1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

የኢትዮ-ቴሌኮም ቴሌ-ብር ምን ይዞ መጣ?

ረቡዕ፣ ግንቦት 4 2013

ኢትዮ-ቴሌኮም ሥራ ባስጀመረው ቴሌ-ብር በ5 አመት 33 ሚሊዮን ደንበኞች በማፍራት 3.5 ትሪሊየን ብር ለማንቀሳቀስ አቅዷል። ግልጋሎቱን የሚሹ በመተግበሪያው፣ በአጭር የጽሁፍ መልዕክት ወይም ፈቃድ ከተሰጠው ወኪል ዘንድ በመቅረብ መመዝገብ ይችላሉ። በ2011 ዓ.ም. የተወጠነው ቴሌ-ብር ከቻይናው ሑዋዌ ኩባንያ በመተባበር ሥራ ላይ የዋለ ነው

https://p.dw.com/p/3tJ7X
Smartphone und Gedlscheine
ምስል babimu - Fotolia.com

ከኤኮኖሚው ዓለም፦ የኢትዮ-ቴሌኮም ቴሌ-ብር ምን ይዞ መጣ?

ኢትዮ-ቴሌኮም ትናንት ማክሰኞ ግንቦት 3 ቀን 2013 ዓ.ም. ለ53 ሚሊዮን ደንበኞቹ የቴሌ-ብር አገልግሎትን በይፋ አቅርቧል። "ቴሌ-ብር ባለፉት 127 አመታት የገነባንውን የቴሌኮም መሠረተ-ልማት በኢንፎርሜሽን የበለጸገ ማሕበረሰብ ከመገንባት ባለፈ ለፋይናንስ አገልግሎት ተደራሽ ያልሆነውን ማሕበረሰባችንን ተጠቃሚ ለማድረግ ታስቦ የተወለደ አገልግሎት ነው። አገልግሎቱን ለመጀመር ውጥኑን የጀመርንው ከሁለት አመት በፊት ነው" ሲሉ ጠቅላይ ምኒስትር ዐቢይ አሕመድን ጨምሮ ከፍተኛ የመንግሥት ባለሥልጣናት በተገኙበት የኢትዮ-ቴሌኮም ዋና ሥራ አስፈፃሚ ፍሬሕይወት ታምሩ ተናግረዋል።

ቴሌ-ብር የስማርት ስልክ ባለቤት ለሆኑ 23 ሚሊዮን ኢትዮጵያውያን በመተግበሪያ አማካኝነት የሚቀርብ ግልጋሎት ነው። የቅንጡ ስልክ ባለቤት ያልሆኑ የአገሪቱ ዜጎች አጭር የጽሁፍ መልዕክትን በመጠቀም ግልጋሎቱን ማግኘት ይችላሉ። ግልጋሎቱን የሚሹ መተግበሪያውን ወደ እጅ ስልኮቻቸው በመጫን፣ በአጭር የጽሁፍ መልዕክት አማካኝነት ወይም ፈቃድ ከተሰጠው ወኪል ዘንድ በመቅረብ መመዝገብ ይችላሉ። ለምዝገባ ደንበኞች፣ ወኪሎች፣ ነጋዴዎች እና ተቋማት ማማላት የሚገቧቸው የተለያዩ መስፈርቶች እንዳሉ ኢትዮ-ቴሌኮም በድረ-ገጹ ያሰፈረው መረጃ ይጠቁማል።

ኢትዮ-ቴሌኮም ከብሔራዊ ባንክ የተሰጠው ፈቃድ "ገንዘብ ለማስተላለፍ እና ለግብይት" ብቻ መሆኑን የተናገሩት ዋና ሥራ አስፈፃሚዋ ፍሬሕይወት ታምሩ ቴሌ-ብር የኢንተርኔት ግልጋሎት ባይኖር እንኳ ገንዘብ የመላክ፣ ለመቀበል እና ክፍያ ለመፈጸም የሚያስችል ሥራ እንደሚያከናውን አስረድተዋል።

በተንቀሳቃሽ ስልኮች አማካኝነት ገንዘብ የማንቀሳቀስ እና ክፍያ የመፈጸም ግልጋሎት በማቅረብ ስድስት የብድር እና ቁጠባ ተቋማትን ያካተተው እና 1.9 ሚሊዮን ገደማ ደንበኞች ያሉት ኤም-ብር ቀዳሚው ነው። እንዲህ አይነት ዘመን አመጣሽ ግልጋሎቶች ዘግይተው ለኢትዮጵያ ገበያ ቢደርሱም አስራ ዘጠኙ ባንኮች ላልደረሱት እና ከፋይናንስ ሥርዓት ለራቀው የማኅበረሰብ ክፍል ኹነኛ ዘዴ እንደሆነ በኢንተርኔት ሶሳይቲ የአፍሪካ ቀጠና ምክትል ፕሬዝዳንት ዶክተር ዳዊት በቀለን የመሳሰሉ ባለሙያዎች ያምናሉ።

ዶክተር ዳዊት በቀለ "አብዛኛው የኢትዮጵያ ሕዝብ የባንክ ሥርዓቱ ውስጥ የለም። የሞባይል ገንዘብን ተጠቅመን ለመገበያየት ትልቅ አቅም አለ። ያ ደግሞ ለንግዱ ብቻ ሳይሆን ጥቅም የሚኖረው አብዛኛው ሰው የባንክ አካውንትም ሳይኖረው የፋይናንስ አገልግሎቱ ውስጥ እንዲገባ ያደርገዋል" ሲሉ ፋይዳውን ለዶይቼ ቬለ አስረድተዋል።

ኢትዮጵያ በዚህ ረገድ ከጎረቤቷ ኬንያ እንኳ እጅግ ኋላ መቅረቷን የሚናገሩት የአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲው መምህር ዶክተር ሰለሞን አጥናፉ "እስከ ዛሬ ኤኮኖሚውን ሊያንቀሳቅስ የሚችል መሆኑ እየታወቀ እኛ አገር በፍራቻ እና በኔትወርክ ምክንያት ደፍረን አልገባንበትም" ሲሉ ይናገራሉ።

ቅንጡ ስልኮች የሚጠቀሙ የከተማ ልሒቃንንም ይሁን በገጠራማው የአገሪቱ ክፍል የሚኖሩ ዜጎችን ሊጠቅም የሚችል ግልጋሎት እንደሆነ የሚያምኑት ዶክተር ሰለሞን አጥናፉ "ተደፍሮ ከተገባበት፤ አስፈላጊው መሠረተ-ልማት ከተሟላ እስካሁን ያልተጠቀመበት ሰዉ ሊማረው የሚችል ነው። እስካሁን እየተጠቀሙ ያሉ ብዙ ሰዎች አሉ" ብለዋል።

የኢትዮ-ቴሌኮም ዋና ሥራ አስፈፃሚ ፍሬሕይወት ታምሩ በአዲሱ ቴሌ-ብር አማካኝነት ባለሙያዎቹ እንደሚወተውቱት ከፋይናንስ አገልግሎት የራቀውን ማሕበረሰብ ለመድረስ ትኩረት መሰጠቱን ደጋግመው ሲናገሩ ተደምጠዋል። የገንዘብ ሕትመትን መቀነስ፣ በጥሬ ገንዘብ ዝውውር የሚፈጠሩ የደሕንነት ሥጋቶችን መቅረፍ ከዚሁ ግልጋሎት ይገኛሉ የተባሉ ተጨማሪ ጥቅሞች ናቸው።

Äthiopien Mobiler Geldservice
በኢ-ብር አማካኝነት የትራፊክ ሕግ የተላለፉ ቅጣታቸውን ሊከፍሉ ይችላሉ። ምስል DW/M. Gerth-Niculescu

የኢትዮጵያ መንግሥት ወደ አገሪቱ ቴሌኮም ገበያ መግባት የሚሹ ፍላጎታቸውን እንዲያሳውቁ ጥሪ ሲያቀርብ ብቅ ብለው በመጨረሻው ጨረታ ሳይሳተፉ የቀሩ ኩባንያዎች ካፈገፈጉባቸው ምክንያቶች አንዱ በዚሁ ዘርፍ ለመሠማራት አለመቻላቸው ነበር። በኢትዮጵያ ገንዘብ ሚኒስቴር ከፍተኛ አማካሪ የሆኑት ዶክተር ብሩክ ታዬ ኩባንያዎቹ ካቀረቧቸው ምክንያቶች መካከል "አሁን ያለው የአገሪቱ ሕግ [የውጪ ኩባንያዎች] በሞባይል የገንዘብ አገልግሎት ለመሠማራት አይፈቅድም" የሚለው እንደሚገኝበት ለዶይቼ ቬለ አረጋግጠዋል።

ቴሌ-ብር በይፋ ሥራ መጀመሩ በተበሰረበት የዕለተ ማክሰኞ መርሐ ግብር የተገኙት ጠቅላይ ምኒስትር ዐቢይ አሕመድ በዚሁ ምክንያት ኢትዮጵያ 500 ሚሊዮን ዶላር ማጣቷን ተናግረዋል።

"ሁለት የሥራ ፈቃድ ለቴሌኮም ሲሰጥ የሞባይል ባንኪንግ አልተካተተም። ይኸ ባለመሆኑ የኢትዮጵያ መንግሥት በትንሹ 500 ሚሊዮን ዶላር አጥቷል" ያሉት ጠቅላይ ምኒስትር ዐቢይ አሕመድ "ኢትዮ-ቴሌኮም ያጣንውን 500 ሚሊዮን ዶላር የሚያካክስ ሥራ መስራት ይጠበቅበታል" ሲሉ አክለዋል።

የኢትዮ-ቴሌኮም ዋና ሥራ አስፈፃሚ ፍሬሕይወት ታምሩ "በመጀመሪያው አመት 21 ሚሊዮን ደንበኞች ይመዘገባሉ ብለን እናስባለን። ከዚህ ውስጥ 12.7 ሚሊዮን ንቁ ደንበኞች ይሆናሉ ብለን አስበናል። በመጀመሪያው አመት 710 ሚሊዮን ትራንዛክሽን በቴሌ ብር እናንቀሳቅሳለን። ይኸ ማለት ደግሞ 69.6 ቢሊዮን ብር በቴሌ ብር ይንቀሳቀሳል ብለን እናስባለን። ከአምስት አመት በኋላ 33 ሚሊዮን ደንበኞች ይኖሩናል። በአጠቃላይ 3.5 ትሪሊየን ብር ይንቀሳቀሳል ብለን ተንብየናል" ብለዋል።

ይኸ ለጋስ ግን ደግሞ እጅግ ግዙፍ ዕቅድ ነው። ውጥኑን ለማሳካት ኩባንያው በገበያው ካሉ መሰል ግልጋሎቶች ትከሻ መጋፋት ይጠበቅበታል። ወደ ኢትዮጵያ ገበያ ይገባሉ ተብለው የሚጠበቁት እና የፈረጠመ የገንዘብ፣ የቴክኖሎጂ እና የእውቀት አቅም ያላቸው ሁለት የቴሌኮም ኩባንያዎች ጠቅላይ ምኒስትር ዐቢይ አሕመድ እንዳሉት ከአንድ አመት ገደማ በኋላ በተመሳሳይ የሥራ ዘርፍ እንዲሰማሩ ከተፈቀደ ለቴሌ-ብር እና ኢትዮ-ቴሌኮም ውድድሩ ብርቱ ይሆናል።

Äthiopien Mobiler Geldservice
በኢትዮጵያ ኤም-ብር፣ ሔሎ ካሽ እና አሞሌን የመሳሰሉ ግልጋሎት አቅራቢዎች ቴሌ-ብር ትናንት ማክሰኞ ሥራ በጀመረበት ገበያ ይገኛሉ። ምስል DW/M. Gerth-Niculescu

በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ የኮምፒውተር ሳይንስ ትምህርት ክፍል መምህሩ ዶክተር ሰለሞን አጥናፉ ኢትዮ-ቴሌኮም እና መሰል ግልጋሎት የሚያቀርቡ ባንኮች ሥራዎቻቸውን ማጠናከር እንደሚገባቸው አሳስበዋል።

የቴሌ-ብር ግልጋሎት ሥራ የጀመረው ከቻይናው ሑዋዌ ኩባንያ ጋር በቅንጅት መሆኑን የኢትዮ-ቴሌኮም ዋና ሥራ አስፈፃሚ ትናንት ተናግረዋል። የቻይናዎቹ ሑዋዌ እና ዜድቲኢ ባለፉት አመታት በኢትዮጵያ የቴሌኮም መሠረተ-ልማት ግንባታ ዘርፍ ግንባር ቀደም ሚና ያላቸው ናቸው።

እሸቴ በቀለ

ኂሩት መለሰ