1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

የአፍሪቃ የብድር እፎይታን አራዛሚ ቻይና ወይንስ አሜሪካ?

ቅዳሜ፣ ጥቅምት 3 2016

የእዳ እፎይታ በአዳጊ ሃገራት ላይ የሚፈጥረው ሰቆቃ በመጠኑም ቢሆን እየቀነሰ ይመስላል ። ዓለም በጉዳዩ አፋጣኝ ምላሽ እንዳይሰጥ ቻይና እንቅፋት ተደርጋ ተወስዳለች ። ቻይና በበኩሏ ጣታችሁን ከመቀሰራችሁ በፊት ምን አደረጋችሁ ስትል በአሜሪካ የሚደገፉ ምዕራባውያን ተቋማትን ሞግታለች ። ድሆች በመላው ዓለም በችግር ይማቅቃሉ ።

https://p.dw.com/p/4XWJ4
አንድ ሰው ለእኔ ቢጤ አዛውንት ሊመጸውት ሲዘጋጅ
በአዲስ አበባ ከተማ ተክለ ኃይማኖት ቤተ ክርስቲያን አቅራቢያ አንድ ሰው ለእኔ ቢጤ አዛውንት ሊመጸውት ሲዘጋጅ፦ ፎቶ ከማኅደርምስል Marco Longari/AFP

በአዳጊ ሃገራት እዳ ጉዳይ ኃያላኑ ጣት ይቀሳሰራሉ

በዩክሬን ጦርነት፤ በኮቪድ 19፤ በከባቢ አየር ለውጥ እና በሌሎች መሰል ቀውሶች በብርቱ የተመቱ በአብዛኛው የአፍሪቃ  አዳጊ ሃገራት የውጭ እዳ ጫና ምጣኔ ሐብታቸውን አንቆ እንደያዘባቸው ይነገራል ። የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት (ተመድ) ባወጣው መረጃ መሰረት፦ በአሁኑ ወቅት 3,3 ቢሊዮን የዓለማችን ነዋሪዎች የሚኖሩት ወጪያቸውን በትምህርት እና ጤና ላይ ሳይሆን በእዳ ክፍያ ላይ በሚያውሉ ሃገራት ውስጥ ነው ። 

የምግብ ዋጋ መናር እና የኃይል አቅርቦት ክፍያ ተደምሮም ሃገራቱ የገንዘብ አኩፋዳቸው እየተሟጠጠ  ነው ። የብድር ወለድ መጠኑ እየጨመረ ባለበት በአሁኑ ወቅት ዩናይትድ ስቴትስ እና ሌሎች ሃገራት መንግሥታት ብድራቸውን እንዲከፍሏቸው ጫና እያሳደሩ ነው ። ወትሮ ለብድር እጃቸው ፈጥኖ ይዘረጋ የነበሩት እንደ ዩናይትድ ስቴትስ እና ቻይናን የመሳሰሉ ዋነኛ አበዳሪዎች አሁን እጆቻቸውን እየሰበሰቡ ነው ። ሁኔታው በተለይ አዳጊ ሃገራትን ብርቱ አጣብቂኝ ውስጥ ከቷቸዋል ። ጉይሎም ሻቤር በዓለም አቀፉ የገንዘብ ተቋም (IMF) የሥልታዊ እና ደምብ ቃኚ ክፍል ምክትል ኃላፊ ናቸው ። በተለይ እንደ ጎርጎሪዮስ አቆጣጠር ከ2020 እስከ 2022 ባሉት ጊዜያት በዓለም ዙሪያ የተከሰቱ ዐበይት ሁነቶች በብድር እፎይታ ሒደቱ ላይ ብርቱ ተግዳሮት መፍጠሩን አብራርተዋል ። «ምክንያቱም» ይላሉ ጉይሎም ።የኢትዮጵያ የውጭ ብድር የመክፈል አቅም ምዘና

የቻይና እና የምዕራባውያን ጣት ቅሰራ

«ምክንያቱም የዜሮ ድምር ጨዋታ በመሆኑ ነው ። ተበዳሪዎች ከእዳ ጫናቸው እፎይታን ይሻሉ ። አበዳሪዎች ደግሞ ብዙ  ገቢ ያጡበት ወቅት ነው ። በዚህ ሁኔታ ውስጥ ስለ ይፋዊ አበዳሪዎች ስንናገር  ስለ ግብር ከፋዮች ገንዘብ ነው ። ስለዚህ እንደ ጀርመን፤ ፈረንሳይ፣ ዩናይትድ ስቴትስ፣ ጃፓን፣ ቻይና፣ ሣዑዲ ዓረቢያ፣ ህንድን የመሳሰሉ ሃገራት በእርግጥም የሚያደርጉት ስምምነት የግብር ከፋዮቻቸውን ጥቅም ያስጠበቀ ስለመሆኑ እርግጠኛ መሆን አለባቸው ። »

ማሕደረ ዜና፣ የቻይናና የአሜሪካኖች ሽኩቻ

ባለፉት ጥቂት ዓመታት ዛምቢያ እና ሲሪላንካን ጨምሮ የዓለማችን 10 ሃገራት ብድራቸውን ፈጽሞ መክፈል ወደማይችሉበት ደረጃ ደርሰዋል።  ኢትዮጵያ፤ ግብጽ፤ ኬንያ፤ ጋና፤ ዩክሬን እና ፓኪስታንን ጨምሮ ደግሞ 50 ሃገራት ብድር ለመክፈል እጅግ አስቸጋሪ ሁኔታ ውስጥ እየገቡ መሆኑ ተገልጿል ።  

ዓለምአቀፉ የገንዘብ ተቋም (IMF) የዓለም ባንክ  እንዲሁም  የፓሪስ ቡድን የተሰኙ አበዳሪዎች በተለይ እንደ ቻይና፤ ህንድ እና የገልፍ ሃገራትን ከመሳሰሉ አዳዲስ አበዳሪዎች ጋ ፉክክር ውስጥ በገቡበት በአሁኑ ወቅት አበዳሪዎች የሚሰርዙት ማንኛውም ብድር እጅግ በጥንቃቄ የተሞላ እና ዘገምተኛ ነው ።

 የዓለማችን 10 ሃገራት ብድራቸውን ፈጽሞ መክፈል ወደማይችሉበት ደረጃ ደርሰዋል። 
ባለፉት ጥቂት ዓመታት ዛምቢያ እና ሲሪላንካን ጨምሮ የዓለማችን 10 ሃገራት ብድራቸውን ፈጽሞ መክፈል ወደማይችሉበት ደረጃ ደርሰዋል። 

ከግማሽ ምእተ ዓመት ወዲህ (ጎርጎሪዮሱ 1973 ወዲህ) ዓለምአቀፉ የገንዘብ ተቋም (IMF) እና የዓለም ባንክ ለመጀመሪያ ጊዜ በአፍሪቃ ምድር ትናንት ባደረጉት ዓመታዊ ጉባኤያቸው የዓለም መሪዎች ደሐ ሃገራትን እንዲረዱ ተማጽነዋል ። ማራካሽ ሞሮኮ ውስጥ ዐርብ፤ ጥቅምት 2 ቀን፣ 2016 ዓ.ም ዓመታዊ ጉባኤያቸውን ሲያካሂዱም በከፍተኛ ደረጃ አሳሳቢ የሆነው የአዳጊ ሃገራት በእዳ የመዘፈቅ ሁኔታ እና የእዳ ስረዛ መንገዶች  ዋነኛ የመነጋገሪያ አጀንዳቸው ነበሩ ። ሃገራት በተለያዩ የዓለማችን ክፍሎች ካላቸው የፖለቲካ ጥቅም እና ፍላጎት አንጻር የእዳ ስረዛው ጉዳይ ብርቱ ተግዳሮት እንደሚገጥመው በዓለም አቀፍ ልማት ማእከል አጥኚው ክሌሞን ላንደር ቀደም ብለው ለዶይቸ ቬለ (DW) ተናግረዋል ።

ብሪክስ ጉባኤ፦ በአፍሪቃ እንዴት ይታያል?

«እጅግ ተስፋ አስቆራጭ ጊዜ ነው ምክንያቱም ከቴክኒክ እና ደንብ አንጻር ለነዚህ ሃገራት የብድር ስረዛ መንገዱ በጣም ግልፅ ነውና ። ሆኖም በእውነቱ አካባቢን መሰረት ያደረገው የፖለቲካ ምልከታ የእዳ ስረዛን እጅግ አስቸጋሪ በማድረግ ትልቁ ችግር ሆኖ  ነው ያለው ።»

የእዳ ቀውሱ በጊዜ አፋጣኝ ምላሽ ካልተሰጠው ዳፋው ለአበዳሪ ሐብታም ሃገራትም መትረፉ አይቀርም ። ምክንያቱም በበድር በተዘፈቁ ደሐ ሃገራቱ የሚከሰተው ምስቅልቅል ሁናቴ ነዋሪዎች የተሻለ ኑሮ ፍለጋ ወ ውጪ እንዲፈናቀሉ ያደርጋልና ። ያም ብቻ አይደልም ።  ሃገራት ወደ ውጪ የሚልኳቸው ቁሶችም በከፍተኛ ሁኔታ መቀነሳቸው አይቀርም ። 

የቻይና በዓለም ፖለቲካ ከፍ ማለት የእዳ ስረዛ ጥረቱን አወሳስቦታል

ለወትሮ የእዳ ስረዛ ጥረት የሚመራው የፓሪስ ቡድን በሚባሉ የበለጸጉ ሃገራት ነበር ። ይሁንና የቻይና ዋነኛዋ የደሐ ሃገራት ብቸኛ አበዳሪ እየሆነች መምጣት የእዳ ስረዛ ጥረቶችን ሲበዛ ውስብስብ አድርጓል ።  

ቻይና በአወዛጋቢው «ቀበቶ እና መንገድ ተነሳሽነት» (Belt and Road Initiative) በተሰኘው ግዙፍ የመሰረተ-ልማት ፕሮጄክቷ ስር ከአንድ ትሪሊዮን ዶላር በላይ በከፍተኛ ወለድ አብዛኛውን ጊዜም ግልጽ ባልሆነ መንገድ ማበደሯን ይፋ አድርጋለች ።  አብዛኞቹ ብድሮችም መጨረሻቸው የሚያስከፋ ሆኗል ። እንደ ጎርጎሪዮስ አቆጣጠር በ2010 ቻይና በውጭ ሃገራት ካበደረችው ውስጥ 1 በመቶ ብቻ ነው የተበዳሪ ሃገራትን የገንዘብ ችግር መቅረፍ የቻለው ። ዛሬ ያ ቁጥር ወደ 60 ከመቶ ከፍ ማለቱን በጉዳዩ ላይ ጥናት ያደረጉት ዩናይትድ ስቴትስ ቨርጂኒያ ውስጥ በሚገኘው የዊሊያም እና ሚሪያም ዩኒቨርሲቲ ተመራማሪው ብራድ ፓርክስ ተናግረዋል ። ያም በመሆኑ የእዳ ቅነሳ ወይንም እፎይታ ላይ የቻይና ሚና በአሁኑ ወቅት ከፍተኛ ሆኗል ። ስለዚህም ችግሩን ለረዥም ጊዜ ለመቅረፍ ቻይናን ያካተተ አዲስ እና ለየት ያለ የፓሪስ ቡድን አይነት ስብስብ አስፈላጊ መሆኑን ክሌሞን ላንደር ያሰምሩበታል ። ሆኖም አሁን ካለው የፓሪስ ቡድን አይነት ግን ለየት ያለ መሆን አለበትም ይላሉ ።

የዩናይትድ ስቴትስ ብላክ ሮክ የተሰኘው ባንክ
የዩናይትድ ስቴትስ ብላክ ሮክ የተሰኘው ባንክ በኒው ዮርክ ከተማምስል picture-alliance/dpa/BlackRock

«ሆኖም ቻይና በቡድኑ ውስጥ እንደ አንድ ቁልፍ የሆነ ውሳኔ ሰጪ አካል ሆና በምትገኝበት ሁኔታ ቡድኑ ከፓሪስ ቡድን እጅግ ለየት ያለ አይነት መሆን አለበት ። »

እንዲያም ቢሆን ግን፦ ቻይና የምትሰጠው ብድር ምሥጢራዊነትም የእዳ ጫናን በመቀነሱ ሒደት ላይ ሌላኛው ተግዳሮት ነው ። የግል የቦንድ ባለቤቶችን ጨምሮ የቻይና ያልሆኑ አበዳሪዎች በእዳ ቅነሳ ሒደቱ ላይ በሙሉ ልብ ሊገቡበት የማይፈልጉትም በዚህ ምሥጢራዊ የቻይና ብድር አሰጣጥ ነው ። ምክንያቱም አዳጊ ሃገራት ከቻይና ሲበደሩ በምን አይነት ቅድመ ሁናቴ ከቻይና አበዳሪዎች ብድሩ እንደተገኘ እነዚህ አበዳሪዎች መረጃ ከሌላቸው የቻይና አበዳሪዎች በተሻለ ተጠቃሚ ሊሆኑ ይችላሉ ሲሉም ሥጋታቸውን ይገልጻሉ ።  ቻይናበእርግጥም ዋነኛ አበዳሪ እንደመሆኗ መጠን ለአዳጊ ሃገራት የሰጠችው ብድር ክፍያ ቅድሚያ እንዲሰጠው ትሻለች ። ያ ደግሞ ሌሎች አበዳሪዎች ክፍያቸው እንዲገፋ ያደርጋል ። የዊሊያም እና ሚሪያም ዩኒቨርሲቲ ተመራማሪው ብራድ ፓርክስ በዚህ ሁኔታም ጉዳዩ ለዓመታት ሊራዘም ይችላል ሲሉም ስጋታቸውን ገልጸዋል። 

በአሜሪካ የሚደገፉ የገንዘብ ተቋማትም የእዳ ስረዛ ልይ ሊሳተፉ ይገባል

ቻይና የእዳ ስረዛ ሒደት ላይ ዋነና ደንቃራ ተደርጋ መወሰዷን አትቀበልም ። በሀገሪቱ መንግሥት የሚደገፈው «ዓለም አቀፍ ጊዜ» (Global Times) የተባለው ጋዜጣ፦«እንዲህ ያለ ክፋት የተሞላበት ስም ማጠልሸት በግልጽ ትርኪ ምርኪ ነው » ሲል አስነብቧል ። ቻይና በምትሰጠው ብድር ላይ ጸጉር ስንጠቃ ከተጀመ እንደውም ዓለምአቀፉ የገንዘብ ተቋም (IMF) እና የዓለም ባንክም ካበደሩት የተወሰነውን ሊሰርዙ ይገባል ብላለች ።  በሁለቱ ዓለም አቀፍ አበዳሪ ተቋማት ውስጥ ዩናይትድ ስቴትስ ከፍተኛ ድርሻ አላት ።

የእዳ ጫና ባጎበጣት በአፍሪቃ ርዳታ ፈላጊዎች
በርካታ ሃገራት ወለድ መክፈል አለያም ህዝቸውን መንከባከቡ ላይ መወሰን ይጠበቅባቸዋል ። ምስል picture-alliance/dpa

ሞሮኮ ማራካሽ ከተማ ውስጥ ትናንት በነበረው የዓለም አቀፍ የገንዘብ ተቋማቱ በአፍሪቃ የመጀመሪያ ስብሰባ ከኮኮቪድ ወረርሺን በኋላ ሙሉ ለሙሉ ብድር መክፈል የተሳናት የመጀመሪያዋ አፍሪቃዊት ሀገር ዛምቢያ የረዥም ጊዜ የእዳ እፎይታ ስምምነት ከአይ ኤም ኤፍ ጋር መፈረሟ ተገልጿል። ይህ በእንዲህ እንዳለ የዓለም ባንክ ከዓለማችን ድሕነትን ለማስወገድ ከዘጠኝ ዓለም አቀፍ ግዙፍ የልማት ባንኮች ጋር ትብብሩን ለማጠናከር ቁርጠኛ መሆኑን ዐሳውቋል ። ዓለም አቀፍ ግዙፍ  የገንዘብ ተቋማቱም ሆኑ ቻይና በብድር ጫና ለጎበጡ አዳጊ ሃገራት አሁንም ቢሆን አፋጣኝ መፍትኄ ሊፈልጉ ያሻል ።

ማንተጋፍቶት ስለሺ/አሹቶሽ ፓንዴይ

እሸቴ በቀለ