የኮንጎው ውጊያ
ረቡዕ፣ ነሐሴ 22 2005
እንደገና ያገረሸው የኮንጎ ጦር ና M 23 የተባለው አማፂ ቡድን ውጊያ አንድ ሳምንት ሊሞላው ነው ። ውጊያው ዛሬም ቀጥሎ 3 ሺህ ጠንካራ ወታደሮች ያሰለፈው የተባበሩት መንግሥታት የኮንጎ ጣልቃ ገብ ኃይል ዛሬ በሄሊኮፕተሮችንና በከባድ መሣሪያዎች ጥቃት በመሰንዘር ለኮንጎ ጦር ድጋፍ ሰጥቷል ። M 23 ም ጥቃት እንደተፈፀመበት አረጋግጧል ። የጣልቃ ገቡ ኃይል ቃል አቀባይ ሌተና ኮሎኔል ፌሊክስ ባሴ እንደተናገሩት ጥቃቱ የተፈፀመው ከጎማ ውጣ ብሎ በሚገኘው ኪባቲ በተባለው ኮረብታ ላይ ነው ። ይህን መሰሉ የጣልቃ ገቡ ጦር እርምጃ ግን ለኮንጎ ችግር በተናጠል መፍትሄ ማምጣቱ አንዳንድ አስተያየት ሰጭዎች እንደሚሉት አጠራጣሪ ነው ። በእንግሊዘኛው ምህፃር ISS የተባለው የፀጥታ ጥናት ተቋም ባልደረባ ዴቪድ ዙሜኑ ይህን ከሚሉት አንዱ ናቸው ።« ዓለም ዓቀፉ ኃይል ብቻውን ችግሩን ያቃልላል ብሎ ማመን ስህተት ነው ። ችግሮቹ በአገሪቱ አጠቃላይ መዋቅሮች ውስጥ ስር የሰደዱ ናቸው ። ይህ ደግሞ መፍትሄ ሊያገኝ ይገባል ። ባለፈው የካቲት በአካባቢው ሃገራት የተፈረመው የሰላም ስምምነት የዲሞክራሲያዊት ሪፐብሊክ ኮንጎ ችግር መጠነ ሰፊ መሆኑን አጉልቶ ያሳያል ። ችግሩን የመፍታት ሃላፊነቱንም ለመንግሥትና ለሌሎች ጉዳዩ ለሚመለከታቸው ዘርፎች አከፋፍሏል ። ስምምነቱ የኪንሻሳ ባለሥልጣናት የምር የፖለቲካ ተሃድሶ እንዲያካሂዱም ጠይቋል ። »።
ባለፈው ዓመት ጎማን ለአጭር ጊዜ የተቆጣጠረው አማፂው M23 ወደ ሰሜን የሃገሪቱ ክፍል ቢያፈገፍግም ጎማና አካባቢዋን ማጥቃቱን አላቆመም ። ምንም እንኳን M 23 ጥቃት መሰንዘሩን ቢቀጥልም ቡድኑ ግን በመዳከም ላይ ነው ይላሉ ዴቪድ ዙሜኑ
«M23 አሁን ወደ መዳከሙ መሆኑን መገንዘብ አለብን ። እንደሚመስለኝ አመራሩ ወደ መበታተኑ ተቃርቧል ። የተመድ የአጥኚዎች ቡድን እንዳወጣው ዘገባ ከሆነ ከውጭ ማለትም ከጎረቤት አገራት የሚያገኙት ድጋፍ እየቀነሰ ነው ። እነዚህ ሁሉ ምክንያቶች ተደማምረው ቡድኑ አስቸጋሪ ደረጃ ላይ እንዲገኝ አድርገውታል ። »በዚህ የተነሳም ይላሉ ዙማኔ ቡድኑ የቀረው አማራጭ ወይ መንግሥትና ዓለም ዓቀፉ ማህበረሰብ በጀመሩት ጥረት ለመደራደር መዘጋጀት ና መሣሪያቸውን አስረክበውም ከጦሩ ጋር መቀላቀልን መቀበል አለያም የሚጠብቀው የተባበሩት መንግሥታት ጣልቃ ገብ ኃይልና የኮንጎ ጦር የሚሰነዝሩት የተባበረ ጥቃት ይሆናል ። ራድዮ ኦካፒ የተባለው የኮንጎ ራድዮ ጣቢያ እንደዘገበው M23 ትናንት ከምስራቃዊቷ ከተማ ጎማ 20 ኪሎ ሜትር ወጣ ብሎ በሚገኝ ስፍራ በኮንጎ ጦር ላይ ጥቃት ሰንዝሯል ። በአሶስየትድ ፕሬስ ዘገባ መሠረት ከዚያ ቀደም ሲል አማፂው ቡድን በሰነዘራቸው ጥቃቶች ሰላማዊ ሰዎች ተገድለዋል ። የጎማ አካባቢ ነዋሪዎች በዚያ የተሰማራው የተመድ ኃይል በቂ ጥበቃ አላደረገልንም ሲሉ ባለፈው ቅዳሜ ተቃውሞአቸውን አሰምተዋል ። ዴቪድ ዙሜኑ ዓለም ዓቀፉ ሰላም አስከባሪ ኃይል የቀድሞውን ዝናውን ማስመለስ አለበት ይላሉ
«የተባበሩት መንግስታት ድርጅት ኃይሎች በዲሞክራሲያዊት ሪፐብሊክ ኮንጎ ምንም የጥቅም አላስገኙም ። እንዲያውም አሁን ምንም ዓይነት ጥበቃ አላደረገልንም በሚሉ ነዋሪዎችና በተመድ ኃይሎች መካከል ውጥረት ተፈጥሯል ።
ስለዚህ አሁን የተመድ የቀድሞ ተዓማኒነቱ እንዲመለስና በዲሞክራሲያዊት ሪፐብሊክ ኮንጎ የሰላም ተልዕኮው ለሰማዊ ሰዎች ጥበቃ ማድረግና በM23 ስር የተሰለፉትን አማፅያን ማሸነፍ እንዲችል አንድ ነገር መደረግ አለበት ። »
የኮንጎው ውጊያ ለአካባቢው ሃገራትም ሰላም አልሰጠም ። ለምሳሌ ታንዛኒያ ከምስራቃዊቷ የኮንጎ ግዛት ኪቪ በሚጎርፉ ስደተኞች እየተጥለቀለቀች ነው ። በመሆኑም፣ ታንዛኒያ በኮንጎ በተሰማራው በዓለም ዓቀፉ ኃይል ሥር ወታደሮቿን አሳልፋለች ። የታንዛኒያው ፕሬዝዳንት ጃካያ ኪክዌቴ የሩዋንዳውን ፕሬዝዳንት ፖል ካጋሜን ግጭቱን በማባሳስ ይከሳሉ ። ኪክዌቴ ባለፈው ግንቦት በተካሄደው የአፍሪቃ ህብረት ጉባኤ ላይ ካጋሜ የኮንጎው መሪ ጆሴፍ ካቢላና የዩጋንዳው ፕሬዝዳንት ዩዌሪ ሙሴቬኒ ከሚወጓቸው አማፂያን ጋር እንዲነጋገሩም ሃሳብ ማቅረባቸው ውጥረቱን አባብሶታል ። ከዚህም በኋላ ኪክዌቴና ካጋሜ የቃላት ጦርነት ውስጥ ገብተዋል ።i
ሂሩት መለሰ
አርያም ተክሌ