የኢትዮጵያ የንግድ ሕግ ማሻሻያ
ረቡዕ፣ ኅዳር 23 2013አሁን በሥራ ላይ የሚገኘው የንግድ ሕግ በአምስት መፃሕፍት የተዘጋጀ ነው። የመጀመሪያው "ስለ ነጋዴዎች እና ንግድ መደብሮች" የተዘጋጁ ሕግጋትን ይዟል። ሁለተኛ መጽሐፍ የንግድ ማኅበሮችን፤ ሶስተኛ መጽሐፍ ስለ ማጓጓዝ (ማመላለስ) ሥራ እና ስለ ኢንሹራንስ፣ አራተኛ መጽሐፍ የሚተላለፉ የገንዘብ ሰነዶችና የባናክ ሥራዎች ሕግ፣ አምስተኛው መጽሐፍ የኪሣራና የመጠበቂያ ስምምነትን የተመለከቱ ናቸው። በ1952 ዓ.ም. በነጋሪት ጋዜጣ ታትሞ ሥራ ላይ የዋለው ይኸው ግዙፍ የሕግ መጽሐፍ በአጠቃላይ 346 ገፆችን የያዘ ነው።
ለአመታት የዘለቀው ሕጉን የማሻሻል ሙከራ ተሳክቶ ባለፈው መስከረም ወር ረቂቁ ለሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ቀርቧል። በወቅቱ የመንግሥት ተጠሪ አምባሳደር መስፍን ቸርነት "አሁን በስራ ላይ ያለው የንግድ ሕጋችን ለሁለት ተከፍሎ የንግድ እና የፋይናንስ ኮድ በሚል ሁለት ራሳቸውን የቻሉ መድብሎች እንዲወጡ ተደርጓል። የንግድ ሕጉ በተለያዩ ጊዜ ከወጡ ሕጎች ጋር የተጣጣመ፤ ተመጋጋቢ እና አላስፈላጊ ድግግሞሽ የሌለው እንዲሆን ተደርጓል።" ሲሉ ተናግረዋል።
"ለነጋዴ የተሰጠው ትርጓሜ፤ ነጋዴዎች የሚሳተፉባቸው የንግድ ሥራዎች ዘርዝሮ ከማብቃት ይልቅ አዳዲስ፣ ከዘመኑ ጋር የተከሰቱ ወይም ሊከሰቱ የሚችሉ የንግድ ሥራዎችን በመጨመር እንዲካተት ተደርጓል። በነባሩ ሕግ እንደ ነጋዴ የማይቆጠሩ የእርሻ ሥራ፣ የደን ልማት ሥራ፣ ከብት ማርባት ሥራን የሚሰሩ፣ የእርሻ ሰብላቸውን ወይም የከብታቸውን ርቢ የሚሸጡ እንዲሁም አሳ አጥማጆች እና አርቢዎችን እንደ ነጋዴዎች እንዲቆጠሩ ተደርጓል።" ሲሉም አክለዋል።
ባለፈው ሳምንት በንግድ ሕግ ረቂቁ ላይ የተለያዩ ባለሙያዎች የተሳተፉበት ውይይት በኢንተርኔት አማካኝነት ተካሒዶ ነበር። ውይይቱን ያዘጋጀው በኢትዮጵያ ኢንቨስትመንት ኮሚሽን ሥር የሚገኘው ቢዝነስ ነጋሪት የተባለ ድረ-ገጽ ነው። በዚህ ውይይት በረቂቁ ዝግጅት የተሳተፉት ዶክተር ስዩም ዮሐንስ በርካታ መሻሻያዎች መደረጋቸውን ተናግረዋል።
ዶክተር ስዩም እንዳሉት የንግድ ሕጉ ረቂቅ ባለሙያዎች በሽርክና ማኅበር እንዲያቋቁሙ ይፈቅዳል። ከዚህ በተጨማሪ አንድ ግለሰብ ብቻውን ኃላፊነቱ የተወሰነ የግል ማኅበር እንዲያቋቁም ይኸው የሕግ ረቂቅ ዕድል ሰጥቷል።
በንግድ ሕግ ረቂቁ የተደረጉ ማሻሻያዎች በርካታ ናቸው። ይኸ የሕግ ረቂቅ በአጠቃላይ በኢትዮጵያ የንግድ አሰራርም ይሁን ኢትዮጵያ እንደ የዓለም የንግድ ድርጅት ባሉ ተቋማት አባል ለመሆን ለምታደርገው ጥረት ከፍ ያለ ፋይዳ ይኖረዋል ተብሎ ይጠበቃል።
ሙሉ ዘገባውን ለማድመጥ የድምጽ ማዕቀፉን ይጫኑ
እሸቴ በቀለ
ነጋሽ መሐመድ