1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

የኬንያ ፕሬዚደንት ከአመጹ ጀርባ የውጭ ዜጎች እጅ አለበት አሉ

ቅዳሜ፣ ሐምሌ 6 2016

ለሳምንታት በሕዝብ ተቃውሞ ስትናጥ የከረመችው ኬንያ ፕሬዚደንት ዊሊያም ሩቶ፦ በአብዛኛው የሀገራቸው ወጣቶችን አደባባይ ካስወጣው አመጽ እና ተቃውሞ ጀርባ የውጭ ኃይላት እጅ አለበት ሲሉ ከሰሞኑ ከስሰዋል ።ፕሬዚደንቱ ከተቃውሞው ጀርባ እጃቸው አለበት ያሏቸው ኃይላት የየትኞቹ ሃገራት እንደሆኑ ግን በቀጥታ አልተናገሩም ።

https://p.dw.com/p/4iF0g
በርካቶች ሕይወታቸውን ያጡበት የኬንያ ተቃውሞ
በርካቶች ሕይወታቸውን ያጡበት የኬንያ ተቃውሞምስል Amaury Falt-Brown/AFP

ፕሬዚደንቱ ከተቃውሞው ጀርባ እጃቸው አለበት ያሏቸው ኃይላትን ማንነት አልገለጡም

ለሳምንታት  በሕዝብ ተቃውሞ ስትናጥ የከረመችው ኬንያ  ፕሬዚደንት ዊሊያም ሩቶ፦ በአብዛኛው የሀገራቸው ወጣቶችን አደባባይ ካስወጣው አመጽ እና ተቃውሞ ጀርባ የውጭ ኃይላት እጅ አለበት ሲሉ ከሰሞኑ ከስሰዋል ። ፕሬዚደንቱ ይህን ያሉት በዚሁ ሳምንት ካጃዶ አውራጃ ውስጥ የኪሙካ ኤሌክትሪክ ንዑስ ጣቢያ ግንባታን ባስጀመሩበት መርኃ ግብር ላይ ነበር ።  «ኬንያ ዴሞክራሲያዊ ሀገር» መሆኗን አስረግጠው የተናገሩት ፕሬዚደንቱ ከተቃውሞው ጀርባ እጃቸው አለበት ያሏቸው ኃይላት የየትኞቹ ሃገራት እንደሆኑ ግን በቀጥታ አልተናገሩም ።

በዶይቸ ቬለ ኪስዋሂሊ ቋንቋ ክፍል ባልደረባ ጋዜጠኛ ዳኒኤል ሙቴቲ፦ ፕሬዚደንቱ ይህን ካሉ በኋላ ክፍላቸው በዚህ ጉዳይ ላይ የተለያዩ የፖለቲካ ተንታኞችን ማነጋገሩን ገልጧል ።  ሆኖም ይህ ነው በሚል በፕሬዚደንቱ በስም የተጠቀሰ ሀገር አለመኖሩንም አክሏል ።

«የተለያዩ የፖለቲካ ተንታኞችን አነጋግረናል አንዳቸውም የትኛውንም ሀገር አልጠቀሱም ስለዚህ ፕሬዚደንቱ በመሠረቱ ያሉት ምንድን ነው? በውጭ ሃገራት የሚኖሩ ኬንያውያንን ነው ወደ ሀገር ቤት ገንዘብ በመላክ በተቃውሞው የቆሰሉት እንዲታከሙ፤ የሞቱት እንዲቀበሩ ገንዘብ ነመላክ እጅግ የነቃ ተሳትፎ የሚያደርጉትን ነው ስለዚህ ፕሬዚደንቱ የውጭ ኃይላት ሲሉ የገለጡት እነዚህን ነው ግን ፕሬዚደንቱ የጠቀሱት አንድም ሀገር ስለመኖሩ ዐናውቅም »

የኬንያ ፕሬዚደንት  የውጭ ኃይላት ሲሉ ከመጥቀሳቸው ውጭ በቀጥታ በስም የተገለጠ ሀገር አለመኖሩንም የኬንያ ጉዳይ ዐዋቂ የፖለቲካ ተንታኞች ተናግረዋል ። «ባለፉት ጥቂት ቀናት ዊሊያም ሩቶ ያደረጓቸውን ተመልክተናል» ያለው ጋዜጠኛ ዳንኤል፦ ከሰሞኑ «ፕሬዚደንቱ የሚይዙ የሚጨብጡትን» ማጣታቸውን ሳይሸሽግ አላለፈም ። በውጭ ሃገራት እየኖሩ ኬንያ ውስጥ ያሉ ወጣቶችን ስለሚረዱ ስመጥር ሰዎችም ጠቅሷል።  

«በዝርዝር ሳይገልጡ በደፈናው የውጭ ኃይላት ነው ያሉት እኛ ግን በተጨባጭ ልንዘግበው የምንችለው ውጭ ሃገራት ስለሚኖሩ ሰዎች ነው ለአብነት ያህል ስመጥሩው ሚጉና ሚጉና አሉ በትዊተር በተደጋጋሚ የተጠቀሰው ኪሙዚም አሉ እነዚህ ሰዎች ውጭ ሃገራት ውስጥ የሚኖሩ ናቸው   ካሉበት ሀገር ሆነውም ገንዘብ ርዳታ ወደ ኬንያ ይልካሉ ሳይታክቱ በትዊተር መልእክት ያስተላልፋሉ እነዚህ ሰዎች የሚፈልጉት መንግሥት ተጠያቂ እንዲሆን ነው »

ተቃውሞ የበረታባቸው የኬንያ ፕሬዚደንት ዊሊያም ሩቶ
ተቃውሞ የበረታባቸው የኬንያ ፕሬዚደንት ዊሊያም ሩቶምስል TONY KARUMBA/AFP

ፕሬዚደንት ዊሊያም ሩቶ  ለኬንያ አመጽ  የውጭ ኃይላትን በከሰሱ ማግስት(ሐሙስ ዕለት) ከሁለት ሰዎች በስተቀር የካቢኔ ሚኒስትሮቻቸውን በአጠቃላይ መበተናቸው ተሰምቷል ። ፕሬዝደንቱ የወሰዱት ርምጃ በመላው ሀገሪቱ ለተነሳው ፀረ መንግሥት ተቃውሞ እንደምላሽ የሚታይ ነውም ተብሏል ። 

«ዛሬ በሕገመንግሥቱ አንቀጽ 1521 እና 1525B የጠቅላይ አቃቤ ሕግ አዋጅ ክፍል 12 በተሰጠኝ ሥልጣናት መሠረት ከአሁኑ ሰአት ጀምሮ የኬንያ ሪፐብሊክ ካቢኔ ጽሕፈት ቤቶችን እና ጠቅላይ አቃቤ ሕግን በትኛለሁ »

በፕሬዚደንት ዊሊያም ሩቶ ሳይሰናበቱ የቀሩት ሁለት ሰዎች የካቢኔያቸው ተቀዳሚ ዋና ጸሐፊ፤ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ሙሳሊያ ሙዳቫዲ እንዲሁም ምክትል ፕሬዝደንት ሪጋቲ ጋሻጉ ብቻ ናቸው ።  ፕሬዝደንቱ ርምጃውን የወሰዱት የሕዝባቸውን ድምፅ በመስማት መሆኑን ተናግረዋል ። በእርግጥ የፕሬዚደንቱ ርምጃ ለሕዝባዊ አመጹ ተቃውሞ ምላሽ ነውን? ከዚህ በኋላስ በቀጣይ አመራራቸው ምን ሊከተል ይችላል? ጋዜጠኛ ዳንኤል ሙቴቲ ወጣቶቹ ጊዜው ረፍዷል እያሉ ነው ማለታቸውን ጠቅሷል ።

«ሳይሰናበቱ የቀሩት ሁለት ሰዎች እነዚህ ብቻ ናቸው ግን ደግሞ ጎዳናዎች ላይ የወጣው ሰው የሚለው ይህ ራስን የማዳን ስልት እንደሆነ ነው ሰዉ የሚለው፦ ለፕሬዚደንት ዊሊያም ሩቶ ምርጡና ተገቢው አማራጭ ሥላጣን ለቅቀው ገሸሽ ማለታቸው እንደሆነ ነው ምክንያቱም ራሳቸውን ከጠቅላላ ካቢኔያቸው ሲነጥሉ የሚያሳየው መንግሥታቸው እየሠራ እንዳልሆነ ነው ካቢኔው ተበትኗል »

ኬንያውያን በአደባባይ ሰልፍ ላይ። ፎቶ፦ ከማኅደር
ኬንያውያን የሕምና ባለሞያዎች በአደባባይ ሰልፍ ላይ። ፎቶ፦ ከማኅደርምስል DANIEL IRUNGU/EPA

ምንም እንኳን ፕሬዚደንት ዊሊያም ሩቶ በቤታቸው የነደደውን አመጽ ለማብረድ ካቢኔያቸውን እስከመበተን ቢደርሱም እሳቱ ግን የጠፋ አይመስልም ። በትናንትናው እለት የኬንያ ፖሊስ አዛዥ ጃፌት ኮሜ ሥልጣናቸውን በገዛ ፈቃዳቸው ለቅቀዋል ። የፖሊስ አዛዡ ሥልጣን የለቀቁት  በኬንያ ጸረ መንግሥት አመጽ ወቅት  የፀጥታ ኃይላት በወሰዱት የኃይል ርምጃ በደረሰባቸው ብርቱ ነቀፌታ ነው ተብሏል ።

«Gen-Z» በሚለው ቅጽል ከሚታወቁት የኬንያ አመጽ ዋነኛ አቀጣጣይ ወጣቶች መካከል የተወሰኑት የፖሊስ አዛዡ ከሥልጣናቸው ይነሱ በማለት ድምፃቸውን ሲያስተጋቡ ነበር ። የፖሊስ አዛዡ ጃፌት ኮሜ የሥልጣን መልቀቅ ጥያቄን ፕሬዚደንት ዊሊያም ሩቶ ትናንት (ዐርብ ዕለት) መቀበላቸውን ሮይተርስ ዘግቧል ። ያም ብቻ አይደለም፤ የተቃውሞ ድምፆችን አድምጫለሁ ያሉት የኬንያ ፕሬዚደንት ተቃዋሚዎችን ያሳተፈ አዲስ ብሔራዊ የአንድነት መንግሥት ለመመስረት ቃል ገብተዋል ። ወይንም ተገድደዋል ። ተቃዋሚዎች ምን አሉ?

 በኬንያ ደም አፋሳሽ አመጽ ቢያንስ 39 ሰዎች ተገድለዋል
በኬንያ ደም አፋሳሽ አመጽ ቢያንስ 39 ሰዎች ተገድለዋል ምስል Shisia Wasilwa/DW

«የቀድሞው የተቃውሞ መሪ ራይላ ኦዲንጋን ወደ መንግሥታቸው ለመሳብም ሞክረው ነበር   ሰዎች ወደ በይነ መረብ ብቅ ብለው  ራይላ ኦዲንጋ ይህን እንዲያደርጉ አንሻም ሲሉ ነግረዋቸዋል እሳቸውም በትዊተር መልእክታቸው፦ አዎ ሰዎች ሰምቻለሁ፤ ይህን ነገር አላደርገውም ብለዋል   ስለዚህ ሰዉ፤ ተንታኞች በአጠቃላይ የሚሉት ምንድን? ፕሬዚደንት ዊሊያም ሩቶ እጅግ ሲበዛ አጭበርባሪ ናቸው   ለራሳቸው ጊዜ ለመግዛት ነው እየጣሩ ነው ይሏቸዋል »

በእርግጥ  ፕሬዚደንቱ እንደተባለው ጊዜ እየገዙ ነው ወይንስ  ለተቃውሞው ግፊት ምላሽ እየሰጡ? በውል የሚታወቅ ነገር የለም ። በትክክል የሚታወቀው፦ በኬንያ ደም አፋሳሽ አመጽ ቢያንስ 39 ሰዎች መገደላቸው ነው ። አብዛኛው የኬንያ ባለሥልጣናት እጅግ ቅንጡ በሆኑ ቁሶች ተሽቆጥቁጠው ሄሊኮፕተር ጭምር እየገዙ የተንደላቀቀ ኑሮ እየገፉ እኛ ግን የዕለት ቁራሽ ዳቦ አጥተናል ነው የአብዛኞቹ ወጣቶች የአደባባይ ጥያቄ ነው። እናስ በገዛ ፈቃድ ሥልጣን በመልቀቅም ሆነ ካቢኔ በመበተን የኬንያ ወጣቶችን አመጽ እንዲህ ማዳፈን ይቻል ይሆን? ጊዜ የሚፈታው ነው ።

ማንተጋፍቶት ስለሺ

ፀሐይ ጫኔ