1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

የከተራ በዓል በአዲስ አበባ

ዓርብ፣ ጥር 10 2016

አዲስ አበባን በመሳሰሉ ከተሞች በመንግስትና በኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ-ክርስቲያን መካከል ተፈጠረ በተባለ አለመግባባት በዓሉ በቀድሞዉ ወግና ሥርዓት ላይከበር ይችላል የሚል አስተያየት ሲሰጥ ነበር።በተለይ የጠቅላይ ቤተ-ክሕነት ዋና ሥራ አስኪያጅ በቅርቡ «አዛዣችን በዝቷል» በማለት የሰጡት መግለጫ ሥጋት አሳድሮ ነበር

https://p.dw.com/p/4bTS9
የከተራ በዓል አከባበር በአዲስ አበባ በከፊል
የከተራ በአል ዛሬ አዲስ አበባ ዉስጥ በየዓመቱ እንደሚደረገዉ በደማቅ መንፈሳዊ ሥርዓት ተከብሯልምስል Solomon Muche/DW

የከተራ በዓል አከባበር በአዲስ አበባ

                       

በኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተ ክርስትያን የሚከበረው  የከተራ በዓል ዛሬ በተለያዩ ከተሞች መንፈሳዊ ድባቡን ጠብቆ ተከብሯል።በዓሉ አንዳድ አካባቢ በፀጥታ መታወክ፣ አዲስ አበባን በመሳሰሉ ከተሞች ደግሞ በመንግስትና በኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ-ክርስቲያን መካከል ተፈጠረ በተባለ አለመግባባት በዓሉ በቀድሞዉ ወግና ሥርዓት ላይከበር ይችላል የሚል አስተያየት ሲሰጥ ነበር።በተለይ የጠቅላይ ቤተ-ክሕነት ዋና ሥራ አስኪያጅ በቅርቡ «አዛዣችን በዝቷል» በማለት የሰጡት መግለጫ የበዓሉ የአከባር ሥርዓት ሊታጎል ይችላል የሚል ሥጋት አሳድሮ ነበር።ይሁንና የአዲስ አበባዉ ወኪላችን ሰለሞን ሙጩ እንደዘገበዉ የከተራ በአልን ለማክበር ዛሬ ከጧት ጀምሮ የርዕሰ ከተማዋ ዋና ዋና መንገዶችን ፣ አደባባዮችን ፣ አብያተ ክርስትያናትን እና ቅጥራቸው በልዩ ልዩ መንፈሳዊ መገለጫዎች ተውበዋል።ታቦታትም ወደየማደሪያቸዉ ተጉዘዋል።


የከተራ እና የጥምቀት ክብረ በዓላት የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን በየዓመቱ ጥር ወር ኢየሱስ ክርስቶስ ዮርዳኖስ ወንዝ ወርዶ ለሰው ልጆች ሁሉ ፀጋን ለመስጠት መጠመቁን ለማስታወስ ይከበራል። ለዚሁ ሲባል ታቦታት ከመንበረ ክብራቸው ወጥተው በአቅራቢያቸው ወደሚገኝ ውኃ የሚገኝበት ስፍራ ወይም ወንዝ ይወርዳሉ።ታቦታቱም በልዩ ልዩ የቤተ ክርስትያኗ መንፈሳዊ ዝማሬዎች፣ የምእመኑ እጀባ ሄደው በድንኳን ውስጥ እንዲያድሩ ይደረጋል።ይህ ለብዙ ሺህ ዓመታት የተደረገ መንፈሳዊ ሥነ ሥርዓት ነው። ይሄው ሥርዓት ዛሬም ቀጥሏል።

በዓሉ በተለያዩ መንፈሳዊ ሥርዓቶች ተከብሯል
የከተራ በዓልን ለማክበር አዲስ አበባ ዉስጥ ከጧት ጀምሮ ልዩልዩ ዝግጅቶች ሲደረጉ ነበርምስል Solomon Muche/DW

 

በአዲስ አበባ ከተማ 74 ጥምቀተ-ባህራት መኖራቸውን ከቤተ ክርስትያኗ የተገኘው መረጃ ያሳያል። የጥምቀት በዓል ከሀይማኖታዊ ፋይዳው በተጓዳኝ ኢኮኖሚያዊ እና ማኅበራዊ ፋይዳውም እጅግ የጎላ መሆኑ በግልጽ የሚታይ ነው። በዓለም የትምህርት፣ ሳይንስና ባህል ድርጅት (ዩኒስኮ) የማይዳሰስ ቅርስ ሆኖ የተመዘገበው የጥምቀት በዓል በከተራው ዛሬ ደምቆ ተከናውኗል። ጥምቀትም ሆነ ከተራው በሁሉም የሀገሪቱ አካባቢዎች  የሚከበር ሲሆን በተለይ በጥንታዊቷ ጎንደር  እናአዲስ አበባ ከተማ በጃን ሜዳ  በልዩ ድምቀት ይከበራል።

ሰለሞን ሙጩ

ነጋሽ መሐመድ

ታምራት ዲንሳ