1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

የኢትዮጵያ መንግሥት የአስቸኳይ ጊዜ አዋጁን እንዲያነሳ ተጠየቀ

ማክሰኞ፣ ግንቦት 20 2016

ከሕግ ውጭ ግድያ፣ የሲቪል ሰዎች ሞት፣ የአካል ጉዳት፣ የንብረት ውድመትና ዘረፋ፣ የዘፈቀደ፣ የጅምላና የተራዘመ እሥራት፣ አስገድዶ መሰወር እንዲሁም እገታ አሳሳቢነታቸው አሁንም የቀጠሉ የመብት ጥሰቶች መሆናቸውን የኢትዮጵያ ሰብዓዊ መብቶች ኮሚሽን ገለፀ። የመብቶች እና ዴሞክራሲ ዕድገት ማዕከል መንግሥት የአስቸካይ ጊዜ አዋጁን እንዲያነሳ ጠይቋል።

https://p.dw.com/p/4gNed
 የኢትዮጵያ ሰብዓዊ መብቶች ኮሚሽን
የኢትዮጵያ ሰብዓዊ መብቶች ኮሚሽን ከሕግ ውጭ ግድያ፣ የሲቪል ሰዎች ሞት፣ የአካል ጉዳት፣ የንብረት ውድመትና ዘረፋ፣ የዘፈቀደ፣ የጅምላና የተራዘመ እሥራት፣ አስገድዶ መሰወር እንዲሁም እገታ አሳሳቢነታቸው አሁንም የቀጠሉ የመብት ጥሰቶች መሆናቸውን የኢትዮጵያ ሰብዓዊ መብቶች ኮሚሽን ገልጿል።ምስል Ethiopian Human Rights Commission

የኢትዮጵያ መንግሥት የአስቸኳይ ጊዜ አዋጁን እንዲያነሳ ተጠየቀ

ከሕግ ውጭ ግድያ፣ የሲቪል ሰዎች ሞት፣ የአካል ጉዳት፣ የንብረት ውድመትና ዘረፋ፣ የዘፈቀደ፣ የጅምላና የተራዘመ እሥራት፣ አስገድዶ መሰወር እንዲሁም እገታ አሳሳቢነታቸው አሁንም የቀጠሉ የመብት ጥሰቶች መሆናቸውን የኢትዮጵያ ሰብዓዊ መብቶች ኮሚሽን ገለፀ።

ኮሚሽኑ የደረሱ ዝርዝር የመብት ጥሰቶችን የተመለከተ ዘገባ ያወጣ ሲሆን አስቸኳይ ጊዜ አዋጁ ሥልጣንን አላግባብ ለመጠቀም እንዳይውል፤ ከሕግ ውጭ የሆኑ የጅምላ እሥሮችንና ግድያዎችንም የመሰሉ ጥሰቶችን ለመፈፀም እንዳይውል ጥንቃቄ ሊደረግ ይገባል ብሏል። በሌላ በኩል የኢትዮጵያ መንግሥት የአስቸኳይ ጊዜ አዋጁን እንዲያነሳ ተጠይቋል።

የኢትዮጵያ ፖለቲካ መዋቅራዊ መዛቦቶች እና መፍትሔያቸው

ጥሪውን ያደረገው የመብቶች እና ዴሞክራሲ ዕድገት ማዕከል መንግሥት ሐቀኛ የተጠያቂነት ሥርዓት እንዲዘረጋ እና የሲቪክ ምህዳሩን እንዲያከብር እና እንዲጠብቅም ጠይቋል።

የኢሰመኮ የምርመራ ዘገባ ውጤት እና ጥሪ

የኢትዮጵያ ሰብአዊ መብቶች ኮሚሽን በኦሮሚያ ክልል በሚንቀሳቀሱ ታጣቂ ቡድኖች እና በመንግሥት የጸጥታ ኃይሎች መካከል በሚደረጉ ውጊያዎች እና ከውጊያ ዐውድ ውጭ በሚፈጸሙ ቤላቸው ጥቃቶች ሳቢያ በሲቪል ሰዎች ላይ እየደረሰ ያለውን ሞት፣ የአካል ጉዳት፣ ዘረፋ፣ የሰዎች እገታ እና መፈናቀል መፍትሔ ለመስጠት የፌዴራል መንግሥት አፋጣኝ እርምጃ እና ተጨባጭ ዘላቂ መፍትሔ መስጠት የሚገባው መሆኑን፣ በተመሳሳይ በአማራ ክልል በቀጠለው የትጥቅ ግጭት ዐውድ ውስጥ ለሚፈጸሙ ከሕግ ውጭ ግድያ፣ የዘፈቀደ እስር፣ እገታ፣ አስገድዶ መሰወር፣ ሲቪል ሰዎችን የማይለዩ የከባድ መሣሪያና የአየር ጥቃቶች፣ የአካል ጉዳት እና የንብረት ውድመት ዘላቂ እልባት ለመስጠት ሰላማዊ መፍትሔ ማፈላለግን ጨምሮ፣ በሲቪል ሰዎች ላይ የሚደርሱ ጉዳቶችን ለመከላከል የሚያግዙ አፋጣኝ እርምጃዎች እንዲወሰዱ ሲጠይቅ መቆየቱን አስታውቋል። 

የመብቶች እና ዴሞክራሲ ዕድገት ማዕከል የሰላም ጥሪን የሚያሳይ ምስል
የአስቸኳይ ጊዜ አዋጁ እንዲነሳ የጠየቀው የመብቶች እና ዴሞክራሲ ዕድገት ማዕከል ከዚህ ቀደም በኢትዮጵያ ሰላም እንዲሰፍን ጥሪ ሲያቀርብ ቆይቷል።ምስል CARD

ኮሚሽኑ በአሁኑ ዘገባው በእለት፣ በቦታ፣ በደረሰው የሰብዓዊ መብት ጥሰት አይነት እና የጥሰቶች አፈፃፀም ሁኔታን በዝርዝር አመልክቷል። ኮሚሽኑ እጅግ አሳሳቢ ሆነው የቀጠሉ ያላቸውን የሰብአዊ መብቶች ጥሰቶች በኮሚሽኑ የሰብዓዊ መብቶች ክትትል እና ምርመራ ሥራ ክፍል ከፍተኛ ዳይሬክተር ዶክተር ሚዛኔ አባተ ዘርዝረዋል።

ከሕግ ውጭ ግድያ፣ የሲቪል ሰዎች ሞት፣ የአካል ጉዳት፣ የንብረት ውድመትና ዘረፋ

ኮሚሽኑ ባወጣው ዘገባ በአማራ ክልል በተለያዩ ዞኖች በመንግሥት የጸጥታ ኃይሎች እና በታጣቂዎች መካከል የተካሄዱ የትጥቅ ግጭቶችን ተከትሎ የድሮን ጥቃቶችን ጨምሮ በሲቪል ሰዎች ላይ ሞትና ከፍተኛ ጉዳቶች መድረሳቸውን አመልክቷል።

 የሰብዓዊ መብት ጥሰት በኦሮሚያ ክልል

በተመሳሳይ በኦሮሚያ ክልል በመንግሥት የፀጥታ አካላት የድሮን ጥቃትን ጨምሮ ሌሎች ጥቃቶች መፈፀማቸውን፣ የኦሮሞ ነጻነት ሰራዊት አባላት ወይም የኦነግ ሸኔ ታጣቂዎች በሚያደርሱት ጥቃትም የከፋ የሰብዓዊ መብት ጥሰት መድረሱ አመልክቷል።

የኢትዮጵያ ሰብአዊ መብቶች ኮሚሽን ዋና መሥሪያ ቤት
የኢትዮጵያ ሰብአዊ መብቶች ኮሚሽን ባወጣው ዘገባ በአማራ ክልል በተለያዩ ዞኖች በመንግሥት የጸጥታ ኃይሎች እና በታጣቂዎች መካከል የተካሄዱ የትጥቅ ግጭቶችን ተከትሎ የድሮን ጥቃቶችን ጨምሮ በሲቪል ሰዎች ላይ ሞትና ከፍተኛ ጉዳቶች መድረሳቸውን አመልክቷል። ምስል Solomon Muchie/DW

የዘፈቀደ፣ ሕገወጥ፣ የጅምላና የተራዘመ እስራትና የተፋጠነ ፍትሕ እጦት 

የአስቸኳይ ጊዜ አዋጁን ተከትሎ በአዋሽ አርባ፣ በአዲስ አበባ ፌዴራል ፖሊስ ወንጀል ምርመራ ቢሮ፣ በአዲስ አበባ ፖሊስ ኮሚሽን 3ኛ ፖሊስ ጣቢያ፤ በአማራ ክልል በባሕር ዳር፣ ሸዋሮቢት፣ ኮምቦልቻና ጎንደር በሚገኙ የኮማንድ ፖስቱ ማቆያ ስፍራዎች እና በሌሎች የሀገሪቱ ክፍሎች በርካቶች ለተራዘመና የዘፈቀደ እስራት ተዳርገዋል ያለው ኢሰመኮ በአስቸኳይ ጊዜ አዋጁ አማካኝነት በቁጥጥር ሥር ከዋሉ ሰዎች ውስጥ ለተለያዩ የጤና ችግሮች የተጋለጡ መኖራቸውን፣ የተወሰኑትም ከሥራቸው የተሰናበቱ መሆኑን እና ቤተሰቦቻቸው ለከፍተኛ ጭንቀት የተዳረጉ መሆኑን  ለመረዳት መቻሉን ኃላፊው አብራራርተል።

የአስቸኳይ ጊዜ አዋጁ እንዲነሳ መጠየቁ

በሌላ በኩል የኢትዮጵያ መንግሥት የአስቸካይ ጊዜ አዋጁን እንዲያነሳ ተጠይቋል። ይህንን ጥሪ ያደረገው የመብቶች እና ዴሞክራሲ ዕድገት ማዕከል መንግሥት ሐቀኛ የተጠያቂነት ሥርዓት እንዲዘረጋ እና የሲቪክ ምህዳሩን እንዲያከብር እና እንዲጠብቅም ጠይቋል። 

"በኢትዮጵያ እንደ አዲስ እየተባባሱ የመጡ" ያላቸው የሲቪክ ምህዳሩን የሚያጣብቡ ድርጊቶች በእጅጉ አሳስቦኛል" ያለው ካርድ የፀጥታ እና የደህንነት አካላት የሰብዓዊ መብቶች ጥሰቶችን ምርመራ የሚሠሩ የሲቪል ማህበረሰብ ድርጅቶችን እያዋከቡ መሆኑን ጠቅሷል።

 በአማራ ክልል ንፁሐን በድሮን ድብደባ ተገድለዋል - ኢሰመኮ

ይሄው ድርጅት "አደገኛ እና ሕገ መንግሥታዊ መብቶችን የሚጋፉ" ያላቸውና በትያትር ባለሙያዎች፣ በኪነ ጥበብ ሥራዎች እና በጋዜጠኞች ላይ የሚደርሱ መብትን የሚጋፉ ድርጊቶች ተቀባይነት የሌላቸው' መሆናቸውንም ገልጿል። 

ኢሰመኮ በሰጠው ምክረ ሀሳብ ከጦርነቱ ጋር በተገናኘ "የሰላም አማራጮች ቅድሚያ እንዲሰጣቸው መክሯል" ያሉት ዶክተር ሚዛኔ አባተ የግጭት ተሳታፊ ወገኖችም አለም አቀፍ ሕጎችን እንዲያከብሩ እና በንፁሃን ላይ ጉዳት እንዳይደርስ ጥንቃቄ እንዲያደርጉ ጠይቋል ብለዋል። 

ሰለሞን ሙጬ

አዜብ ታደሰ

እሸቴ በቀለ