1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

የአፍሪቃ ወታደራዊ ወጪ እና የሲፕሪ ዘገባ

ማክሰኞ፣ ኅዳር 11 2011

ዋና ጽህፈት ቤቱ ስቶክሆልም ስዊድን የሚገኘው ዓለም  አቀፍ የሰላምና ፀጥታ ተቋም፣ በምህፃሩ ሲፕሪ ከሰሀራ በስተደቡብ ስለሚገኙ አፍሪቃውያት ሀገራት ወታደራዊ ወጪን በተመለከተ አዲስ ዘገባ አወጣ። እንደዘገባው፣ ሀገራቱ ስለወታደራዊ ወጪያቸው ከበፊቱ በተሻለ መንገድ መረጃ ከማቅረባቸውም ሌላ፣ ይኸው ግልጽ አሰራራቸው እየዳበረ መጥቷል።

https://p.dw.com/p/38bq6
Nigeria Armee Task Force gegen Islamisten Boko Haram
ምስል Getty Images/AFP/I. Sanogo

«የሀገራቱ ወታደራዊ ወጪ መረጃ አቀራረብ ተሻሽሏል።»

የተመድን ጨምሮ፣ ዓለም አቀፍ ድርጅቶች፣ እስካሁን ድረስ ስለሀገራት ወታደራዊ ወጪ የተወሰነ እውቀት ብቻ እንዳላቸው የስቶክሆልም ስዊድን ዓለም  አቀፍ የሰላምና ፀጥታ ተቋም፣ በምህጻሩ ሲፕሪ አስታውቋል። የሲፕሪ ዘገባ ይፋ እንዳደረገው፣ ድርጅቶቹ ይህን በሚመለከት የተዘጋጁ መረጃዎች ሁሉ አይደርሷቸውም፣ መረጃዎቹንም ማግኘት ቀላል አይደለም። ይህ ሁኔታ ታድያ መረጃዎቹ የሉም ወደሚለው የተሳሳተ ድምዳሜ ሲያደርስ የሚታይ ሲሆን፣  ባንዳንድ አካባቢዎች መንግሥታት ስለሚያደርጉት ወታደራዊ ወጪ የሚጠቅሱ ብዙ ይፋ  መረጃዎች ቢኖሩም፣ የሉም የሚል ግምትም አሳድሯል። 
ከሰሀራ በስተደቡብ  ያሉት ሀገራት ለጦር መሳሪያ ግዢ ስለሚያደርጉት ወጪ በቀጥታ ዘገባ ማቅረብ ያለባቸው ብቸኛው ዓ/አቀፍ ድርጅት የተመድ ነው፣ ግን ፣ ይላሉ  አንዱ የሲፕሪ ዘገባ አዘጋጅ የሆኑት ናን ቲያን ፣ አንድም የዚሁ አካባቢ ሀገር ባለፉት ሶስት ዓመታት የጦር መሳሪያ ወጪውን በተመለከተ ለተመድ አንዳችም መረጃ አላቀረበም፣ ባለፉት አምስት ዓመታት ውስጥ ይህን ያደረጉት  አስር ሀገራት ብቻ ናቸው ። እና ሀገራት ያላቸውን መረጃ ለተመድ እንዲያቀርቡ ሊበረታቱበት የሚያስችል ዘዴ እንዲኖር ነው አሁን በጥናታችን  ያሳሰብነው። 
« ከሰሀራ በስተደቡብ  ካሉት 47 ሀገራት መካከል 45 የራሳቸውን  ጥናት ማካሄዳቸውን ማወቅ ችለናል። ይህን መረጃ አንድም በየገንዘብ ሚንስቴሮቻቸው ወይም በምርምር እና በትራንስፓሬንሲ ድረ ገጾች ላይ አውጥተዋል። ስለዚህ መረጃ ካለቸው ቢያስተላልፉት መልካም ነው፣ ምክንያቱም፣  ግልጽነት ሀገራት በጋራ እንዲሰሩ  የሚያስችለውን መተማመን ያሳድጋል። ይሁንና፣ ሀገራት በወቅቱ ለተመድ እያቀረቡ አይደለም። »
በሲፕሪ ጥናት የወጣው መዘርዝር እንደሚያሳየው፣ ለጦር መሳሪያ የተደረገው ወጪ ከፍተኛ ነው። ሱዳን ቀዳሚውን ቦታ ስትይዝ፣ ደቡብ አፍሪቃ፣ አንጎላ እና ናይጀሪያ ይከተላሉ። በዚሁ አካባቢ የሚገኑት አፍሪቃውያት ሀገራት ለወታደራዊው ቁሳቁስ ከጠቅላላ ብሔራዊ ገቢያቸው በአማካይ 1,7% አውጥተዋል።    የሀገራቱ  ወጪ በጣም ልዩነት ታይቶበታል፣ ለዚህም  የተፈጥሮ ሀብት ዋጋ  መውደቅ እና ባካባቢው  የሚካሄዱ የትጥቅ ውዝግቦችን እንደ ምክንያት ጠቅሷል።  በነዳጅ ዘይት ዋጋ ውድቀት በተለይ ናይጀሪያ በ2017 ዓም ወጪዋን ከሶስት ዓመት በፊት ከነበረው በ3,2 ቢልዮን ዶላር  እንድትቀንስ አስገድዷታል። በአንጻሯ፣ የመከፋፈል ስጋት የተደቀነባት ማሊ በአክራሪዎች አንጻር በምታካሂደው ትግል ለምሳሌ በ2014 እና በ2017 ዓም ወታደራዊ ወጪዋን በ152 ከመቶ በማሳደግ ወደ 275 ሚልዮን ዶላር ከፍ አድርጋለች።  
ከዚህ በተጨማሪ በያንዳንዱ ሀገር ፖለቲካዊ ባህል ሰበብ ሰብዓዊው እና የፋይናንሱ ወጪ ጭማሪ  እንደታየበት የጥናቱ አዘጋጆች መገንዘባቸውን ናን ቲያን በማመልከት፣ ይህ የንግድ ሂደቱ እንዲቀዘቅዝ እና የውው ቀጥተኛ ኢንቬስትመንት እንዳይገባ ማድረጉን ተናግረዋል። 
« « በእነዚህ ሀገራት ውስጥ አንድም ፈላጭ ቆራጮች ወይም በገንዘብ ኃይል የተቋቋሙ መንግሥታት ነው ያላቸው። መንግሥታቱ ፣ በተለይ የጦር ኃይሉን በስልጣን የሚቆዩበትን ሁኔታ ለማረጋገጫ እና ብዙኃኑን ህዝብ ለመቆጣጠሪያ ተግባር ይጠቀሙበታል። ምክንያቱም፣ እነዚህ መንግሥታት፣ በዴሞክራሲያዊ መንገድ በተመረጡ ብዙ መንግሥታት አንጻር፣ ግለሰቦች ወይም ቡድኖች መላውን ሀገር ሊቆጣጠሩ ስለሚችሉ  በጦር ኃይሉ ላይ የሚተማመኑ ይመስለኛል።  ይህ ስለሆነም፣ ወታደራዊ ወጪያቸውን የሚመለከተውን መረጃ ከህዝብ መደበቁን  ሊመርጡ ይችላሉ። »  
ይህም ቢሆን ግን፣ የስቶክሆልም ዓለም ዓቀፍ የሰላም ጥናት ተቋም ያወጣው ዘገባ ፣ የወታደራዊ ወጪን መረጃ ይፋ በማድረጉ  ላይ ሀገራቱ  እያሳዩት ያለው የተሻሻለው የግልጽነት አሰራር፣ ወደፊት እስከቀጠለ ድረስ፣ ባጠቃላይ ባካባቢው ዴሞክራሲን ለማሳደግ የተያዘ ትክክለኛ ጅምር አድርጎ ተመልክቶታል።   

Mali Gao
ምስል DW/K. Gänsler
Logo Friedensforschungsinstitut SIPRI

አርያም ተክሌ/ኬርስተን ክኒፕ 

ሂሩት መለሰ