የወልቃይት አቤቱታ
ማክሰኞ፣ የካቲት 15 2008የህዝቡን ጥያቄ ለፌደሬሽን ምክር ቤት ለማቅረብ ወደአዲስ አበባ መጓዛቸዉን የሚናገሩት የኮሚቴዉ አባላት ብዙ ተንገላተዉ መግባት ቢችሉም አቤታቸዉን ካቀረቡ በኋላ አሸባሪዎች ተብለዉ ተይዘዉ ለሰዓታት መመርመራቸዉንም ይናገራሉ።
ቀደም ሲል የወልቃይትን ህዝብ የአማራነት ጥያቄ ያነሱ ሰዎችም እስካሁን ያሉበት እንኳ አይታወቅም ይላሉ የአስተባባሪ ኮሚቴዉ አባላት። ከሁለት ሺህ ሰባት ወዲህም ሀገሪቱ ከራሷ አልፎ ለአፍሪቃ የሚበቃ ህገ መንግሥት እያላት የእኛ ጥያቄ በህገ መንግሥቱ ምላሽ ያገኛል በሚል ምሁራንንና ሀገሬዉን በማማከር ለህዋሃት ጽህፈት ቤት፤ ለአማራ ክልል፤ የፌደሬሽን ምክር ቤት ጨምሮ ለሚመለከተዉ ሁሉ በሰነድ የተደገፈ አቤቱታቸዉን እንዳቀረቡም አስረድተዋል።
የወልቃይት ህዝብ የአማራ ማንነት ጥያቄ አስተባባሪ ኮሚቴ አባላቱ እንደሚሉት አሁንም ይህን ጥያቄ ያነሳሉ ያስተባብራሉ ተብለዉ የሚጠረጠሩ ሰዎች በአካባቢዉ ለወከባ ተዳርገዋል። ድብደባ የተፈጸመባቸዉ ግለሰብም ጎንደር ሃኪም ቤት እንደገቡም ጠቅሰዋል። መረጃዎቹን ለማጣራት ወደወልቃይት ዞን ባለስልጣናት ስልክ ብንደዉልም ስብሰባ ላይ ነን እና ሥራ ላይ ነን በሚሉ ምክንያቶች ለጥያቄያችን ምላሽ ማግኘት አልቻልንም። የሀገሪቱ የፌደራል ጉዳዮች የህዝብ ግንኙነት ኃላፊ አቶ አበበ ወርቁ አቤቱታ አቅራቢዎቹ ደረሰብን ስላሉት የእስር እንግልት እሳቸዉም ሆነ መሥሪያ ቤታቸዉ የሚያዉቀዉ ነገር የለም ካሉ በኋላ ያቀረቡት ጥያቄ ግን በሽምግልና እየታየ እንደሆነ ገልጸዋል።
ሸዋዬ ለገሠ
አዜብ ታደሰ