1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

የኤርትራው ፕሬዚዳንት ጉብኝት፤ በቤንሻንጉል ጉምዝ የንፁሃን መገደል

ዓርብ፣ ጥቅምት 6 2013

የኤርትራው ፕሬዝዳንት ኢሳያስ አፈወርቂ የሶስት ቀናት የኢትዮጵያ ጉብኝት  የአንበጣ መንጋ በሰብል ላይ እያደረሰ ያለዉ ጉዳት እንዲሁም በቤንሻንጉል ጉምዝ ክልል  የንፁሃን ዜጎችን  ህይወት የቀጠፈው ጥቃት በዚህ ሳምንት የማህበራዊ መገናኛ  ዘዴዎችን ያነጋገሩ ጉዳዮች ናቸው።

https://p.dw.com/p/3k3EN
Facebook User Symbolbild
ምስል Reuters/D. Ruvic

«የማኅበራዊ መገናኛዎች ቅኝት»

 

ለሦስት ቀናት የሥራ ጉብኝት ያለፈው ሰኞ ወደ ኢትዮጵያ የመጡት የኤርትራው ፕሬዚዳንት ኢሳያስ አፈወርቂ ከጠቅላይ ሚንስትር ዶክተር ዐብይ አህመድ ጋር የተለያዩ ቦታዎችን ጎብኝተዋል። ፕሬዚዳንት ኢሳያስ ጉብኝቱን አጠናቀው ሀሙስ ማለዳ  ወደ ሀገራቸው ተመልሰዋል።ይህ የፕሬዚዳንቱ ጉብኝት በዚህ ሳምንት የማኅበራዊ መገናኛ ዘዴዎችን ብዙ ያነጋገረ ጉዳይ ሲሆን፤ጉብኝቱን በበጎ የተመለከቱ የመኖራቸውን ያህል ትችት የሰነዘሩም አልጠፉም።

ሶሎሞን ሽፈራው የተባሉ አስተያየት ሰጪ «ወይ አጀንዳ ቅልበሳ። ህዝብ ያልቃል መሪው ደግሞ ጠላዋ እንዳማረላት ሴት ልማቴን እዩልኝ ቅመሱልኝ ይላል። »ሲሉ፤ ሸጌ  ማሬ የተባሉ አስተያየት ሰጪ ደግሞ «የኢሳይያስ አፈወርቂ የብዙ ዓመታት ልምድና የዐቢይ አሕመድ የወጣትነት ዕሳቤ ምሥራቅ አፍሪቃን ተመራጭ ክልል እንደሚያደርገው አልጠራጠርም።»ብለዋል።

ወልዱ ብርሃኔ  በበኩላቸው «የብሽሽቅ ፖለቲካና ዲፕሎማሲ መሆኑ ነው?»ሲሉ ፤ሙሌ ኪዳን ደግሞ«ኢሱ ወደ ኢትዮጵያ በመጣ ቁጥር ለቅሶ የምትቀመጡትን ቤት ይቁጠራችሁ»በማለት ፅፈዋል።

ቃል አብ  ባዬ ደግሞ  «እነዚህ ሰዎች ግን በድብቅ ምንድን ነው የሚሰሩት ? ስራ ነው ወይስ ሴራ?» ሲሉ። አመለ ሲሳይ የተባሉ የፌስቡክ ተከታታይ ደግሞ «የሱዳን፣ የጅቡቲ ፣የኬንያና ሌሎች ሀገሮች ፕሬዝዳንቶች ሲመጡ መደበኛ የዲፕሎማሲ ስራ ነው የምትሉ፤ ነገር ግን የኤርትራው ፕሬዚዳንት ሲመጡ፤ መጡ ሄዱ እያላችሁ የምትንጫጩ ሰዎች ትገርሙኛላችሁ።ታዲያ መሪዎች ሳይገናኙ ስለሁለቱ ሀጋራት  ሰላም እንዴት ይመክራሉ? በማለት የጉብኝቱን አስፈላጊነት ገልፀዋል።

ለእውነት እሞታለሁ በሚል ስም የሰፈረው አስተያየት ደግሞ«ሰው እያለቀ የዝሆን ጀሮ ይስጠኝ ብሎ።የመንግስታችን እንዲህ በጉብኝት ሽር ጉድ ማለት።ምን የሚሉት ፈሊጥ ነው?።»በማለት ተችተዋል። 

ቢኒ ቶሎሳ የተባሉ አስተያየት ሰጪ ደግሞ «ጉብኝቱን የሁለት ግለሰቦች ለምን ታደርጉታለችሁ?ይህ እኮ የሀገር ጉዳይ ነው።በሀገራቱ መካከል መተማመንና ሰላም የሚመጣው በዚህ መልኩ በመሆኑ ጉብኝቱ በግሌ ጥሩ ነው ብዬ አስባለሁ።»የሚል አስተያየት ሰጥተዋል።

ጌጡ ማሞ በበኩላቸው  «ዶ/ር አብይ ከፈጠረው ከፍተኛ ዲፕሎማሲ ውስጥ ከኢሳያስ ጋር እርቅ መፍጠሩ ነው፡፡ ይህ ባይሆን ኖሮ  የአባይና የነእንትና ጉዳይ  ምን ሊሆን ይችል ነበር።»ብለዋል።

ቲጂ ቲጂ በሚል ስም የሰፈረው አስተያየት ደግሞ እንዲህ ይላል «ምን እንደተነጋገሩ ባላውቅም እኛ ኢትዮጵያውያን ኤሪትራ ሄደን መዝናናት፣መሥራትና ኤሪትራዊያን ወገኖቻችንን መየት እንፈልጋለን። በመሃል ያለውን ተራራ አፍርሱትና መንገድ ሠርታችሁ በቅርብ ቀን አገናኙን»

ነፃነት ግዛው ደግሞ የፕሬዚዳንቱን ጉብኝት የወደዱት አይመስልም «ዶ/ር አብይ ግን ኢሳያስን ምን ያክል ቢያምነው ነው። የሃገርን የውስጥ ጉዳይ እንዲህ ከፋፍቶ የሚያሳየው። እኔ በበኩሌ ጥሩ አይመስለኝም።»ሲሉ፤

Instagram-Icon
ምስል picture-alliance/xim

መለስ ጴጥሮስ የተባሉ አስተያየት ሰጪም የላይኛውን ሀሳብ በመደገፍ «አየር ኃይለችን ያለበትን ሁኔታ መጎብኘታቸው አልተመቸኝም። ምንም እንኳ የቅርብ ወዳጃችን ቢሆኑ ለሌላ ሀገር መሪ በዚህ መልኩ ውስጣችንን ማሳዬት የለብንም።ድንገት አል ሲሲ ቢመጡስ እናሰያቸው ይሆን?»በማለት ፅፈዋል።

«አታስቡ ምርጡ መሪያችን ሰውንም አገርንም መለወጥ ያውቅበታል።»በማለት ጠቅላይ ሚንስትሩን ያሞካሹት ደግሞ ካሳሁን የተባሉ የፌስቡክ ተከታታይ ናቸው።

በቤንሻንጉል ጉምዝ ክልል መተከል ዞን የፀጥታ ችግርና ማንነት ላይ ያተኮረ ጥቃት በተደጋጋሚ ሲከሰት የቆዬ ሲሆን  በዚህ ሳምንትም በማንዱራ ወረዳ የበርካታ ንጹሃንን  ህይወት የቀጠፈ ጥቃት ተፈጽሟል። ይህንን ተከትሎ«ጥቃቱ በግለሰብ ግጭት የተከሰተ ነው።» መባሉና  ምክትል ጠቅላይ ሚንስትር ደመቀ መኮንን ደግሞ«ህዝቡ ራሱን ይከላከል» በሚል  ሰጡ የተባለው ምላሽም ሌላው በዚህ ሳምንት የማኅበራዊ መገናኛ ዘዴዎችን ያነጋገረ ጉዳይ ነው።

መልኬ ሀይሉ«የንፁሃን ደም እየፈሰሰ መንግስት ለምን በቸልተኝነት እንደሚመለከት አይገባኝም።ለፖለቲካው ይጠቅማሉ ተብሎ ስለሚታሰብ ብቻ በአካባቢው ችግር እጃቸው ያለበት ሰዎችን ሁሉ እሹሩሩ ማለት የት ያደርሳል።»ሲሉ

አማረ ማሞ ደግሞ «የአማራ ክልል የሰላም ግንባታ ሀላፊ ችግሩ ማንነት ላይ ያተኮረ ነው እያሉ።በሌላ ወገን የግለሰብ ጠብ ነው ይሉናል።በሞት ላይ መቀለድ ይሉሃል ይህ ነው።»ብለዋል።

ሽመልስ ተስፋዬ በበኩላቸው«የታጠቁ ሀይሎች እየተባለ የነበረው ድራማ ወደ ግለሰብ ጠብ ተቀየረ ማለት ነው?»ብለዋል። ዳሳሽ በንቴ የተባሉ አስተያየት ሰጪ ደግሞ «ህዝቡ ራሱን እንዳይከላከል መሳሪያ ተነጥቆ እንዲገደል ከተደረገ በኋላ ምንዋጋ አለው።በጣም የዘገዬ መፍትሄ ነው።» የሚል አስተያየት ሰንዝረዋል። 

ቲጂ ላቭ በሚል ስም የሰፈረው አስተያየት ደግሞ«ህዝቡ ግብር የሚከፍለው መንግስት ይጠብቀናል ብሎ አይደለም እንዴ? መንግስት የማንን ጎፈሬ ሊያበጥር ነው። ህዝቡን ወደ ወታደርነት የሚቀየረው።»ይላል።

ጣሂር ሙሌ በበኩላቸው «የምክትል ጠቅላይ ሚንስትር ደመቀ መኮነን መልስ ምርጫ ከማጣት የመጣ ይመስለኛል።በቅርቡ የሰላም ሚንስትር ፣የመከላከያ ሚንስትርና ምክትል ጠቅላይ ሚንስትሩ ራሳቸው ባሉበት ችግሩ ተፈቷል ከተባለ ወዲህ ።አፍታም ሳይቆይ እንዲህ ያለ ችግር መከሰቱ ተስፋ ያስቆረጣቸው ይመስለኛል።»ብለዋል።

«መከላከያን የሚገል የተደራጀ አካል ህዝቡ በምን አቅሙ ነው የሚከላከላው?መፍትሄው መንግስት  ችግሩን በዘላቂነት መፍታትና ህዝቡ በሰላም የሚኖርበትን መንገድ መፈለግ ነው።ማስታጠቅ ዘላቂ መፍትሄ  አይመስለኝም። »ያሉት ደግሞ ከዲጃ ዑመር ናቸው።

ትግስት ተረፈ«ተፈናቅለው የሄዱና ሰላም ወርዷል ተብለው ወደ አካባቢው የተመለሱ ሰዎች ሁሉ እየተገደሉ ስለሆነ ራስን መከላከል ለጊዜውም ቢሆን ከችግር ያድናል።መከላከያና ፖሊስም ቢሆን የሚደርሰው ሰው ከሞተ በኋላ ነው።»

ዲያሞ ዳሌ «ዜጎች ታጥቀው ራሳቸውን እንዲከላከሉ ማድረግ ዘላቂም ባይሆን ጥሩ መፍትሄ ነው።ሰላማዊ ዜጋ በታጠቀበት ሽፍታ ዝር አይልም።»ሲሉ ዞላ መንግስቱ ኢትዮጵያ ደግሞ «መፍትሄ አይሆንም»ብለዋል።

Symbolbild Apps Facebook, Google und Google + Anwendungen
ምስል Imago Images/P. Szyza

«የመንግስት መዋቅርን ተጠቅሞ የሚገል ቡድን ባለበት ቦታና  ሆን ተብሎ አንድን የማኅበረሰብ ክፍል ለማጥቃት እየተደረገ ያለን ነገር እንደ ቀላል ነገር የግለሰብ ጠብ ምናምን ማለት ግን ያስተዛዝባል።»ይላል ጆኒ ጆኒ በሚል የፌስቡክ ስም የሰፈረው አስተያየት።

ቢኒያም መለሰ በበኩላቸው«የንፁሃን ሞት መቼ ነው የሚቆመው?ከሬሳ ቆጠራና ከነብስ ይማርስ መቼ ነው የምንወጣው።? መንግስታችን እባክህ ለጊዜው ከተማ ማስዋቡን  ቆም አድርግና ህዝብን ታደግ።»ሲሉ፤«መንግስታችን ምነው ችግሩ ላይ መተኛት መረጥክ።»ያሉት ደግሞ ሄዋን መካሻ ናቸው።

ሌላው በዚህ ሳምንት ካነጋገሩ ጉዳዮች አንዱ  በአማራ በትግራይና ኦሮሚያ ክልል አንዳንድ አካባቢዎች  የአንበጣ መንጋ በሰብል ላይ እያደረሰ ያለው ጉዳት ነው።መንግስት የተከሰተውን የአንበጣ መንጋ በፍጥነት ለመቆጣጠርና በሰብል  ላይ የሚያደርሰውን ጉዳት ለመቀነስ  ርብርብ በማድረግ ላይ መሆኑንም ቢያስታውቅም በደረሰው ችግር መንግስትን የተቹ ብዙዎች ናቸው።

ከማል ሰኢድ «የበረሃ አንበጣ ለመከላከል የኬሚካል ርጭት ሲካሄድ አደጋ ደርሷል የሚለውን ብቻ ነው የሰማነው።በተረፈ ውጤታማ ስራ አላየንም።» ሲሉ፤ክፍሎም ጎታን «የገበሬው ምርት በአንበጣ መንጋ እያለቀ ነው።በአውሮፕላን ምትክ በኢትዮጵያ ሰማይ ላይ አንበጣ እየበረረ ነው።ያሳዝናል።»ብለዋል።አበራሽ በበኩላቸው «የደረስውን ጉዳት በስፍራው ተገኝቶ መጎብኘት ግብዝነት ነው። ጉዳቱ ሳይደርስ ቀድሞ መከላከል ነው እንጂ ጉዳት ካደረሰ ቦኋላ ጉብኝት ማድረግ ለአርሶ አደሩ ምንም አይፈይድም።»ሲሉ፤መሀመድ አወል ሀጎስ ደግሞ«የምስራቅ አፍሪካ የበርሃ አንበጣ ተቆጣጣሪ ድርጅት ከስምንት ወራት በፊት የኢትዮጵያን ምስራቅ እና ሰሜን ምስራቅ አከባቢዎች ጨምሮ በርካታ የምስራቅ አፍሪካን ሃገራት ከፍተኛ የአንበጣ መንጋ ጥቃት እንደሚያደርስባቸው ጠቁሞ ተገቢው የቅድመ-መከላከል ስራ መንግስታት እንዲሰሩ አስታውቆ ነበር።ታዲያ የኢትዮጵያ መንግስት የተሰጠውን ጥቆማ መሠረት አድርጎ ችግሮችን ቀድሞ መከላከል ላይ ቢሰራ ኖሮ አሁን የአንበጣ መንጋ በገበሬው ሰብል ላይ እየደረሰ ያለው ውድመት መቀነስ በቻለ ነበር።ግን አልሆነም።»ብለዋል።

ውቅያኖስ ብርሃነ ደግሞ «አንድ ፊቱን ኣንበጣ ይሻላል  ሰብል እንጂ የሰው ሂወት ኣይበላም።»ያሉ ሲሆን፤

ኤፍሬም ማሜ «ችግሩ የክፋታችን ድምር ውጤት ቢሆንም ግን የጉዳቱ ሰለባ የዋሁ አርሶ አደር  የዚህ እዳ ተሸካሚ ሲሆን ሀዘኑ ከባድ ነው።»ብለዋል።ተስፋዬ መሀሪ ደግሞ«አምበጣዉ ገና በኩብኩባነት ደረጃዉ እያለ ህዝቡን አስተባብሮ  በመጠነኛ የኬሚካል ርጭት መከላከል ይቻል ነበር። በስንቱ እንቃጠል ።»በማለት በቁጭት ፅፈዋል። 

ልባርጋቸው የተባሉ የፌስቡክ ተከታታይ ደግሞ «በለያዩ የሀገሪቱ ክፍሎች የገበሬው ሰብል ከመውደሙ በፊት የሚመለከተው አካል ከ ወረዳ እስከ ፌደራል ያሉት አካላት ምን ያህል ዝግጅት አድርገው ነበር? የምስራቅ አፍሪካ የበረሃ አንበጣ መከላከል «ሄድ ኳርተር» አዲስ አበባ ተቀምጦ ምን አይነት ዝግጅቶች አከናወነ? መንጋው ከተከሰተ ቦኋላስ የሚመለከታቸው ባለድርሻ አካላት ምን ይሰሩ ነበር? የሚለውንም ደጋግሞ መጠየቅ ይገባል።»በማለት አስተያየታቸውን አስፍረዋል።

ፀሐይ ጫኔ

ሽዋዬ ለገሠ