1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

«ለልጆቻቸው የሚኖሩ ሩህሩህ እናት ነበሩ»

ልደት አበበ
ዓርብ፣ ሐምሌ 2 2013

ወላጅ የሞቱባቸው የበርካታ ልጆች እናት ነበሩ። የክብር ዶ/ር አበበች ጎበና። ሰሞኑን ከዚህ ዓለም በሞት ሲለዩ በተለይ እንደ እናት ላሳደጓቸው ልጆች ሀዘኑ ይጠነክራል። በዛሬው የወጣቶች ዓለም ዝግጅት ከእነዚሁ ልጆች ጥቂቱን አነጋግረናል።

https://p.dw.com/p/3wE2M
Abebech Gobena Äthiopien
ምስል DW/Y. Geberegeziabeher

ወጣት ቃልኪዳን ሀብታሙ ከክብር ዶ/ር አበበች ጎበና ልጆች አንዷ ናት። የአሳዳጊ እናቷ ስርዓተ ቀብር ማክሰኞ ሰኔ 29 ቀን 2013 ዓ.ም. ሲፈፀም በመስቀል አደባባይ በተደረገው የክብር ሽኝት ሥነስርዓት ላይ ግጥም አቅርባለች። የ3ኛ ክፍል ተማሪ ሳለሁ ነው ወደ የ «አበበች ጎበና ሕጻናት ክብካቤ እና ልማት ማህበር» የገባሁት የምትለው ቃልኪዳን በመድረክ ላይ ያቀረበች ግጥም በጋራ የተዘጋጀ እንደሆነ ነግራናለች። ዛሬ የግብርና ኢኮኖሚ የ2ኛ ዓመት የዩንቨርስቲ ተማሪ የሆነችው ቃልኪዳን እንደ ሌሎቹ ልጆቻቸው « እዳዬ» ስትል ነው የምትጠራቸው።ስሙን ያወጣችላቸው ከልጆቻቸው አንዷ ናት። « እዳዬ እዚህ ለመቆማችን ምክንያት ናቸው። የመኖራችን እዚህ ቦታ የመድረሳችን ሚስጥር ናቸው እዳዬ።ለልጆቻቸው የሚኖሩ ሩህሩህ እናት ነበሩ»ትላለች ቃልኪዳን።
ስለ ወይዘሮ አበበች ጎበና ሥራ ሲወራ ከ40 ዓመት በፊት ሁለት ወላጆቻቸው የሞቱባቸው ሕጻናትን ወስደው በማሳደግ እንደጀመሩ ይነገራል። ከእነዚህ ልጆች አንዷ ራሄል ብርሃኑ ናት። ዛሬ በአንድ የግል ድርጅት ውስጥ ተቀጥራ ትሠራለች። « ከግቢ ብወጣም አልተለየኋቸውም ነበር። እየሄድኩ አያቸው ነበር።» ራሄል በቅርቡ ሴት ልጅ ተገላግላ ከቤት ነው ያለቸው። የአሳደጓት እናቷ በኮሮና ተህዋሲ ታመው ሀኪም ቤት በመግባታቸው የተነሳ ሄዳ እንኳን ልትጠይቃቸው አልቻለችም ነበር። በቀብራቸው ሥነ ሥረዓት ላይም አልተገኘችም። እያለቀሰች በስልክ እንኳን ልታገኛቸው እንዳልቻለች እና ካመማቸው አምስት ዓመት እንደሆናቸው ነግራናለች።
ራሄል የሦስት ዓመት ገደማ ልጅ ሳለች አንስቶ ያሳደጓት ወይዘሮ አበበችን በአካል አግኝታ መሰናበት ባትችልም ከእሳቸው የተማረችው እና ሁሌም እሳቸውን የምታስታውስበት ብዙ ነገሮች አሏት። 
ማህበሩ ከተመሠረተ አንስቶ ከ 1,5 ሚሊየን በላይ ሰዎች ከክብር ዶ/ር አበበች ጎበና ተቋም ተጠቃሚ ለመሆን ችለዋል። በአሁኑ ሰዓት በማዕከሉ ስር የሚያድጉት ልጆች ቁጥር 35 ይሁን እንጂ 6000 የሚጠጉ ልጆች በማኅበረሰቡ ስር ድጋፍ እየተደረገላቸው እንደሚያድጉ ከማህበሩ ያገኘነው መረጃ ይጠቁማል። ደረጀ ቱፋ ሌላው የክብር ዶ/ር አበበች ጎበና ልጅ ነው። የ4 ዓመት ገደማ ልጅ ሳለ ነው ወደ ማህበሩ የገባው።  « ትምህርቴን የጨረስኩት እዛው ነው። አሁን የማስታወቂያ ድርጅት አለኝ።» ደረጀ እናቱን ለመጨረሻ ጊዜ ያገኘው ሆስፖታል ከመግባታቸው በፊት ነው። እሳቸው የጀመሩት ስራ እንዲቀጥል « ምክትል ከንቲባዋ ቃል በገቡት መሠረት መንግሥት የተቻለውን ሁሉ ያደርጋል ብዬ ተስፋ አደርጋለሁ። 
ከማኅበረሰቡስ ምን ይጠበቃል? ቃልኪዳን « እዳዬ ይህንን ተቋም ሲመሠርቱ ምንም አልነበራቸውም። እንደ ደሀ እናት ቆሎ ሸጠው ሁሉም ልጆቻቸውን እኩል አድርገው ያሳደጉት ስለዚህ ሰው ለሰው መኖር አለበት። ሁሉም የየድርሻውን መወጣት አለበት እላለሁ» ትላለች።

Äthiopien | Beisetzung Abebech Gobena
ምስል Seyoum Getu/DW
 Äthiopien | Abebech Gobena und Karheinz Böhm in 2010
አበበች ጎበና ከ“የሰዎች ለሰዎች” በኢትዮጵያ መስራች ካርል ሀይንዝ በም ጋር እጎአ 2010ምስል DW

ሰላም ዮሴፍ ፤ የድርሻዋን መወጣት ከጀመረች የተወሰኑ ዓመታት ተቆጠሩ። እሷንም ያሳደጓት የክብር ዶ/ር አበበች ጎበና ናቸው። አሁን በሂሳብ አያያዝ ትምህርት ተመርቃ ለማህበሩ የፋይናንስ ክፍል ሠራተኛ ናት።  « እዳዬ ያለ ደሞዝ ነው እድሜልካቸውን ማህበሩን ሲያገለግሉ የነበሩት እኔ ግን ደሞዝ እየተከፈለኝ ስብዕና በተሞላው ጊቢ ውስጥ ነው እየሰራሁ የምገኘው። በዚህም ደስተኛ ነኝ» ትላለች ሰላም። «ጊቢውን ማየቴ በራሱ ከደሞዝ በላይ ነው » የምትለው ሰላም  እሷም እንደሌሎቹ ልጆች በልጅነቷ ነው ወደ ሕጻናት ማሳደጊያው የገባችው። 14 ዓመት አካባቢ ሲሆናት «የቤተሰብ ግንኙነት ፕሮግራም» በሚል መርኃ ግብር ስር ተመርቃ እስክትጨርስ ድረስ ከማህበሩ ግቢ ወጥታ ነው ያደገችው። ሰላም « ኢትዮጵያዊቷ ማዘር ትሬዛ» የሚል ስም ስለተሰጣቸው አሳዳጊ እናቷ ስትናገር፤ በጎነታቸውን ቆጥራ አትጨርስም። « እዳዬ አቻችሎ ማኖርን፣ ትግዕስተኝነትን፣ ጠንክሮ መስራትን፣ ሰውነትን፣ ... እያለች ትቀጥላለች።
ከ 10 ዓመቱ ጀምሮ በዚሁ የሕጻናት ማሳደጊያ የኖረው ይልፋሰው ተክሉም ቢሆን አሳዳጊውን ወይዘሮ አበበችን አመስግኖ አይጨርስም። እዛው ተቋም ውስጥ ተምሮ ዛሬ የዘመናዊ የቀርከሀ ሥራ ባለሙያ ነው። « የተለያዩ የጥበብ ስራዎችን ያሰለጥኑን ነበር። የቀርክሃ፣ የእንጨት ስራ፣ የብረታ ብረት፣ የስጋጃ፣ጥልፍ፣ ስፌት የተለያዩ የእጅ ስራ ሙያዎችን ያሰለጥኑን ነበር።» ይልፋሰው ተቋሙ ባስተማረው ሙያ የሚሠራው ይልፋሰው ዛሬ የግሉን ሥራ ይሥራ እንጂ እሱም እንደ ሰላም ከአደገበት ግቢ አሁንም አልራቀም። በግቢው ብዙ የልጅነት ትውስታ አለው። « አብረውኝ ከሚያድጉት እህትና እና ወንድሞቼ ጋር ምንም እንኳን ብዙ ብንሆንም ከአንድ እናት እና አባት እንደተወለዱ ልጆች አድርገን ነበር ራሳችንን የምናየው። እዛ የነበረኝ ህይወት መቼም ሁሌም የማልረሳው ትውስታ ነው።» ይላል ይልፋሰው። 

ልደት አበበ

ሸዋዬ ለገሠ