1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

የወሎ አማራ የማንነትና ወሰን አስመላሽ ኮሚቴ የተቃውሞ መግለጫ

ዓርብ፣ ነሐሴ 10 2016

የአማራና የትግራይ ክልሎች የይገባኛል ጥያቄ በሚያነሱባቸው አካባቢዎች የተከናወኑ ስራዎች ችግሩን በዘላቂነት ለመፍታት የሚደረገውን ጥረት ስኬታማ ያደርጋል ሲል ጉዳዩን ለመከታተል የተቋቋመው ኮሚቴ ሰሞኑን ባወጣው መግለጫ አመልክቷል።የወሎ አማራ የማንነትና ወሰን አስመላሽ ኮሚቴ ግን መግለጫው እውነታውን የካደና የራያ ህዝብን ግፍ የዘነጋ ነው ብሏል።

https://p.dw.com/p/4jXJd
ራያ አለማጣ ከተማ
ራያ አለማጣ ከተማ መግቢያ በር ምስል Alemnew Mekonnen/DW

የወሎ አማራ የማንነትና ወሰን አስመላሽ ኮሚቴ የተቃውሞ መግለጫ

.

የአማራና የትግራይ ክልሎች የይገባኛል ጥያቄ  በሚያነሱባቸው አካባቢዎች የተከናወኑ ስራዎች ችግሩን በዘላቂነት ለመፍታት የሚደረገውን ሂደት  ስኬታማ እንደሚያደርገው ጉዳዩን ለመከታተል የተቋቋመው ዐቢይ ኮሚቴ ሰሞኑን ባወጣው መግለጫ አመልክቷል፣ በአንፃሩ የወሎ አማራ የማንነትና ወሰን አስመላሽ ኮሚቴ ኮሚቴው ያወጣው መግለጫ ተጨባጭ እውነታውን የካደና በራያ ህዝብ ላይ እየደረሰ ያለውን ግፍና በደል የዘነጋ ነው ሲል ገልጧል፡፡

የብሔራዊ ኮሚቴ መግለጫ

ብሔራዊ ኮሚቴው ባለፈው ነሐሴ 6/2016 ዓ ም ባወጣው መግለጫ ጉዳዩን በተመለከተ የተቋቋመው የቴክኒክ ኮሚቴ ዝርዝር ጉዳዮችን አጥንቶ ያቀረበለትን ሪፖርት ከገመገመ በኋላ የእስካሁን የትግበራ ምዕራፎች ስኬታማና መሬት ላይ ውጤት የታየባቸው መሆናቸውን ገልጧል፡፡
ከራያና ፀለምት ተፈናቅለው የነበሩ ዜጎች ወደ አካባቢያቸው እንዲመለሱ መደረጉን ያመለከተው የዐቢይ ኮሚቴው መግለጫ፣ ለዚህ ስኬትም የሀገር መከላከያ ሰራዊት ሂደቱን በመምራትና በማስፈፀም ረገድ ከፍተኛ አስዋፅኦ ማበርከቱን ጠቅሷል፡፡
ተፈናቃዮችን በመመለስ ሂደት በህዝቦች መካከል የታየው ኢትዮጵያዊ ባህል፣ አንድነት፣ ፍቅርና መተሳሰብ ዋጋ የሚሰጠውና ልምድ የሚወሰድበት እንደሆነ አብራርቷል፡፡
ተፈናቃዮችን በመመለሱ ሂደት ከሁለቱም ክልሎች በኩል የማደናቀፍ ስራዎች እንደነበሩ ያመለከተው የዐቢይ ኮሚቴው መግለጫ ሆኖም ችግሮቹ ከህዝብና ከመንግስት ፍላጎትና አቅም በላይ ባለመሆናቸው ስራዎቹ በስኬት ተጠናቅቀዋል ብሏል፡፡
በሀገር መከላከያ ሰራዊት አስተባባሪነት የፌደራል መንግስቱ በሚመድባቸው ሲቪል አመራሮች እገዛና በሁለቱ ክልሎች ታዛቢነት ህዝቦች በራሳቸው ተሳትፎ የራሳቸውን ጊዜያዊ አስተዳደር እንዲመርጡም ዐቢይ ኮሚቴው አቅጣጫ ማስቀመጡን አመልክቷል፡፡

ራያ፤ አለማጣ ከተማ
የወሎ አማራ ማንነት እና ወሰን አስመላሽ ኮሚቴ እንደገለፀው ከአለማጣ ከተማ የተናቀሉ ከ70 ሺህ በላይ የአማራ ተፈናቃዮች ለመመለስ ቢሞክሩም እስካሁን አልተሳካም ምስል Alemnew Mekonnen/DW

የወሎ አማራ የማንነትና ወሰን አስመላሽ ኮሚቴ መግለጫ

ይህ በእንዲህ እንዳለ የወሎ አማራ የማንነትናወሰን አስመላሽ ኮሚቴ ዐቢይ ኮሚቴው ያወጣውን መግለጫ በመቃወም ትናንት መግለጫ አውጥቷል፡፡
የአስመላሽ ኮሚቴው ሰብሳቢ አቶ ኃይሉ አበራ በተለይ ለዶይቼ ቬሌ እንደገለፁት አካባቢው ከሚገኙ በርካታ ቀበሌዎች በትግራይ ኃይሎች ቁጥጥር ስር እያሉ ዐቢይ ኮሚቴው “የትግበራ ምዕራፎች እጅግ ስኬታማ ናቸው” ብሎ መግለጫ ማውጣቱ ከእውነታው የራቀ ነው፡፡ አቶ ኃይሉ አክለውም ወደ ራያ አላማጣ የተመለሱ የትግራይ ተፈናቃዮች ሳይተቹ በጅምላ ገብተዋል ብለዋል፣ በአንጻሩ በአማራ በኩል የተፈናቀሉ ከ70 ሺህ በላይ ተፈናቃዮች ለመመለስ ቢሞክሩም እስካሁን አልተሳካም ነው ያሉት፡፡
አቶ ኃይሉ በራያ አላማጣ ካሉት 56 ቀበሌወች 44ቱ አሁንም በትግራይ ኃይሎች ቁጥጥር ስር እንዳሉ አመልክተዋል፣ ተፈናቃይ ተብለው የገቡት አብዛኛዎቹ ደግሞ ተዋጊዎች እንደሆኑ ነው የሚያብራሩት፣ ተፈናቃይ ቢሆኑ ኖሮ ቤታቸው በገቡ ነበር ግን ከሌላ አካባቢ ስለመምጣታቸው የሚያሳየው ተፈናቃይ ተብለው የመጡት በትምህርት ቤቶች እንደሚገኙ ነው የሚገልፁት፡፡ ተፈናቃይ የተባሉ አካላትም ወደ ከተማው ሲገቡ ደማቅ አቀባበል ተደርጎላቸዋል የሚለውን የዐቢይ ኮሚቴው መግለጫ አይቀበሉትም፡፡ “ተፈናቃዮች በሀገር ሽማግሌዎች እየተተቹ ይገባሉ ነበር የሚለው ስምምነቱ፣ እንኳን ሊተቹ ቀርቶ በይኃል ነው የገቡት” በማለት ገልጠዋል፡፡

ራያ፤ አለማጣ አካባቢ
በራያ አላማጣ ካሉት 56 ቀበሌወች 44ቱ አሁንም በትግራይ ኃይሎች ቁጥጥር ስር እንዳሉ የወሎ አማራ ማንነት እና ወሰን አስመላሽ ኮሚቴ ገልጿል።ምስል Alemnew Mekonnen/DW

አቶ ኃይሉ አካባቢው ለአለፉት 4 ዓመታት በጀት ሳይበጀትለት የቆየ ከመሆኑ አንጻር በርካታ ችግሮች አጋጥመውታል ብለዋል፣ ከ60ሺህ በላይ ተማሪዎች ከትምህርት ገበታ ውጪ ሆነዋል ያሉት አቶ ኃይሉ፣ የፌደራሉ መንግስትም ለአካባቢው ትኩረት ነፍጎታል ሲሉ ይከስሳሉ፡፡
ከ9ሺህ በላይ መሬት ባልታረሰበት፣ ከ13ሺህ በላይ አርሶ አደሮች የእርሻ ስራቸውን እንዳያከናውኑ በተስተጓጎሉበት ሂደቱ ስኬታማ መባሉን እንደማይቀበሉ ነው አቶ ኃይሉ የተናገሩት፡፡
“የፌደራል መንግስቱ ለራያ ህዝብ የነበረው እይታ ጤናማም፣ ጥሩም ነብር ብለን አንወስድም፣ ጊዜ ይፍታው በሚል ነው የተሄደበት፣ እንጂ ባለፉት 4 ዓመታት ከበጀት ውጪ የነበረ ህዝብ ነው”  ብለዋል፡፡

ችግሩን በዘላቂነት ለመፍታት ህዝበ ውሳኔ እንደሚደረግ ስምምነትና ቃልም የተገባ የነበረ ቢሆንም ህወሓት አልቀበለውም በማለቱ ብቻ የራያ ህዝብ አሁንም ተደጋጋሚ በደል እየደረሰበት ነው ሲሉ አክለዋል፡፡ የተሰጠው መግለጫም ከነባራዊ እውነታው ጋር አይገናኝም ሲሉ መግለጫውን ኮንነዋል፡፡
የወሎ አማራ የማንነትና ወሰን አስመላሽ ኮሚቴ ባወጣው መግለጫ የፕሪቶሪያው ስምምነት ፈርሷል የሚል እምንት እንዳለውና የፌደራሉ መንግስት ጉዳዩን እንደገና እንዲታይና ስምምነቱ እንዲከበር ፍትሀዊና ሚዛናዊ ያለውን አመራር እንዲሰጥ ጠይቋል፡፡
በጉዳዩ ዙሪያ አስተያየት እንዲሰጡን ለደቡባዊ ትግራይ ዋና አስተዳዳሪ አቶ ሀፍቱ ኪሮስ የእጅ ስልክ በድምፅና በአጭር የፅሁፍ መልዕክት ያደረግነው ሙከራ አልተሳካም፡፡

ዓለምነው መኮንን
ሂሩት መለሰ
ፀሀይ ጫኔ