የኬንያ ዘመቻ በሶማሊያና የአሸባብ በቀል
ማክሰኞ፣ ግንቦት 21 2004ለቆ የወጣው በሽንፈት ሣይሆን ስልታዊ ማፈግፈግ መሆኑን አመልክቷል። እንዲሁ ትናንት በኬኒያ ናይሮቢ በፈነዳ ፈንጅ 33 ሰዎች መቁሰላቸው ተሰምቷል። አሸባብ ጥቃቱን ስለማድረሱ በይፋ ባይናገርም፣ ባይወስድም፣ ብዙዎች ተጠያቂ ሳይሆን እንደማይቀር ይገምታሉ። በሶማሊያ የኬንያ ጦር የጀመረው ዘመቻንና አሸባብ በምላሹ እየወሰደው ነው የሚባለውን በቀል በተመለከተ ልደት አበበ በፕሪቶሪያ-የደቡብ አፍሪቃ የአለም አቀፍ የፀጥታ ተቋም የፖለቲካ ተንታኝን አነጋግራለች።
የአፍሪቃ ሕብረትና የሶማሊያ ወታደሮች ከሞቃዲሾ ሰሜን-ምዕራብ 30 ኪሎሜትር ፈንጠር ብላ የምትገኘው አፍጎዬን ከአሸባብ ቡድን አስጥለው 400 000 ተፈናቃይ ሱማሊያውያን ይኖሩበት ነበር የተባለውን መሬት በቁጥጥር ስር ማዋላቸውን አስታውቀዋል። ይህ ትክክል ከሆነ የአፍሪቃ ህብረት በአሸባብ ላይ የያዘውን ዘመቻ አጠናቅሮ መዝለቅ ይችላል ማለት ይሆን?- ፕሪቶሪያ- ደቡብ አፍሪቃ በሚገኘው አለም አቀፍ የፀጥታ ጥናት ተቋም ISS የአፍሪቃ ቀንድ ጉዳዮች ከፍተኛ ተመራማሪ- ኤንድሩስ አታ አሳሞአ መልስ ሰተውናል።
« የአፍሪቃ ህብረት ይህንን ቦታ ማስለቀቅ መቻሉ የአፍሪቃ ህብረት ወደፊትም ትግሉን መቀጠል ያስችለዋል ብዬ አስባለሁ። ይህንን ስል የአፍሪቃ ህብረት ከሱማሊያ የሽግግር መንግስት TFG ጋ በመተባበር ሞቃዲሾን ከአሸባብ ለማስለቀቅ ከመቻላቸው በመነሳት ነው። በዚህም የተነሳ የአፍሪቃ ህብረት ነፃ ያደረጋቸውን ቦታዎች ይዞ የመቆየት አቅም አለው ማለት ይቻላል። አንደኛ የአፍሪቃ ህብረት ወታደሮች ቁጥር በቦታው እየጨመረ ነው። ሁለተኛ አሸባብ ቀደም ሲል እንደነበረው ጠንካራ አይደለምና።»
በነዚህ ሁለት ምክንያቶች የተነሳ ለአሸባብ የአፍሪቃ ህብረት ወታደሮችን መዋጋት አዳጋች ቢያደርገውም ትግሉ ለአፍሪቃ ህብረትም ፈታኝ እንደሚሆን አታ አሳሞአ ይገልፃሉ።
« ቦታውን ይዞ መቆየቱ ፈታኝ ይሆናል።ምክንያቱም ግጭት ሊኖር እንደሚችል መጠበቅ ይኖርብሻል። የአፍሪቃ ህብረት ወታደር መከላከሉ ላይ ነው የተሰማራው እነሱ ደግሞ ማጥቃቱ ላይ ነው። ከመከላከል ይልቅ የአጥቂውን ቦታ መያዝ የተሻለ ነው። ስለዚህ ፈታኝ ይሆናል። ይሁንና የአፍሪቃ ህብረት ኃይል ቦታውን በቁጥጥር ስር እንደሚያውል እጠብቃለሁ።»
ትናንት በኬንያ ናይሮቢ በተጣለው ፈንጅ ቢያንስ 33 ሰዎች መቁሰላቸው ተነግሯል። ይህን መሰሉ ጥቃት ምን ያመላክታል? ኤንድሩስ አታ አሳሞአ « የኬኒያ የፀጥታ ተቋማት ቦንቡ በአሸባብ አካላት መጣል አለመጣሉን ማረጋገጥ ይኖርባቸዋል። ግን የትናንቱ የናይሮቢ ጥቃት የሚያመላክተው በተለይ ለምን እንደተጣለ ስናይ በኬንያ ላይ የሚጣሉት ጥቃቶች መጠናከራቸውን ነው። ከአሸባብ ይሁን አይሁን አላውቅም። አሸባብ ነው ብዬ ማለት አልፈልግም። ግን ኬንያ ደህንነት አስከባሪዎቿን ማጠናከር ይኖርባታል። ከጥቅምት ጀምሮ በኬንያ መኖሪያ በአሸባብ የሚጣሉት ጥቃቶች አይነት ጨምረዋል። ስለዚህ ኬንያ የሚቻል ከሆነ እነዚህን ቡድኖች ለማስወገድ በአገሪቷ እና በሶማሊያ የፀጥታ ቁጥጥሩን የበለጠ ማጠናከር አለባት።»
እንዲሁም የአፍሪቃ ቀንድ ጉዳዮች አጥኚ- ኤንድሩስ አታ አሳሙአ በምስራቅ አፍሪቃ ያለውን የሽብር ጥቃት እንዴት መከላከል እንደሚቻል ሲያብራሩ፤ « ሽብርን እና ጥቃትን ማሸነፍ ከፈለግን ፤ የሽብር መንስኤዎችን መመልከት ይኖርብናል።ሁለተኛ ደግሞ ቁጥራቸው እየጨመረ የመጡትን ምንም አይነት ስራም ሆነ መኖሪያ የሌላቸውን ወጣቶች ቁጥር መቀነስ ይኖርብናል። ይህንን የአፍሪቃ መንግስታት በስፋት ሊገነዘቡ ይገባል። የስራ አጥ ወጣቶች ቁጥር በጨመረ ቁጥር በአገሪቷ ላይ አለመረጋጋት እንዲፈጠር በር እየከፈትን መሆኑን መገንዘብ ይቻላል።»
ልደት አበበ
ሂሩት መለሰ