1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

የኦሮሚያ ክልል ፕሬዝደንት አቶ ሽመልስ አብዲሳ የሰሞኑ ንግግርና አስተያየት

ዓርብ፣ ኅዳር 20 2017

የኦሮሚያ ክልል ፕሬዝዳንት ሽመልስ አብዲሳ በኦሮሚያ ክልል ውስጥ የፋኖ ታጣቂዎች ወደ ክልሉ እየገቡ ንጹሐን ዜጎች ላይ ጥቃት እንዲያደርሱ ሁኔታዎችን ያመቻቻል በማለት «ኦነግ-ሸነ» ያሉት የኦሮሞ ነጻነት ሠራዊት (ኦነግ-ኦነሰ)ን ወቀሱ።

https://p.dw.com/p/4naCh
የኦሮሚያ ክልል ፕሬዝዳንት ሽመልስ አብዲሳ
የኦሮሚያ ክልል ፕሬዝዳንት ሽመልስ አብዲሳ ፎቶ ከማኅደር ምስል Seyoum Getu/DW

«እንዳሻን እንዳንራመድ እያደናቀፈን ያለው ሸነ ነው»

ማክሰኞ ኅዳር 17 ቀን 2017 ዓ.ም. የገዢው ብልጽግና ፓርቲ አምስተኛ ዓመት ምስረታን ዘክረው በምሥራቅ ወለጋ ዞን ነቀምቴ ከተማ የአካባቢውን ኅብረተሰብ ያወያዩት የኦሮሚያ ክልላዊ መንግሥት ፕሬዝዳንት አቶ ሽመልስ አብዲሳ፤ በክልሉ የጸጥታ ሁኔታ ላይ አተኩረው በሰጡት ማብራሪያ፤ መንግሥታቸው በክልሉ ሰላም እንዲወርድ በሁለት አማራጮች፤ «በሰላም አማራጭ እና ሕግ በማስከበር» ረገድ ትልቅ ሥራ ቢሰራም እሳቸው «ኦነግ ሸነ» ያሉት ታጣቂ ቡድን ሰላም እንዳይወርድ እንቅፋት መሆኑን ገልጸዋል።

የክልላዊ ፕሬዝዳንቱ ንግግር

አቶ ሽመልስ በአሁኑ ንግግራቸው በክልሉበተለይም በአማራ ክልል አዋሳኝ አከባቢዎች ለሰላም መደፍረስ «ኦነግ ሸነ» ካሉት ታጣቂ በተጨማሪ «ጽንፈኛ» ያት የፋኖ ታጣቂዎችን ወቅሰዋል። በዚህም ሁለቱ ታጣቂዎች መንግሥትን ለማዳከምና ንጹሐንን ለማጥቃት አብረው ይሠራሉ ሲሉ ወንጅለዋል። «የኦነግ ሸነ ኃይል የጽንፈኛውን ኃይል በአራት መንገዶች ይደግፈዋል። የመጀመሪያ ሥራው ሕዝባችንን ትጥቅ አስፈትቶ አቅም በማሳጣት ለጥቃት ዳረጋቸው። ሁለተኛው መንግሥትን በወረዳ እና በቀበሌዎች ደረጃ በማዳከም ድጋፍ እየሰጡዋቸው ነው። ሦስተኛው የመንግሥት የፀጥታ ኃይል በጽንፈኞች ላይ እርምጃ ለመውሰድ ሲሄድ በመንግስት ጦር ላይ ተኩስ በመክፈት ለማዳከም ይጥራል።» ሲሉ ለክልሉ ሰላምና ጸጥታ አለመሻሻል ታጣቂ ቡድኑን ተጠያቂ አድርገዋል።

የመሳሪያ ንግድን በተመለከተ

«እንዳሻን እንዳንራመድ እያደናቀፈን ያለው ይሄ ኃይል ነው» ያሉት ሽመልስ የሚያስተዳድሩትን ክልል አስተዳደራዊ ወሰን እንደሚያስከብሩም ዝተዋል። ሁለቱን ታጣቂ ቡድኖች ደግሞ የመሳሪያ ንግድ ይለዋወጣሉ በማለትም ከሰዋል። «የጽንፈኛው ኃይልም ይሄው እናንተን እዚህ ሸነ እንደሚያሰቃያችሁ ነው የአማራን ሕዝብ የሚሰቃየው። ያንን ሕዝብ አይወክልም። አማርኛ ቢናገርም የሸነ ወንድም ነው። ከሚናገሩት ቋንቋ ውጪ በአመለካከትም በዓላማም ያው ናቸው። እንደዛ ያለ የጽንፈኝነት አመለካከት ግን ቦታ አያገኝም» ሲሉም ወቀሳቸውን ሰንዝረዋል።

የፕሬዝዳንቱ ንግግር ማወዛገብ

ይህ የኦሮሚያ ክልል ፕሬዝዳንት ሽመልስ አብዲሳ ንግግር ግን በስፋት ከተጋራ በኋላ በማኅበራዊ መገናኛ ዘዴዎች ሙገሳ እና ነቀፋ ገጥሞታል። የክልሉን ፖለቲካዊ ሁናቴ በቅርበት በመከታተል የሰላ ትችት በማቅረብ የሚታወቁት ፖለቲከኛ ጃዋር መሃመድ በይፋዊ ማኅበራዊ ገጻቸው፤ የፕሬዝዳንቱን ንግግር «ዛቻ» በማለት «እኛ የምንጣራው ሰላም እንዲያወርዱ ነው» ብለዋል። በርግጥ የፕሬዝዳንቱን ንግግር ወቅታዊ እና ትክክለኛ ነው በማለት አስተያየታቸውን የተጋሩም በርካቶች ናቸው። 

ነቀምቴ ከተማ
ነቀምቴ ከተማፎቶ ከማኅደር

አቶ ሽመልስ «ኦነግ ሸነ» ብለው ወቀሳያቀረቡበት የኦሮሞ ነጻነት ሠራዊት (ኦነግ-ኦነሰ) ትናንት ባወጣው ይፋዊ መግለጫ ደግሞ፤ «የክልሉን ሰላም ማስከበር የኛ ሥራ አይደለም» በማለት ሠራዊቶቹም «ለመንግሥት ሠራዊት ድክመት ምክንያት ሆኖ ሊቀርብ አይገባም» በማለት የቀረበበትን ክስ አስተባብሏል። ዶይቼ ቬሌ በኦሮሚያ ክልል ፕሬዝዳንት ወቀሳ ከቀረበበት ከሌላኛው ወገን የፋኖ ታጣቂዎች ለጊዜው የተሰጠ ማስተባበያም ሆነ ማረጋገጫ ባለማግኘቱ አስተያየታቸውን በዚህ ዘገባ ማካተት አልተቻለም።

የችግሩ እልባት

የኦሮሚያን ክልል ፖለቲካዊ ሁናቴን በቅርበት የሚከታተሉት የሰላምና ደህንነት ባለሙያ እንዲሁም በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ የሦስተኛ ድግሪ እጩ መብራቴ ገርጅሶ በሰጡን አስተያየት፤ በተፋላሚዎች መወቃቀስ ክፉኛ እየተጎዳ ያለውን ንጹሐን የክልሉ ማኅበረሰብን እንደማይጠቅም ገለጸው «መንግሥት የመጀመሪያ ሃላፊነቱ የዜጎችን ደህንነት ማስጠበቅ ነው» በማለት ሁለቱም ተፋላሚዎች ግን “እንታገልለታለን” ላሉት ሕዝባቸው ሲሉ ሰላምና እርቅ ቢያወርዱ እንደሚበጅ ተናግረዋል።

ሥዩም ጌቱ

ሸዋዬ ለገሠ

ፀሐይ ጫኔ