1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

የነዳጅ ዋጋ ጭማሪና የንሮ ውድነት

ረቡዕ፣ መስከረም 23 2016

በኢትዮጵያ የምግብ እህል ዋጋ ግሽበት 28.2 በመቶ እንደሆነ መንግሥት ይገልጻል። በዚህ ሁኔታ የነዳጅ ድጎማ ማንሳት ተገቢ እንዳልሆነ የኢኮኖሚ ባለሙያው ዶክተር አለማየሁ ከበደ ያስረዳሉ። ይህ ካልሆነ ግን የዋጋ ግሽበቱ ከመንግሥት ቁጥጥር ውጭ ሊሆን እንደሚችልም አስጠንቅቀዋል።

https://p.dw.com/p/4X6fm
Äthiopien Kraftstoffknappheit in der Amhara Region
ምስል Alemnew Mekonnen/DW

"የዋጋ ግሽበቱ ከቁጥጥር ውጭ ሊሆን ይላል"

መንግሥት የነዳጅ ምርቶችን ለመደጎም በየወሩ በአማካይ 10 ቢልዮን ብር ወጪ እያደረገ ለዓመታት መቆየቱን ይገልጻል። ይህም ለኪሳራ እንደዳረገው በማከል። በዚህ ምክንያትም 147 ቢልዮን ብር የተከማቸ እዳ እንዳለበት አስታውቋል። በመሆኑም የሕዝብ ማመላለሻዎችን በመደጎም ለቀሪዎች ግን በየደረጃው ድጎማውን እያነሳ እንደሚሄድ ግልጽ አድርጓል። በዚህም መሰረት ባለፈው ዓመት በተደጋጋሚ የነዳጅ ጭማሪ የተደረገ ሲሆን በአዲሱ ዓመትም ጭማሪው ቀጥሏል። 
ይህ በጦርነትና በኢኮኖሚያዊ ውድቀት ምክንያት የኑሮ ውድነት ላደቀቀው ሕዝብ በእንቅርት ላይ ጀሮ ደግፍ እንደሚባለው ኑሮውን የበለጠ ከባድና ውስብስብ እንዳደረገበት መረጃዎች ያመላክታሉ። አቶ ሚካኤል አለማየሁ የአዲስ አበባ ነዋሪ ናቸው።የነዳጅ ጭማሪውን ተከትሎ እየተስተዋለ ያለው የዋጋ ጭማሪ ጫናው ከባድ እንደሆነ ይናገራሉ።
``የነዳጅ ዋጋ ጭማሪው ተከትሎ የሸቀጦች ዋጋ ወድያዉኑ ነው የጨመረው።ለምሳሌ የሽንኩርት ዋጋ በ3 ዕጥፍ ነው የጨመረው። ተጽዕኖው ለሁሉም የሕብረተሰብ ፍል ነው፤ ጫናው ከባድ ነው።``

የነዳጅ ወረፋ በድሬ ዳዋ
በድሬዳዋ ነዳጅ ለመቅዳት የተሰለፉ መኪኖች። የነዳጅ ዋጋ በጨመረ ቁጥር እጥረቱም አብሮ የሚከሰትበት ሁኔታ ለብዙዎች እንቆቅልሽ ሆኗል።ፎቶ ከማህደራችን የተወሰደምስል Messay Teklu/DW

በመጓጓዣው ዘርፍ ያለውን ተጽዕኖ


የነዳጅ ጭማሪው በቀጥታ ተጽዕኖ ከሚያሳድርባቸው መስኮች አንዱ የመጓጓዣው ዘርፍ ነው። በአዲስ አበባ የሜትር ታክሲዎች ከፍተኛ ጭማሪ ያደረጉ ሲሆን በመደበኛ ታክሲዎች ጭማሪውን ታሳቢ በማድረግ ይህ ዝግጅት እስከተጠናቀረበት ጊዜ ድረስ መንግሥት አዲስ ታሪፍ ባያወጣም ታክሲዎች ግን በዘፈቀደ ዋጋ እየጨመሩ እንደሆነ አቶ ሚካኤል ያስረዳሉ።
የሰለንዳ ኮሚዩኒኬሽን ሥራ አስኪያጅና የኢኮኖሚ ጉዳዮች ዘጋቢ ጋዜጠኛ ፍትህ አወቅ የወንድ ወሰን የነዳጅ ዋጋ ጭማሪውን ተንተርሶ አዲስ አበባ ውስጥ ተንቀሳቅሶ ለመሥራት አዳጋች ሁኔታ መፈጠሩን ይገልጻል። ኢኮኖሚውን ብዙ የማገገሚያ ፈውሶችችን ተጠቅሞ ማሻሻል ሲገባ የነዳጅ ድጎማ በማንሳት መፍትሄ እንደማያመጣ በማከል።
``የነዳጅ ድጎማ ተደርጎም የትራንስፖርት ችግሩ ሊፈታ አልቻለም። በተለይ አሁን ላይ ድጎማ የማይደረግላቸውም ስላሉ ከተማ ውስጥ መንቀሳቀስና መስራት ፈታኝ እየሆነ ነው ያለው``

ነዳጅ ለመቅዳት በአዲስ አበባ
በአዲስ አበባ ከተማ የነዳጅ እጥረትን ተከትሎ መኪኖች በዚህ መልኩ ረዥም ወረፋ መጠቅና፤ ለረዥም ጊዜ ጠብቆ አልቋል ተብሎ ሳይቀዱ መመለስም ብርቅ እየሆነ አደለም። ፎቶ ከማህደራችንምስል Solomon Muchie/DW

የማምረት ዓቅምን ስለማዳከም
ሸቀጦች በሚፈለገው መጠን በሌለባት ሀገር፤ የሕዝብ የመግዛት አቅም ተዳክሞ፤ እንዲህ ያለው የነዳጅ ዋጋ ጭማሪ ሕይወቱን ይበልጥ ሊያመሳቅለው እንደሚችል ይታሰባል። ከሰሞኑም የነዳጅ ዋጋው እንደጨመረ አዲስ አበባ ላይ በብርሃን ፍጥነት የሸቀጦች ዋጋ እየናረ እንደሆነ ጋዜጠኛ ፍትህአወቅ ያስረዳል።
የነዳጅ ዋጋ የማምረት ሂደትና ውጤት ላይ ቀጥተኛ ተጽዕኖ ከሚያሳድሩት አንዱ መሆኑን የሚገልጹት የኢኮኖሚ ባለሙያው ዶክተር አለማየሁ ከበደ በነዳጅ ላይ የሚደረግ የዋጋ ጭማሪ የማምምረት አቅምንም እንደሚያዳክም ነው የሚናገሩት።
``የማምረቻ ዋጋን ከሚጨምሩ ወይም ምርት ላይ ቀጥታ ተጽዕኖ ከሚያሳድሩት አንዱ ነዳጅ ነው። የማምረቻ ዋጋ ሲጨምር በምርት ላይ ዋጋ ይጨምራል። አምራቹ ሃይል ደግሞ ለምርት ያወጣውን ወደ ተጠቃሚው ነው የሚያሸጋግረው። ዞሮ ዞሮ እንዲህ አይነት የድጎማ ማንሳት በሃገሪቱ ኢኮኖሚ ላይ ከፍተኛ ጫና ያሳድራል። የአገሪቱ የማምረት አቅም ያዳክማል።``
መንግሥት ለሕዝብ ማመላለሻዎች ድጎማው እንዲቀጥል ያደረገ ቢሆንም ውጤታማነቱን ግን ብዙዎች አብዝተው ይጠራጠራሉ። የኢኮኖሚ ጉዳዮች ዘጋቢው ጋዜጠኛ ፍትህአወቅ የወንድወሰን «ድጎማው እየሠራ ነው ብዬ አላምንም» በማለት ትዝብቱን አጋርቶናል።

የዋጋው ፍትሃዊነት

በሌላ በኩል መንግሥት ሰሞኑ ያደረገው የነዳጅ ዋጋ ጭማሪ አሁን ካለው ዓለም አቀፍ የነዳጅ ዋጋ ጋር ሲነጻጸር ፍትሃዊ አደለም የሚሉ ወቀሳዎችም ይሰነዘራሉ። በዚህ ላይ ያላቸውን አስተያየት እንዲያጋሩን የኢኮኖሚ ባለሙያው ዶክተር አለማየሁ ከበደን ጠየቅናቸው።
``አለምአቀፍ ዋጋው ለ1 ሊትር 1.36 ዶላር ነው አሁን ያለው ዋጋ። ይህ ዛሬ ባለው የውጭ ምንዛሪ ብናሰላው 1 ዶላር 55 ብር ከ24 ሳንቲም ነው፤ ስለዚህ አንድ ሊትር  75 ብር ከ12 ሳንቲም ነው ዋጋው። እኛጋ እየተሸጠ ያለው 77 ብር አካባቢ ነው። ይህ የትራንስፖርትና አስተዳደራዊ ወጪዎች ጨምሮ ነውና ወ,ደፊትም በዚህ ይነት ሁኔታ የሚሄድ ከሆነ የዓለም የነዳጅ ዋጋ እየጨመረ ስለሆነ በኢትዮጵያ ኢኮኖሚ የሚያሳድረው ጫና ከባድ ይሆናል።``
በአገሪቱ ካለው ነባራዊ የኑሮ ውድነት አንጻር መንግሥት በነዳጅ ላይ የሚያደርገውን ድጎማ የማንሳት መርሃግብሩን እንዲያጤነው ብዙዎች እየወተወቱ ነው። የአዲስ አበባው ነዋሪው አቶ ሚካኤል እንደውም መንግሥት ድጎማ ማድረግ አለበት ባይ ናቸው።

እንደ ምክር

በኢትዮጵያ  የምግብ እህል ዋጋ ግሽበት 28.2 በመቶ እንደሆነ መንግሥት ይገልጻል። የዚህ አጠራጣሪነት እንደተጠበቀ ሆኖ በዚህ ሁኔታ የነዳጅ ድጎማ ማንሳት ተገቢ እንዳልሆነ የኢኮኖሚ ባለሙያው ዶክተር አለማየሁ ከበደ ያስረዳሉ። ይህ ካልሆነ ግን የዋጋ ግሽበቱ ከመንግሥት ቁጥጥር ውጭ ሊሆን እንደሚችልም አስጠንቅቀዋል።
``የነዳጅ ድጎማ በሚነሳበት ጊዜ የማምረት አቅም ነው የሚያዳክመው። የማምረት አቅም ሲዳከም 2 ዓይነት ነገሮችን ያስከትላል። አንዱ የምታመርተው ምርት ይቀንሳል። ሁለተኛ የምታመርተው ምርት ዋጋው ይጨምራል።

በተለይ ነዳጅ ሁሉንም የኢኮኖሚ ዘርፎችንስለሚነካ መንግስት ድጎማውን ባያነሳው ይመከር ነበረ ከመጀመሪያውኑ። እዚህ ከደረሰም በኋላም ቢሆን ወደፊት ባይሄድበት ይመከራል። ካልሆነ የዋጋ ግሽበቱ ከመንግስት ቁጥጥር ውጭ እንደሚሆን የሚገመትበት ሁኔታ ነው ያለው።``

ዮሐንስ ገብረእግዚአብሔር
ሽዋዬ ለገሠ