1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

የአፍሪቃ ሃገራት የራሳቸውን የቅሪተ አጽም ነዳጅ ማልማት ይኖርባቸዋል?

ቅዳሜ፣ ሐምሌ 13 2016

ሴኔጋል ባለፈው ሰኔ ወር በባሕር ዳርቻ የሚገኘው የድፍድፍ ነዳጅ ማውጣት እንቅስቃሴዋን ከተጀመረ በኋላ የአፍሪቃ የነዳጅ ዘይት አምራች ሃገራት ዝርዝር ውስጥ መግባቷን በደስታ እያከበረች ነው። ሀገሪቱ የጀመረችው የነዳጅ ዘይትና ጋዝ ኢንደስትሪዋ ለኤኮኖሚ እድገቷ እንደ ወሳኝ ትመለከተዋለች።

https://p.dw.com/p/4iWfZ
የነዳጅ ዘይት ማጣሪያ
የነዳጅ ዘይት ማጣሪያ ፎቶ ከማኅደር ምስል Pond5 Images/IMAGO

የአፍሪቃ ሃገራት እና የቅሪተ አጽም ነዳጅ ፕሮጀክቶች

 

በሳንግማር የተጀመረው የመጀመሪያ ዙር ምርት ከአፍሪቃ ትላልቅ የነዳጅ ዘይት አምራች ሃገራት አቅም አኳያ ሲታይ በጣም ያነሰ ነው። ከሴኔጋል የባሕር ጠረፍ 90 ኪሎ ሜትር ርቀት ላይ የሚገኘው የሳንጎማር የነዳጅ ዘይት ማውጫ ስፍራ በቀን መቶ ሺህ በርሜል ድፍድፍ ነዳጅ ዘይት የማምረት አቅም አለው። የናይጀሪያው 1,2 ቢሊየን በቀን ያመርታል።

ሌላኛው በሴኔጋልና ሞሪታንያ ድንበር አቅራቢያ የሚገኘው ግዙፉ የሴኔጋል የጋዝ ክምችት ያለበት ስፍራ ከታሰበለት በሦስት ዓመት ቀደም ብሎ በመጪው ታኅሣሥ ወር አካባቢ ነዳጅ ዘይት ማምረት እንደሚጀምር ይጠበቃል።

ፔትሮሰን የተሰኘው የሴኔጋል መንግሥታዊ የኃይል ኩባንያ ዋና አስተዳዳሪ ቲየርኖ ሊ፤ «ከሳንግማር ድፍድፍ የነዳጅ ዘይት ማምረት መጀመሩ ለሀገራች ኢንደስትሪ ብቻ ሳይሆን ከምንም በላይ ለሕዝባችን የአዲስ ዘመን ምልክት ነው።» ይላሉ።

ፔትሮሰን እንደዋና ባለድርሻ ከሳንግማር ፕሮጀክት ከአውስትራሊያው ግዙፍ የኃይል ዘርፍ ኩባንያ ውድሳይድ ጋር በመሆን 18 በመቶ ድርሻ ይዟል። ከዚህም ሌላ ከቢፒ እና ኮስሞስ ኢነርጂ ጋር በጋራም የ10  በመቶ ድርሻ አለው።

ከቅሪተ አጽም የሚገኘው የነዳጅ ዘይት ሀብት የሴኔጋልን ኤኮኖሚ እንደሚያነቃቃው ቢገመትም ወደ ሀብታም ሀገርነት አያሸጋግርም በማለት ምሁራን እያስጠነቀቁ ነው።

ባለፈው ሚያዝያ ወር የዓለም የገንዘብ ድርጅት IMF የአካባቢውን የኤኮኖሚ ገጽታ በተመለከተ ይፋ እንዳደረገው ፈጣን የኤኮኖሚ እድገት ካላቸው ከሰሃራ በስተደቡብ ከሚገኙ ሃገራት ሴኔጋል አንዷ ናት። እንዲያም ሆኖ የነዳጅ ዘይትእና ጋዝ ምርት ለአጠቃላይ ኤኮኖሚው ያደርጋል ተብሎ የሚጠበቀው አስተዋጽኦ ግን በአንጻራዊነት ውስን መሆኑ ነው የሚገለጸው። መቀመጫውን ዩናይትድ ስቴትስ ያደረገው የብሔራዊ ሀብት አስተዳደር ተቋም የባለሙያዎች ቡድን ባልደረባ፤ ፓፓ ዳዑዳ ዲኔ እንደሚሉትም ከዚህ ዘርፍ የሚገኘው ካጠቃላይ ዓመታዊ ገቢ ከአምስት በመቶ ያንሳል።

«ምንም እንኳን ለአጠቃላይ ኦኮኖሚው የሚኖራቸው አስተዋጽኦ በአንጻራዊነት ውስን እንደሚሆን ቢጠበቅም፤ በቅርቡ የዓለም የገንዘብ ተቋም IMF ባደረገው ቅኝት እነዚህ ገቢዎች የሴኔጋልን የአጭርና የመካከለኛ ጊዜ ኤኮኖሚ ተስፋ ማሻሻል አለባቸው ብዬ አምናለሁ። ከአጠቃላይ ዓመታዊ ምርት ከአምስት በመቶ በታች ስለሆነው ያወራሉ። እንደምታዩት ደግሞ እነዚህ ሀብቶች ብቻ ሴኔጋልን ወደ ዱባይ ለመቀየር አይችሉም ። »

የሴኔጋል የነዳጅ ፕሮጀክት
የሴኔጋል የባሕር ዳርቻ የነዳጅ ፕሮጀክት ፎቶ ከማኅደርምስል DW

ከቅሪተ አጽም የሚገኘው ነዳጅ ዘይት ገበያ መቀዛቀዝ

ሴኔጋል ከነዳጅ ዘይት እና ጋዝ የምትገምተውን ያህል ገቢ የማግኘቷ ነገር እርግጠኛ አይደለም። ምክንያቱ ደግሞ በዓለም ደረጃ ወደ ንጹህ የኃይል ምንጭ ለመሸጋገር የሚደረገው እንቅስቃሴ ለረዥም ጊዜያት ለነዳጅ ዘይት እና ጋዝ የነበረውን ፍላጎት እንደሚቀንሰው ይገመታል።

አልጀሪያዊቱ የአየር ንብረት ፖሊሲ ተንታኝና የአየር ንብረት ለውጥን ለመግታት የሚነጋገረው የመንግሥታት መድረክ የአየር ንብረት ለውጥ ዘገባ ዋና አዘጋጅ ያሚና ሳሀብ፤ የሴኔጋል የነዳጅ ዘይት እና ጋዝን አዋጭነት በተመለከተ ያቀረቡት ግምገማ እውነታውን በግልጽ ያመላክታል። እሳቸው እንደሚሉትም ምንም እንኳን አሳዛኝ ዜና ሊሆን ቢችልም፤ የሀገሪቱን ኤኮኖሚ አሁን በማይሠራ ሞዴል ውስጥ የሚቀረቅር ነው።

በጀርመሩ አዲስ የአየር ንብረት ተቋም የአየር ንብረት ፖሊሲ ተንታኝ የሆኑት ማትስ ማርኳርድም ከነዳጅ ዘይት ገቢ ኤኮኖሚን አሳድጋለሁ የሚለው ግምት ተጋኗል ባይ ናቸው።  

«ከቅሪተ አጽም ነዳጅ የሚገኘው ገቢ እድገትን ያፋጥናት የሚለው ተስፋ ከመጠን በላይ የሆነ ይመስለኛል። እንደሚመስለኝ የጋዝ ወርቃማ ዘመን ማለፉን በግልጽ እያየን ነው ብዬም አስባለሁ። ይህ ደግሞ ዓለም አቀፉ የኃይል ተቋም ድምፁን በደም ከፍ አድርጎ የሚናገረው ነው፤ እናም በእነዚህ ሁኔታዎች የቅሪተ አጽም ነዳጅን ወደ ውጪ የመላኩ ንግድ በግልጽ አሁን መመርመር አለበት። »

ዓለም አቀፉ የኃይል ተቋም በቅርቡ ያወጣው የዓለም የኃይል ምንጭ ቅኝት እንደሚለው፤ በዓለም ገበያ ለድንጋይ ከሰል፤ ለነዳጅ ዘይት እና ለጋዝ የነበረው ፍላጎት ቀንሷል፤ በቀጣይ አስርት ዓመታትም ጭርሱን ይወርዳል።

የነዳጅ ዘይት እና የጋዝ ዋጋም በዓለም ደረጃ የሚቀንስ ከሆነ፤ ሴኔጋል እና ሌሎች ይህን ዘርፍ ለማሳደግ ከፍተኛ ገንዘብ ያፈሰሱ ሃገራት፤ መነሻ ወጪያቸውን እንኳን ለመሸፈን ፈተና ሊገጥማቸው እንደሚችል ይገመታል።

የአውሮጳ አዲስ የጋዝ አቅራቢዎችን መፈለግ ማቆም

ለምዕራብ አፍሪቃ የጋዝ ምርት ዋነናው ገበያ አውሮጳ ነው። ሆኖም ግን ከሁለት ዓመት በፊት ሩሲያ ዩክሬን ላይ ጦርነት ስትከፍት የአፍሪቃ የጋዝ ፕሮጀክቶች ላይ መዋዕለ ንዋይ ለማፍሰስ ከፍተኛ ፍላጎት ያሳየው የአውሮጳ ኅብረት ትኩረቱን ወደ ታዳሽ የኃይል ምንጮች በማድረግ ለአዲሱ ዘርፍ ድጋፍ አድርጓል። በጎርጎሪዮሳዊው 2022 ዓ,ም ብቻም ከፀሐይና ከንፋስ 22 በመቶ የኤሌክትሪክ ኃይል በኅብረቱ ሃገራት ማምረት ተችሏል።

በዚህ መነሻነትም ከአየር ንብረት አኳያ ግልጽ ግቦች ያሉት የአውሮጳ ገበያ ሌላ የኃይል ምንጭ የሚፈልግበት ደረጃ ላይ እንዳልሆነ ነው ማትስ ማርኳርድ ያመለከቱት።

የንፋስ የኃይል ምንጭ ናሚቢያ
የናሚቢያ የንፋስ ታዳሽ የኃይል ምንጭ ፎቶ ከማኅደር ምስል DW

አፍሪቃ እና የአየር ንብረት ለውጥ 

የአፍሪቃ ሃገራት 50 በመቶ ለሚሆነው ሕዝባቸው የኤሌክትሪክ ኃይል ለማቅረብ ከቅሪተ አጽም የሚገኘውን የነዳጅ ዘይት ሀብታቸውን መጠቀም መብታቸው እንደሆነ በየጊዜው አጽንኦት ሰጥተው ያሳስባሉ።

እርግጥ ነው አሁን ለተከሰተው የአየር ንብረት ለውጥ ሙቀት አማቂ ጋዞችን በመልቀቁ በኩል የአፍሪቃ ሃገራት ድርሻ እዚህ ግባ የሚባል አይደለም። ሆኖም በዚህ የኃይል ምንጭ ዘርፍ ላይ የገንዘብ ሃብትን ማዋል የከባቢ አየርን ብክለት ማባባስ እንደሚሆን ባለሙያዎች ያሳስባሉ። አፍሪቃ እምቅ የታዳሽ ኃይል ምንጭ ሀብት እንዳላት የሚገልጹት ቱኒዚያዊው የኤኮኖሚ ባለሙያ ፈዲል ካቦውብ፤ አፍሪቃ ከዓለም ገበያ እየወጣ ካለው የኃይል ምንጭ ይልቅ በታዳሽ የኃይል ምንጭ ላይ ብታተኩር ያዋጣታል ነው የሚሉት።

«በአፍሪቃ ክፍለ ዓለም ከቅሪተ አጽም ለሚገኘው ነዳጅ አማራጫችን ታዳሽ የኃይል ምንጭ መሆኑን ማስታወስ ይኖርብሃል። እንደ ዓለም አቀፉ የኃይል ተቋም ከአፍሪቃን የተመለከተ የቅርብ ዘገባ ሆነ ፤ በጎርጎሪዮሳዊው 2040 ማለትም በመጪዎቹ 15 ዓመታት፤ በአዳዲስ ቄንጠኛ ፈጠራዎች ሳይሆን ባለው የታዳሽ የኃይል ምንጭ ቴክኒዎሎጂ በመጠቀም አፍሪቃ የሚፈለገው ኃይል አንድ ሺህ ጊዜ ማመንጨት ትችላለች። አንዲ ሺህ ጊዜ!።»

ሸዋዬ ለገሠ