1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

የካንሰር ታማሚዎች ቁጥር መጨመር

ማክሰኞ፣ የካቲት 1 2014

በዓለማችን ከበሽታዎች በገዳይነቱ በሁለተኛ ደረጃ ላይ ተቀምጧል ካንሰር። የዓለም የጤና ድርጅት እንደሚለው በጎርጎሪዮሳዊው 2020 ዓ,ም ካንሰር ለ10 ሚሊየን ሰዎች ሞት ምክንያት ሆኗል። ይኽም ማለት በተጠቀሰው ዓመት ከሞቱ ስድስት ሰዎች አንዱ ሕይወቱ ያለፈው በካንሰር ምክንያት ነው።

https://p.dw.com/p/46hnC
krebs metastasen
ምስል Spectra/imago images/Shotshop

ጤና እና አካባቢ

ካንሰር በገዳይነታቸው ግንባር ቀደም ከሚባሉ የህመም አይነቶች አንዱ ቢሆንም በጊዜው ከተደረሰበት ሊታከም አስቀድሞም መንስኤዎቹ ላይ አተኩሮ መከላከል እንደሚቻል የዘርፉ የህክምና ባለሙያዎች ይናገራሉ። በብዛት ከሚያጋጥሙ የካንሰር አይነቶች የጡት፣ የሳንባ፣ የአንጀት፣ እንዲሁም የወንዶች የዘር ፍሬ ላይ የሚከተቱት የካንሰር አይነቶች ይጠቀሳሉ። ኢትዮጵያ ውስጥ በሚደረጉ የህክምና ምርመራዎች መሰረት በሴቶች ላይ የጡር ካንሰር በወንዶች ላይ ደግሞ የአንጀት ካንሰር በብዛት እንደሚያጋጥሙ ያነጋገርናቸው የካንሰር ከፍተኛ ህክምና ባለሙያ ገልጸውልናል።

ምንም እንኳን ላለፉት ሁለት ዓመታት ዓለም በኮቪድ 19 ወረርሽኝ ትኩረቱ ቢያዝም ዘንድሮም የዓለም የጤና ድርጅት በገዳይነቱ ከቀዳሚዎቹ ተርታ የፈረጀው ካንሰር እንደወትሮው ሁሉ ባለፈው ሳምንት ዓርብm በጎርጎሪዮሳዊው ፌብሩዋሪ 4 ማለትም ጥር 27 ቀን ዕለቱ ሲታሰብ የህክምናው ተደራሽነት በተለይ በድሃ እና በበለጸጉ ሃገራት መካከል ያለውን ከፍተኛ ልዩነት አመላክቷል። እንደ ድርጅቱ መረጃ ከሆነ አጠቃላይ የካንሰር ህክምና እና ክትትሉ በበለጸጉት ሃገራት 90 በመቶ ሲሆን በድሃ ሃገራት ግን 15 በመቶ ብቻ ነው። በካንሰር ምክንያት ከሚከሰተው ሞትም ከሦስቱ አንዱ አንድም በትንባሆ ማጨስ፣ አለያም ከመጠን ባለፈ ውፍረት፤ በአልክሆል መጠጥ መዘዝ፤ እንዲሁም በቂ ፍራፍሬ እና አትክልት ባለመመገብ ከዚህ በተጨማሪ ደግሞ በቂ የአካል እንቅስቃሴ ካለማድረግ ጋር በተያያዘ ሊሆን እንደሚችል ተጠቁሟል። የካንሰር ታማሚዎች ቁጥር እየጨመረ መሆኑን ያመላከተው የድርጅቱ መረጃ ምንም እንኳን በስፋት በሴቶች በኩል ስለጡት እና የማህጸን ጫፍ ካንሰር፤ በወንዶች ላይ ደግሞ ስለአንጀት እንዲሁም ስለዘር ፍሬ ካንሰር ጎልቶ ቢወራም በሽታው በየትኛውም የሰውነት ክፍል ሊከሰት እንደሚችል አጽንኦት ሰጥቷል።

Infografik Krebstote Afrika EN
አፍሪቃ ውስጥ ሕይወት የሚቀጥፈው ካንሰር

ኢትዮጵያ ውስጥ በየዓመቱ 65 ሺህ ገደማ የሚሆን ሕዝብ በካንሰር እንደሚያዝ መረጃዎችን ጠቅሰው የገለጹልን ዶክተር ማቴዎስ አሰፋ የዘርፉ ከፍተኛ የህክምና ባለሙያ ናቸው። ዶክተር ማቴዎስ እንደሚሉትም መረጃውን በተመለከተ በአብዛኛው ስለሚመዘገብ አዲስ አበባ ውስጥ በተሻለ ደረጃ ማግኘት ይቻላል። በየዓመቱም የአዲስ አበባ ከተማ ነዋሪ የሆኑ ብቻ ከ2500 እስከ 2900 የሚደርሱ የካንሰር ታማሚዎች ይኖራሉ። የታማሚዎቹ ብዛትን ተከትሎ የትኛው የካንሰር አይነት ጎልቶ ይታያል ለሚለው ባለሙያው እንዲህ ይዘረዝሩታል።

«በሴቶች በዋናነት የጡት ካንሰር እና የማህጸን ጫፍ ካንሰር፤ ከዚያ የአንጀት እና የእንቁላል አመንጪ ህዋስ ካንሰር ከአንድ እስከ አራት ያሉትን ይይዛሉ። ወንዶች ላይ የአንጀት ካንሰር ከዚያ የፕሮስቴት(የዘር ፍሬ አመንጪ አካል) ካንሰር ከዚያም ከግላንዶች ወይም እጢዎች ላይ የሚነሱ የካንሰር አይነቶች በዋናነት እስከ ሦስተኛ ደረጃ ያለውን ይይዛሉ።»

Symbolbild Brustkrebs Untersuchung
በግል የሚደረግ የጡት ላይ ካንሰር ፍተሻምስል Bo Valentino/Zoonar/picture alliance

የካንሰር ታማሚዎች ቁጥር በዓለም ደረጃ እየጨመረ መሄዱ በሚነገርበት በዚህ ወቅት ኢትዮጵያ ውስጥም ከቅርብ ጊዜያት ወዲህ የካንሰር ታማሚዎች እየተበራከቱ መሄዳቸውን የማይተላለፉ የጤና ችግሮች ላይ አተኩረው የሚሠሩ የተለያዩ ድርጅቶች ሲገልጹ ይደመጣል። ካንሰር ስለገዳይነቱ ጎልቶ የሚወራለት ቢሆንም አስቀድሞ በሚደረግ የአመጋገብም ሆነ በቂ የአካል እንቅስቃሴ ላይ በሚደረግ ጥንቃቄ መከላከል የሚቻል፤ ቀድሞ በምርመራ ከተደረሰበትም የመዳን ዕድሉ ሰፊ መሆኑን የዓለም የጤና ድርጅት መረጃ ያመለክታል። ለዚህም ኅብረተሰቡ ግንዛቤ እንዲያገኝ ማድረግ እንደሚገባም ይመክራል። የዘርፉ ከፍተኛ የህክምና ባለሙያ የሆኑት ዶክተር ማቴዎስም ይኽንኑ ያጠናክራሉ።

የሰዎችን ግንዛቤ ለማጎልበት ዓመታዊ መታሰቢያ ዕለቶች ጠብቆ የሚደረገው እንቅስቃሴ ብዙም ፋይዳ ሊኖረው እንደማይቻል ያሳሰቡት ዶክተር ማቴዎስ፤ ተከታታይ በሆነ እና ሰዎች ሊረዱት በሚችሉት መልኩ ስለካንሰር መንስኤዎች እና የህክምና መንገዶች በቂ መረጃዎችን ማዳረሱ አስፈላጊ መሆኑን አሳስበዋል።

ሸዋዬ ለገሠ

አዜብ ታደሰ