1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

በጋምቤላ ክልል የወንዞች መሙላት መፈናቀል አስከተለ

ረቡዕ፣ መስከረም 9 2016

በጋምቤላ ክልል በወንዝ ሙላት ምክንያት ከዘጠኝ ወረዳዎች የተፈናቀሉ ዜጎች ቁጥር 25ሺ መድረሱን የክልሉ መንግሥት አስታወቀ። ነዋሪዎች እንደሚሉት ከባለፈው እሑድ አንስቶ የባሮ ወንዝ በመሙላቱ በሺዎች የሚቆጠሩ በወንዝ ዳርቻ የሚኖሩ ዜጎች ተፈናቅለዋል።

https://p.dw.com/p/4Wbsq
ፎቶ፤ ጋምቤላ ክልል ባሮ ወንዝ
የባሮ ወንዝ መሙላት በአካባቢው የኗሪዎችን መፈናቀል አስከትሏል። ፎቶ፤ ጋምቤላ ክልል ባሮ ወንዝምስል privat

የወንዞች ሙላት በጋምቤላ ክልል

በጋምቤላ ክልል በወንዝ ሙላት ምክንያት ከዘጠኝ ወረዳዎች የተፈናቀሉ ዜጎች ቁጥር 25ሺ መድረሱን የክልሉ መንግሥት አስታወቀ። ሰሞኑን በባሮ ወንዝ ከገደቡ አልፎ ያስከተለው ጎርፍ በጋምቤላ ከተማ አራት ቀበሌዎች ውስጥ በርካታ መኖርያ ቤቶች መጥለቅለቃቸውን፤ ነዋሪዎችም ተፈናቅለው በየትምህርት ቤቱ ተጠልለው እንደሚገኙ የከተማው አስተዳደር አስታውቋል። ከተፈናቀሉት ሰዎች በተጨማሪ በንብረት ላይ ከፍተኛ ጉዳት መድረሱንና እየተመዘገበ እንደሚገኝ የጋምቤላ ከተማ ከንቲባ ተወካይ የሆኑት የጤና ጽሕፈት ቤት ኃላፊ አቶ ሳይመን ቲያች ተናግረዋል። የጋምቤላ ክልል ርዕሰ መስተዳድር ተወካይ አቶ ኡሞድ ኡሞድ ከባሮ ወንዝ በተጨማሪ የአኮቦ ወንዝ፣ የጊሎና አልዌሮ የተባሉ ወንዞች በመሙላት በኑዌር ዞን ወረዳዎች፣ በኢታንግ ልዮ ወረዳ፣ በጎግና በጋምቤላ ወረዳ ሰዎች መፈናቀላቸው ገልጸዋል፡፡ በክልሉ በአጠቃላይ በወንዝ ሙላት በዘጠኝ ወረዳዎች ውስጥ ሰዎች መፈናቀላቸውን አቶ ኡሞድ ለመገናኛ ብዙን በሰጡት መግለጫ አመልክተዋል።

ፎቶ፤ ጋምቤላ ክልል የወንዞች ከመጠን በላይ መሙላት
ባለፈው ዓመትም በጋምቤላ ክልል የወንዞች መሙላት ባስከተለው የጎርፍ አደጋ ከ1000 በላይ ሰዎች በ10 ወረዳዎች ውስጥ ተፈናቅለዋል። ፎቶ፤ ጋምቤላ ክልል የወንዞች ከመጠን በላይ መሙላት ምስል privat

ጋምቤላ ከተማ ነዋሪ የሆኑት አቶ ምትኩ ይልማ እንደተናገሩት ከባለፈው እሑድ አንስቶ የባሮ ወንዝ በመሙላቱ በሺዎች የሚቆጠሩ በወንዝ ዳርቻ የሚኖሩ ዜጎች ተፈናቅለዋል። የባሮ ወንዝ በዛሬው ዕለትም መጠኑ ከፍተኛ በሆነ መልኩ መጨመሩን አብራርተዋል። በከተማው አራት ቀበሌዎች ውስጥ ጉዳት ማድረሱን የገለጹት ነዋሪው ከከተማው በተጨማሪ በሌሎች ወረዳዎችም ውስጥ የወንዝ ሙላት ሰዎችን ከቤት ንብረታቸው ማፈናቀሉን ጠቁመዋል። የባሮ ወዝን መሙላቱን ተከትሎ በተለይም በጋምቤላ ከተማ በወንዝ አቅራቢያ የሚገኙ ነዋሪዎች በብዛት መፈናቃላቸውንም ተናግረዋል። በጋምቤላ ከተማ ቀበሌ አንድ ነዋሪ መሆናቸውን የነገሩን ሌላው በዚሁ የባሮ ወንዝ ሙላት የተፈናቀሉ ነዋሪም በአሁኑ ወቅት በትምህርት ቤት ውስጥ ተጠልለው እንደሚገኙ ጠቁመዋል፡፡ በጋምቤላ ክልል በክረምት ወራት የጎርፍ አደጋ እና ወንዝ ሙላት አልፎ አልፎ እንደሚከሰት የገለጹት ነዋሪው ከስድስት ዓመት ወዲህ የባሮ ወንዝ ዘንድሮ በከፍተኛ ሁኔታ መሙላቱን አብራርተዋል።

ፎቶ፤ ጋምቤላ ክልል ከገደቡ ያለፈው የባሮ ወንዝ ሙላት
በጋምቤላ ክልል በአጠቃላይ በወንዝ ሙላት በዘጠኝ ወረዳዎች ውስጥ ሰዎች መፈናቀላቸውን የክልሉ ባለሥልጣን ለመገናኛ ብዙሃን በሰጡት መግለጫ አመልክተዋል። ፎቶ፤ ጋምቤላ ክልል ከገደቡ ያለፈው የባሮ ወንዝ ሙላትምስል privat

የጋምቤላ ከተማ ከንቲባ ተወካይ የሆኑት አቶ ሳይመን ቲያች በከተማው ውስጥ እስካሁን ከአምስት ሺህ በላይ ሰዎች በውኃ ሙላት መፈናቀላቸውን አብራርተዋል። በጋምቤላ ከተማ ቀበሌ 1 ፣ 2 ፣ 4 እና 5 ውስጥ ነዋሪዎች መፈናቀላቸውን እና የባሮ ወንዝ ከሰሞኑ ከባድ ዝናብ ጋር ተያይዞ እየጨመረ መሆኑን ገልጸዋል። የጉዳት መጠኑን ለመቀነስ የአካባቢው ነዋሪዎች ጥንቃቄ እንዲያደረጉ እና ወደ ደርቃማ ስፍራዎች እንዲጠለሉ ለማድረግ በአደጋ መካላከልና ዝግጁነት በኩል ጥረት እየተደረገ እንደሚገኝም ተናግረዋል። በከተማው አራቱም ቀበሌዎችን ከንብረት ውድመት ውጪ በሰው ሕይወት ላይ ጉዳት አለመድረሱንም አቶ ሳይመን አመልክተዋል። ባለፈው ዓመትም በተመሳሳይ በጋምቤላ ክልል በደረሰው የጎርፍ አደጋ ከ1000 በላይ ሰዎች በ10 ወረዳዎች ውስጥ ተፈናቅለው እንደ ነበር ይታወሳል።

ነጋሳ ደሳለኝ

ሸዋዬ ለገሠ

ማንተጋፍቶት ስለሺ