1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

የኦሮሞ ተወላጆች መፈናቀል

ሐሙስ፣ መስከረም 11 2010

ዶቼቬለ ያነጋገራቸው አንድ የጭንሀክሰን ነዋሪ እንደሚሉት ከተለያዩ የሶማሌ ክልል አካባቢዎች ጭንሀክሰን ተጠልለው የነበሩ የኦሮሞ ተወላጆች በሙሉ ከዚያ እንዲወጡ ተደርጓል። ከመካከላቸው ከሶማሌላንድዋ ከተማ ከሐርጌሳ የተባረሩም ይገኙበታል።

https://p.dw.com/p/2kUj0
Karte Äthiopien Amhara, Tigray, Oromia Englisch

የኦሮሞ ተወላጆች መፈናቀል ቀጥሏል

በሶማሌ እና በኦሮምያ ክልል አዋሳኝ አካባቢዎች በተቀሠቀሰው ግጭት ምክንያት የኦሮሞ ተወላጆች መፈናቀላቸው መቀጠሉን ተፈናቃዮች እና የዓይን ምስክሮች ለዶቼቬለ ተናገሩ። ተፈናቃዮቹ እና የአይን እማኞች እንደሚሉት ሰዎች የሚፈናቀሉት ከተለያዩ የሶማሌ ክልል ከተሞች እና ከሶማሌላንድ ጭምር ነው። ከዚህ ቀደም ከተፈናቀሉት መካከልም ወደ ተለያዩ የኦሮምያ ከተሞች የተወሰዱ እንዳሉ እነዚሁ ሰዎች ለዶቼቬለ ተናግረዋል። ደም ያፋሰሰው የሶማሌ እና የኦሮምያ ክልሎች አዋሳኝ አካባቢዎች ግጭት አሁንም በርካታ የኦሮሞ ተወላጆችን እያፈናቀለ ነው እንደ አይን ምስክሮች። በግጭቱ  የተፈናቀለው ህዝብ ቁጥር ከ55 ሺህ በላይ ይገመታል ተብሏል። ከሶማሌ ክልልዋ ውጫሌ ተፈናቅለው አሁን ወተር በሚገኝ አንድ ትምህርት ቤት ውስጥ መጠለላቸውን የነገሩን አንድ ስማቸው እንዲጠቀስ ያልፈለጉ ተፈናቃይ በከተማይቱ በኦሮሞ ተወላጆች ላይ ከባድ በደል እየተፈፀመ ነው ይላሉ። ግለሰቡ ባለፈው ሳምንት ከሌሎች የአካባቢው ነዋሪዎች ጋር ህይወታቸውን ለማትረፍ ውጫሌ የሚገኝ የመከላከያ ሠራዊት ካምፕ ውስጥ ከገቡ በኋላ ያለ አንዳች ዝግጅት ድንገት ውጫሌን ለቀው እንዲወጡ መደረጉን ይናገራሉ።
ለ12 ዓመታት በኖሩበት በውጫሌ እንደዚህ ዓይነት ነገር ደርሶ አያውቅም ያሉት እኚሁ ተፈናቃይ ከአንድ ሳምንት በፊት አወዳይ ውስጥ የሶማሌ ተወላጆች ከተገደሉ በኋላ ሁሉም ነገር መቀየሩን ገልጸዋል። እኚሁ የአይን እማኝ ልጆቻቸው እና ወላጆቻቸውን ውጫሌ ጥለው ነው የመጡት። የቤተሰቦቻቸው አባላት እና ሀያ ሺህ ይሆናሉ ያሏቸው እዚያ የቀሩ ሰዎች ሁኔታ እጅግ አሳሳቢ ነው ይላሉ።የዛሬ ሳምንት ሐሙስ ድንገት ከውጫሌ እንዲወጡ የተደረጉት ተፈናቃዮች ወደ ተነሱበት ጭንሀክሰን እስኪደርሱ ድረስ ብዙ ስቃይ እና መከራ ደርሶባቸዋል እንደ ተፈናቃዩ።ዶቼቬለ ያነጋገራቸው አንድ የጭንሀክሰን ነዋሪ እንደሚሉት ደግሞ ከተለያዩ የሶማሌ ክልል አካባቢዎች ጭንሀክሰን ተጠልለው የነበሩ የኦሮሞ ተወላጆች በሙሉ ከዚያ እንዲወጡ ተደርጓል። ነዋሪው እንደተናገሩት ከመካከላቸው ከሶማሌላንድዋ ከተማ ከሐርጌሳ የተባረሩም ይገኙበታል። እኚሁ የጭንሀክሰን ነዋሪም ሆነ ሌሎች የዓይን እማኞች እንደሚሉት ከሶማሌ ክልል ከተፈናቀሉት የኦሮሞ ተወላጆች መካከል ወደ ተለያዩ የኦሮምያ ከተሞች የተወሰዱ ሰዎችም አሉ። ብዙዎቹ ወደ መኖሪያቸው ለመመለስ ተስፋ እያደረጉ ወደ ሌሎች አካባቢዎች መወሰዳቸው እያጠያየቀ ነው። የውጫሌው ተፈናቃይ ጭንሀክሰን ከደረሱ በኋላ ከሌሎች የውጫሌ ነዋሪዎች ጋር መኪና ተከራይተው ሐረርን ጨምሮ ወደ ተለያዩ ከተሞች ሄደው ነበር። ሆኖም የሚያስተናግዳቸው ባለማግኘታቸው ወደ ተወለዱበት አካባቢ ወደ ወተር እንደሄዱ ተናግረዋል። በዚያም የሚያውቋቸው ሰዎች ከሚያደርጉላቸው ድጋፍ ውጭ እርዳታ አላገኙሁም ይላሉ ።
በኦሮምያ እና በሶማሌ ክልል አዋሳኝ አካባቢዎች ግጭት ምክንያት ለተፈናቀሉት ሰዎች ስለ ሚደረገው እርዳታም ሆነ ስለ ቀጠለው መፈናቀል የኢትዮጵያ የአደጋ ስጋት ሥራ አመራር ኮሚሽን ኮሚሽን  እና የኦሮምያ ክልልዊ መንግሥት ባለሥልጣናትን ለማነጋገር ስልክ ብንደውልም ልናገኛቸው አልቻልንም። 

Karte von Äthiopien
ምስል DW/E.B. Tekle

ኂሩት መለሰ

ነጋሽ መሐመድ