ተጠይቀዋል፡፡ 

በትግራይ የምግብ ዋስትና ከምን ጊዜውም በላይ ተመናምኖ ይገኛል ያሉት የዓለማቀፉ ቀይ መስቀል ማህበር ቃል አቀባይ ዳኒኤል ስድለር ባለፉት ጥቂት ወራት እንኳን በትግራይ የተቀሰቀሰው ጦርነት ዳፋው ለአጎራባች ክልሎችም ጭምር በሰፊው ጥላ ያጠላ መሆኑንም ነው ያነሱት፡፡ በአከባቢው ለድጋፍ ተጋላጭ ለሆኑ ማህበረሰብ የእህል ዋጋ መናር እና የገንዘብ እጥረ አይነተኛ ፈተና ሆኖ ቀርቧልም ብለዋል፡፡ 

ሁኔታዎቹ በተመሳሳይ መልኩ ከቀጠሉም ሰዎች በቀን አንድ ጊዜ አንኳ መመገብ ወደ ማይችሉበት ሁኔታ ከማምራትም በላይ ሆስፒታሎች ላይ መድሃኒትና ምግብ ከቀሩ ሊታከም የሚችል በሽታ ሰዎችን ሊገድል እንደሚችልም ስጋታቸውን አስቀምጠዋል፡፡ 

ሥዩም ጌቱ

ልደት አበበ
ኂሩት መለሠ