1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

የኢትዮጵያ ቀይ መስቀል ማሕበር ያቀረበው ጥሪ

ሐሙስ፣ ነሐሴ 4 2015

የኢትዮጵያ ቀይ መስቀል ማሕበር «በአማራ ክልል የተከሰተውን ግጭት ተከትሎ የተፈጠረውን ሰብዓዊ ቀውስ ለመቋቋም በጋራ መቆም ያስፈልጋል» ሲል የሰብዓዊ ድጋፍ ጥሪ አቀረበ። የቁሳቁስ፣ የምግብና የደም ድጋፍ ጠይቋል። ደረሰ ስላለው የሰብዓዊ ቀውስ ሁኔታ ግን በአካባቢው ሠራተኞቹ መንቀሳቀስ ባለመቻላቸው ዝርዝር መረጃ ማግኘት አለመቻሉን አመልክቷል።

https://p.dw.com/p/4V0rt
Äthiopien Addis Abeba | Büro Äthiopisches Rotes Kreuz
የኢትዮጵያ ቀይ መስቀል ማኅበር ብሔራዊ ጽሕፈት ቤት ምስል Solomon Muchie/DW

የቀይ መስቀል መግለጫ

የኢትዮጵያ ቀይ መስቀል ማሕበር በአማራ ክልል የተከሰተውን ግጭት ተከትሎ «የተፈጠረውን ሰብዓዊ ቀውስ ለመቋቋም በጋራ መቆም ያስፈልጋል» ሲል የሰብዓዊ ድጋፍ ጥሪ አቀረበ። በግጭቱ ምክንያት «በርካታ ዜጎች ለተለያዩ ሰብዓዊ ችግሮች ተጋልጠዋል» ያለው ማሕበሩ ሠራተኞቹ ፣ ቁስለኛና ታካሚ አመላላሽ አምቡላንሶች እና በጎ ፈቃደኞች በሚንቀሳቀሱበት ወቅት ተገቢ ትብብር እንዲደረግላቸውም ጠይቋል።

የኢትዮጵያ ሲቪል ማኅበረሰብ ድርጅቶች ምክር ቤት በበኩሉ በአማራ ክልል የተከሰተው ግጭት በአብዛኛው ሕዝብ ተሰባስቦ በሚኖርባቸው ከተሞች የሚካሄድ፣ የንጹሐንን ሕይወት እየቀጠፈ የሚገኝ፣ የዜጎችን መሠረታዊ መብቶች የገደበ፣ ከፍተኛ ማኅበራዊ እና ሰብዓዊ ቀውስ ያስከተለ መሆኑን በመግለጽ ሰላማዊ እና ዘላቂ መፍትሔ እንዲፈለግ ጠይቋል። 

የኢትዮጵያ ቀይ መስቀል ማሕበር በአማራ ክልል በዜጎች ላይ ለተከሰተው ጉዳት ከፍተኛ ድጋፍ እንዲደረግለት ጠይቋል። የቁሳቁስ ፣ የምግብ እና የደም ድጋፍ ጠይቋል። ደረሰ ስላለው የሰብዓዊ ቀውስ ሁኔታ ግን በአካባቢው የሚሠሩት ሠራተኞቹ መንቀሳቀስ ባለመቻላቸው ዝርዝር መረጃ ማግኘት አለመቻሉን አመልክቷል። ለቁስለኞች የሚሆኑ የህክምና ቁሳቁሶች እንደሚያስፈልጉት የገለፀው ማሕበሩ  ለሥራ ወደ ክልሉ ሄደው ያልተመለሱ ሰዎችን ለማገናኘት ጥረት እንደሚያደርግም አስታውቋል።

የኢትዮጵያ ቀይ መስቀል ማሕበር የቦርድ አባል ጌታሁን ሑሴን እና ዋና ጸሐፊ ጌታሁን ታአ
የኢትዮጵያ ቀይ መስቀል ማሕበር ኃላፊዎች በአማራ ክልል ስለሚያስፈልገው የሰብአዊ እርዳታ መግለጫ ሲሰጡምስል Solomon Muchie/DW

የአማራ ሜዲካል አሶሴሽን የተባለ ተቋም በበኩሉ «አሁን ባለው የፀጥታ ችግር ምክንያት በአማራ ክልል  የመንገድ መዘጋት ፣የህክምና ግብዓት፣ የኦክስጅን እና ደም እጥረት እየተከሰተ ነው» ሲል ትናንት ባወጣው መግለጫ አስታውቋል። «በጦርነት ምክንያት ጉዳት እየደረሰባቸው ያሉ ወገኖች ፣ እናቶች እና ሕጻናት ጭምር መሠረታዊ የህክምና አገልግሎት ማግኘት አልቻሉም» ያለው ማሕበሩ የህክምና አገልግሎት ተደራሽ እንዲሆን አስፈላጊውን ድጋፍ እንዲደረግ ጠይቋል።

«አስቸኳይ የህክምና ቁሳቁሶች መቀሌ ደርሰዋል»የዓለም ቀይ መስቀል ድርጅት

የኢትዮጵያ ቀይ መስቀል ማሕበር በአንቡላንሶች፣ በበጎ ፈቃደኞች እና በሠራተኞች ላይ ጉዳት መድረሱንም የማሕበሩ የሥራ አመራር ቦርድ ኃላፊ ኢንጂነር ጌታሁን ሁሴን ገልፀዋል። የኢትዮጵያ ሲቪል ማኅበረሰብ ድርጅቶች ምክር ቤት በአማራ ክልል የተከሰተውን የትጥቅ ግጭት በአብዛኛው ሕዝብ ተሰባስቦ በሚኖርባቸው ከተሞች የሚካሄድ፣ የንጹሐንን ሕይወት እየቀጠፈ የሚገኝ፣ የዜጎችን መሠረታዊ መብቶች የገደበ፣ የክልሉን ሰላም በእጅጉ ያወከ፣ ከፍተኛ ማኅበራዊ እና ሰብአዊ ቀውስ እያስከተለ መሆኑን መገንዘቡን በመግለጽ የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ አፈፃፀሙ ላይ ከፍተኛ ጥንቃቄ እንዲደረግ ጠይቋል።

ሰሎሞን ሙጬ 

ሸዋዬ ለገሠ

እሸቴ በቀለ