1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

“ሰላም ትልቁ ጸሎታችን ነው” የእሬቻ ሆራ ታዳሚያን

ሥዩም ጌቱ
እሑድ፣ መስከረም 26 2017

የዘንድሮው የኢረቻ ሆራ ሀር-ሰዲ ዛሬ በቢሾፍቱ ተከብሮ ውሏል፡፡ ከተለያዩ አቅጣጫዎች ወደ ከተማዋ ተመው የመጡ የእሬቻ ታዳሚያንም ከተማዋን አድምቀው ታይተዋል። በእሬቻ አከባበር ስነስርዓቱ የታደሙት አስተያየት ሰጪዎችም ለዶቼ ቬለ በሰጡት አስተያየታቸው በዓሉ በተከበረበት መንገድ ደስተኛ ናቸው፡፡

https://p.dw.com/p/4lSrx
የእሬቻ አከባበር ፤  ሰዎች ቆመው
የእሬቻ ሆራ ሀር-ሰዲ አከባበርምስል Seyoum Getu/DW

የእሬቻ ሆራ ሀር-ሰዲ አከባበር

ዛሬ ቢሾፍቱ ከተማ ውስጥ ተከብሮ የዋለው የ2017 ዓ.ም. እሬቻ ሆራ ሀርሰዲ እጅግ በርካታ ታዳሚያን የተሳተፉበት ሲሆን ከትናንት አመሻሽም ጀምሮ ከተማዋን በእጅጉ አድምቋታል፡፡ ከኦሮሚያ ክልል ከሁሉም አቅጣጫ እንዲሁም ከአገሪቱ ከተለያዩ ክልሎችም የተውጣጡ ተዳሚያን ያጨናነቋት ቢሾፍቱ እለቱን ደምቃ አሳልፋለች፡፡ 
አቶ አበራ ዳመና ከቢሾፍቱ ነው በበዓሉ የታደሙት፡፡ “እሬቻ ከዓመት ዓመት እያደገ እዚህ ደርሷል፡፡ የዘንድሮውም ላቅ ባለ ስነስርዓት ነው የተከበረው፡፡ የታዳሚን ቁጥርም እንደምትመለከተው በቁጥር ልትገልጸው የምትችለው አይደለም፡፡  ሰው በሚፈልገው መልኩ እሬቻውን እያደረገ እየተመለሰ ነው” ብለዋል፡፡
ወጣት ከቤክ ሞገስም በዚህ ደማቅ የበዓሉ አከባበር ላይ ስትታደም አግኝተን አስተያቷል ጠይቀናል፡፡ “እሬቻ ሁሉም ሚሰባሰብበት ታላቅ በዓል በመሆኑ በጉጉት ነው በየዓመቱ የምጠብቀው፡፡ አሁን አሁን ደግሞ ከኦሮሞም በተጨማሪ ብዙ ማህበረሰብ እየታደሙበት ነውና ለአንድነትም መልካም ምልክት ነው” ትላለች፡፡

የሆራ ሀይቅ ጋር ሰዎች ኤሬቻን ሲያከብሩ
ምስል Seyoum Getu/DW


ከአየርላንድ የመጡና ከቤተሰባቸው ጋር በዚህ ክብረበዓል ላይ ስታደሙ ያነጋገርናቸው ጎብኚም አስተያታቸውን ያጋሩን እንዲህ ሲሉ ነው፤ “ኦሮሞ ያወጣልኝ ስሜ ናሂሊ ነው፤ አየርላንዳዊ ነኝ፡፡ እዚህ የመምጣት አጋጣሚውን ያገኘሁት በኦሮሚያ ህብረት ስራ ባንክ የፋይናንስ አካታችነት ፕሮጀክት ላይ እየሰራሁ አንዱ ጓደኛዬ ጋብዞኝ ነው፡፡ ባለፉት ሁለት ዓመታት በኢትዮጵያ ውስጥ በቆየሁበት አጋጣሚ የታዘብኩት በሚገባው ደረጃ ለዓለም ያልተዋወቀ ማንም ሰው መታደም የሚችልና ደግሞ ማየትም ያለበት የእሬቻ ፌስቲቫል  ነው፡፡ ወደ አየርላንድ ስመለስ አንደኛው እቅዴ ቤተሰቦቼ በሙሉ በዚህ በዓል ላይ እንዲጋበዙልኝ ማድረግ ነው፡፡”
ከተለያዩ የኦሮሚያ ክልል ዞኖች የመጡ የእሬቻ ታዳሚያኑ በህብረት እየሆኑ በሚያዜሙት ዜማ ስለ ሰላም መናፈቅ ድምጻቸውን አጉልተው አንስተዋል፡፡ እርቅ ይውረድ ሲሉም ጥሪያቸውን ለሚመለከተው አካል አስተጋብተዋል፡፡ 


የእሬቻ ሆራ-ፊንፊኔ አከባበር

“በዚህ ያየሁት ነገር አንድነት ነውና  ከነበርንበት መጥፎ ሁኔታ ወደ መልካም የሚያሸጋግረን ይመስላል” ስትል  አስተያየቷን የሰጠችን ከዱከም ከተማ የመጣችው ትዕግስት የተባለች ወታት ታዳሚ ናት፡፡ 
ከሰሜን ሸዋ ዞን ጫንጮ ከተማ የመጡት አባሙዳ ቦረና አገሪ ደግሞ “አብሮነቱ አንድነቱ ተስፋ ሰጪ ነው የሚባለው የተለያዩ ብሔርብሔረሰቦች በዚህ ታድመዋልና አንድነቱን ያመጣ ይሆናል” ሲሉ ተስፋቸውን ገልጸዋል፡፡ አርሲና ከተለያዩ አከባቢ የመጡና አስተያየታቸውን ለዶይቼ ቬለ ያጋሩ ሌሎች አስተያየት ሰጪዎችም ተመሳሳይ ሀሳባቸውን በመጋራት ሰላም ከሁሉም ቀድሞ የሚናፈቅ ሲሉ በቀጣይ ወራት የሚጠብቁትን፤ ደግሞም ተስፋም የሚያደርጉት ሀሳባቸውን አንስተዋል፡፡


ሥዩም ጌቱ
ልደት አበበ