የኢትዮጵያ ጉዳይ በአውሮጳ ፓርላማ
ረቡዕ፣ ጥቅምት 2 2009
በአውሮጳ ኅብረት ምክር ቤት የልማት ኮሚቴ እና የሰብአዊ መብቶች ንዑስ ኮሚቴ አባላት ዛሬ በኢትዮጵያ ወቅታዊ ሁኔታ ላይ ተወያይተዋል። በውይይቱ ላይ የኢትዮጵያ መንግስት ያወጀዉን የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ በተመለከተም ተሳታፊዎች ንግግር አሰምተዋል። የፓርላማ አባላት፣ የኮሚሽኑ እና የልዩ ልዩ ድርጅቶች ተወካዮች በተካፈሉበት በዚሁ ውይይት ላይ በብራሰልስ የኢትዮጵያ ኤምባሲ ተወካዮችም ተገኝተዋል ።በውይይቱ ላይ የፓርላማ አባላት የሰብዓዊ መብት አያያዝ ችግር አለበት ባሉት በኢትዮጵያ መንግሥት ላይ ኮሚሽኑ ለዘብተኛ አቋም ይከተላል ሲሉ ወቅሰዋል ። የአውሮጳ ምክር ቤት አባል የኾኑት ወ/ሮ አና ጎሜሽ በኢሬቻ በአል ላይ የደረሰዉን ጭፍጨፋን ጨምሮ በሀገሪቱ የሚከናወነውን ጭቆና የሚከታተል ገለልተኛ አጣሪ ቡድን ሊኖር ይገባል ብለዋል። ኢንተርኔትን እና ሚዲያን የሚገድበው የአስቸኳይ ጊዜ አዋጁ እንዲነሳም ጠይቀዋል። የፖለቲካ እስረኞች እንዲፈቱ ጥሪ በማስተላለፍ እስሩ አሁንም እንደቀጠለ ነው ያሉት ወ/ሮ አና ጎሜሽ የአውሮጳ ኅብረት ጠንካራ ርምጃ ባለመውሰዱ ወቅሰዋል። የጀርመን መራኂተ-መንግሥት አንጌላ ሜርክል የኢትዮጵያ ጉብኝትንም አጥብቀው ተችተዋል።
«ሌላው ቢቀር ትናንት ወ/ሮ ሜርክል የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ ተደንግጎም ሀገሪቱን መጎብኘታቸው የሁላችንም የጋራ ሐፍረት ነው።»
በስብሰባው ላይ የኢትዮጵያ መንግሥትን ወክለው የተናገሩት በቤልጂግ የኢትዮጵያ አምባሳደር የፖለቲካ እና ዲፕሎማሲ አማካሪ አቶ ዮሐንስ አብራኃ በበኩላቸው ከ80 ብሔሮች በላይ ባላት ሀገር ዲሞክራሲን ተግባራዊ ከማድረግ ውጪ ሌላ የተሻለ አማራጭ የለንም ሲሉ ተናግረዋል።
«ክብርት ሊቀ መንበር፣ እንዲሁም ክቡራን እኛ ዲሞክራሲን ኢትዮጵያ ውስጥ ተግባራዊ እያደረግን ነው ብለን እናምናለን። ይኼን የምናደርገውም ሌሎችን ለማስደሰት ሳይሆን፤ የምናደርገው ሕዝባችን እና ሀገራችን ስለሚፈልጉት ነው።»
አምባሳደሩ በስብሰባው ላይ በኦሮምያ የዘረኝነት ችግር አለ መባሉን እንዳስተባበሉ ውይይቱን የተከታተለው የብራሰልሱ ወኪላችን ገበያው ንጉሴ ዘግቧል ።
ገበያው ንጉሴ
ማንተጋፍቶት ስለሺ
ኂሩት መለሰ
ነጋሽ መሀመድ