1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

የአፍሪቃዉያን አስተያየት በእስራኤል እና ሃማስ ጦርነት

ዓርብ፣ ጥቅምት 2 2016

ጦርነቱ በአፍሪቃ ያለውን አመለካከት ከፋፍሎታል። የአፍሪቃ ሃገራት መንግሥታት መሪዎች፤ አሸባሪ ተብሎ በተፈረጀዉ በሃማስ ቡድንና በእስራኤል መከላከያ ኃይሎች መካከል የተኩስ አቁም እንዲደረግ፣ ውይይት እንዲጀመርና ለንጹኃን ዜጎች ጥበቃ እንዲደረግ እየጠየቁ ነው። የአፍሪቃ ህብረት በበኩሉ ጦርነቱ ይቁም ብሏል።

https://p.dw.com/p/4XVvd
የእስራyle ጥቃት በጋዛ
እስራኤል በጋዛ ላይ ያደረሰችዉ ጥቃት ምስል Ibraheem Abu Mustafa/REUTERS

«የሚሰጠዉ ምላሽ እና አስተያየት፤ ከእስራኤል ጋር ካለው ግንኙነት ጋር የተመሰረተ ነዉ»

የእስራኤልና የሃማስ ጦርነት ተባብሶ እንደቀጠለ ነዉ። ይህ ጦርነት በአፍሪቃ ያለውን አመለካከት ከፋፍሎታል። የአፍሪቃ ሃገራት መንግሥታት መሪዎች፤ በእስራኤል፤ በዩናይትድ ስቴትስ እና በአዉሮጳ ህብረት አሸባሪ ተብሎ በተፈረጀዉ በሃማስ ቡድን እና በእስራኤል መከላከያ ኃይሎች መካከል የተኩስ አቁም እንዲደረግ፣ ውይይት እንዲጀመር እና ለንጹኃን ዜጎች ጥበቃ እንዲደረግ እየጠየቁ ነው። የአፍሪቃ ህብረት በበኩሉ  ጦርነቱ ይቁም ሲል ጠይቋል።

በእስራኤል እና በፍልስጤማዉያኑ መካከል ስለሚካሄደዉ ግጭት፤ አንድ ሀገር የሚሰጠዉ ምላሽ እና አስተያየት፤ ከእስራኤል ጋር ካለው ግንኙነት ጋር የተመሰረተ ነዉ።  ይሁን እና በርካታ የአፍሪቃ መሪዎች በእስራኤል እና በሃማስ መካከል ስለቀጠለው ግጭት በግልጽ የተናገሩት ነገር የለም። አብዛኞቹ የአፍሪቃ ሃገር ምላሾች የሃማስን የሽብር ጥቃት ያወገዙ፣ ሌሎች ደግሞ የሁለት ሉዓላዊ ሃገራት መፍትሄ እንዲፈልግ ጥሪ የቀረቡበት ነዉ።የተባባሰው የእስራኤል ሀማስ ጦርነትና የአውሮጳውያን አቋም

የኬንያው ፕሬዝዳንት ዊሊያም ሩቶ ሃማስ  በእስራኤል ላይ ያደረሰውን ጥቃት በማውገዝ ጠንካራ ቃል የተናገሩ አፍሪቃዊ  መሪ ናቸዉ።  ሩቶ ዓለም አቀፉ ማህበረሰብ “የሽብር ወንጀለኞች ፣ የሽብር ጥቃት አዘጋጆች ፣ ገንዘብ ሰጭዎች፣ ደጋፊዎች እና አጋሮች” ላይ እርምጃ እንዲወስድ ሲሉም በጥብቅ አሳስበዋል።

የኬንያዉ ፕሬዚደንት ሩቶ በይፋዊ የትዊተር ማለት ኤክስ ገጻቸዉ ላይ “ኬንያ ከእስራኤል መንግስት እና  ከተቀረው ዓለም ጋር በመተባበር  በሀገሪቱ ውስጥ ሽብርተኝነትን እና በንጹሃን ዜጎች ላይ የሚደርሰውን ጥቃት በማያሻማ ሁኔታ ታወግዛለች” ብለዋል። ኬንያዊዉ የታሪክ ተመራማሪ ሳሙኤል ኪፕቶ ከ DW ጋር ባደረጉት ቃለ ምልልስ እንዳሉት ከሆነ ደግሞ ኬንያ እና እስራኤል ጠንካራ የሁለትዮሽ ግንኙነት አላቸው።ማሕደረ ዜና፣ የእስራኤልና ሐማስ ጦርነት

«ኬንያና እና እስራኤል ጠንካራ እና ተመሳሳይ ልምድ ላይ ያተኮረ ግንኙነት ያላቸዉ ሃገራት ናቸዉ። እስራኤል  ላይ ምንም ነገር ይፈፀም እንደ ሃገርም ሆነ እንደ ህዝብ ኬንያ ትልቅ ትኩረት የምትሰጠu ሃገር ናት። በጎርጎረሳዉያኑ 1998 ናይሮቢ ላይ የሽብር ጥቃት ሲደርስ ፤ እስራኤል በቅስበታዊ ፍጥነት ኬንያ ደርሳ እርዳታን የሰጠች፤ ከፈረሰዉ ህንጻ ስር ህዝብ ለማዳን ከፍተኛ ርብርብ ያደረገች ሃገር ናት»   

አንጎላ፣ኬንያ፣ጊኒ-ቢሳው እና ደቡብ አፍሪቃ በእስራኤል እና በፍልስጤማዉያን መካከል እየተካሄደ ስላለዉ ጦርነት ስጋታቸውን ከገለጹ እና ካወገዙ የአፍሪቃ ሀገራት መካከል ይጠቀሳሉ። እነዚህ ሀገራት ጦርነቱ በአስቸኳይ እንዲቆም እና ሁለቱም ወገኖች ወደ ውይይት እንዲገቡ  አሳስበዋል።በሃማስ ጥቃት በርካታ ቤተ እስራኤላዉያን ተገድለዋል ተባለ

የአፍሪቃ ህብረት ኮሚሽን ሊቀ-መንበር ሙሳ ፋኪ ማሃማት በበኩላቸዉ “የፍልስጤም ህዝብ የነፃ እና የሉዓላዊ መንግስት መብቶች መከልከሉ  ለቋሚ የእስራኤል እና የፍልስጤም ውጥረት ዋንኛ መንስኤ ነው” ብለዋል። ሊቀመንበሩ ሁለቱ ወገኖች ወታደራዊ ግጭቶችን እንዲያቆሙ እና ያለምንም ቅድመ ሁኔታ ወደ ድርድር እንዲመለሱም ለሁለቱም ወገኖች ጥሪ አቅርበዋል።

በዩጋንዳ ካምፓላ ነዋሪ የሆኑ የሰብአዊ መብት ተሟጋች ኢብራሂም ሴንዳውላ እንደሚሉት ከሆነ ደግሞ በአንድ ግጭት ዉስጥ ወግኖ መቆም ግጭቱን ከማባባስ በቀር የሚፈይደዉ ነገር የለም። «ለእስራኤል እና ለፍልስጤማዉያን ግጭት መፍትሄዉ መነጋገር እና መወያየት ብቻ ነዉ። መፍትሄዉ አሜሪካ እና የሌሎች ሃገራት መንግሥታት ሲያደርጉ እንዳየነዉ ሁሉ በዚህ ግጭት ዉስጥ እጃቸዉን እንዳያስገቡ ነዉ።»

እስራኤል በጋዛ ሰርጥ ላይ ያደረሰችዉ የጥቃት አጸፋ
እስራኤል በጋዛ ሰርጥ ላይ ያደረሰችዉ የጥቃት አጸፋ ምስል Rizek Abdeljawad/Xinhua/picture alliance

የደቡብ አፍሪቃው ፕሬዝዳንት ሲሪል ራማፎሳ የሃገራቸዉን የግጭት አፈታት ልምድ በመጥቀሰ በእስራኤል እና ፍልስጤም መካከል ያለዉን ቁርቁስ  በሽምግልና ለመፍታት ዝግጁ መሆናቸውን ተናግረዋል። በመካከለኛው ምስራቅ ዕርዳታ ለሚያስፈልጋቸው ሰዎች ሁሉ እንዲደርስ "የሰብአዊ ርዳታ ማስገብያ ኮሪደሮች" በአስቸኳይ እና ያለምንም ቅድመ ሁኔታ እንዲከፈት ራማፎሳ ጠይቀዋል።

በእስራኤል እና በፍልስጤም ግዛቶች ዉስጥ የሚደረገዉ  ዉግያ፤ በአፍሪቃዉያን ዘንድ በእስራኤል መንግሥት በአዉሮጳ ህብረት በዩናይትድ ስቴትስ እና ብሪታንያ በአሸባሪነት በፈረጀዉ በሃማስ ቡድን መካከል የሚደረግ የተናጠል ዉግያ ሳይሆን፤ በእስራኤል  እና በፍልስጤማዉያን መካከል ለረጅም ጊዜ የሚካሄደዉ  ግጭት ቀጣይ አካል ተደርጎ ነዉ የሚታየዉ።

አዜብ ታደሰ / አይዛክ ሙጋቤ 

እሸቴ በቀለ