ሁሉን ሰው ሊያጋጥም የሚችለው የአጥንት መሳሳት
ማክሰኞ፣ ሚያዝያ 8 2016
የአጥንት መሳሳት መንስኤ
ከአድማጭ የተላከልንን ጥያቄ መነሻ በማድረግ በድጋሚ ስለአጥንት መሳሳት የጤና ችግር መንስኤ የጠየቅናቸው በዘርፉ ለረዥም ዓመታት በከፍተኛ ሃኪምነት ያገለገሉት ዶክተር ውብታየ እንደገለጹልን የአጥንት መሳሳት ችግር የዕድሜው ሁኔታ ሊለያይ ቢችልም ሁሉንም ሰው ሊያጋጥም የሚችል ነው። እሳቸው እንደሚሉትም ለአጥንት መሳሳት ከሚጠቀሱ ምክንያቶች በሰውነታችን ውስጥ ያሉ ሆርሞኖች ወይም ንጥረ ነገሮች በሂደት የሚያደርጉት ለውጥ አንዱ ነውና ምናልባትም ዋነኛው ነው።
ችግሩ በዕድሜ ሂደት በሴቶች ላይ ቀድሞ የሚከሰት ሲሆን ወንዶችም የአጥንት መሳሳት ተጋላጭ ናቸው። ጠያቂያችን የእናትዎን ዕድሜ አልገለጹም፤ ቢታወቅ ኖሮ ለማብራሪያው የተሻለ እንደሚሆን ነው የተረዳነው። እንዲያም ሆኖ ለአጥንት መሳሳት የሚታወቁም የማይታወቁም ምክንያቶች መኖራቸውን ባለሙያው ይገልጻሉ። አጥንት እንዲሳሳ የሚያደርጉ ምክንያቶች ከሰውነት ውስጥ ያሉ ሂደቶች ብቻም አይደሉም ይላሉ ዶክተር ውብታዬ። ውጫዊ ምክንያቶች ማለትም አልክሆል መጠጥ ማዘውተር፤ እንዲሁም ትንባሆ ማጨስ የመሳሰሉ መንስኤዎች አሉ።
ይህም ብቻም አይደለም ተጓዳኝ ህመም እንደ ስኳር፣ ኩላሊት፤ ሪህ እና የመሰሳሰሉ የጤና ችግሮች መኖር፤ ለእነሱም ሲባል የሚወሰዱ መድኃኒቶች ተጽዕኖ እንደሚኖራቸውም አብራርተዋል። በተጨማሪ፤ ከመጠን ያለፈ ውፍረትና በቂ እንቅስቃሴ አለማድረግም እንዲሁ መንስኤዎች እንደሆኑ ነው ባለሙያው የተናገሩት።
የአጥንት መሳሳት ችግርን ለማወቅ የሚደረገው
አስቀድሞ የአጥንት መሳሳቱ ችግር እንዳለና በምን ያህል መጠን እንደሆነ ተገቢውን ምርመራ አድርጎ ከታወቀ በኋላ በሀኪም ትዕዛዝ መሠረት አስፈላጊውን መድኃኒት መውሰድ ሊያግዝ እንደሚችል የገለጹት ዶክተር ውብታዬ፤ መድኃኒቱ ግን ለሕይወት ዘመን የሚወሰድ መሆኑንም አመልክተዋል። ምርመራዎችን ሳያደርጉ ሊወሰዱ የሚችሉ መድኃኒቶችን በተመለከተም የቫይታሚን ዲ ንጥረ ነገር ያለባቸውን የምግብ ተጨማሪዎችን መጠቀም እንደሚመከርም ገልጸዋል። እንዲያም ሆኖ ግን የተሻለ የሚሆነውና የሚመከረው ግን በሀኪም ተመርምሮ የሚታዘዘው መድኃኒት እንደሆነ አጽንኦት ሰጥተዋል።
የሀኪም ምክር
የአጥንት መሳሳት ችግር በአብዛኛው ከዕድሜ መጨመር ጋር የሚገናኝ ቢሆንም በተለያዩ ምክንያቶች በወጣትነትም ሊያጋጥም እንደሚችልም ነው ዶክተር ውብታዬ መለከቱት። ጠያቂያችን እናትዎ ያጋጠማቸው የአጥንት መሳሳት ከተጠቀሱት መንስኤዎች በአንዱ ወይም በሌላው ሊሆን እንደሚችል በመገመት ሀኪም ቤት በመሄድ ተገቢውን ምርመራ እንዲያደርጉ መክረዋል። አጥንት እንዲጠነክር ደግሞ በየቀኑ ቢያንስ ለ30 ደቂቃ የእግር ጉዞ ማድረግ እንደሚረዳም ጠቁመዋል። ካልሲየም የሚገኝባቸውን እንደ ወተት እና የወተት ተዋጽኦ ያሉ ምግቦችን መመገብ፤ ክብደት መቀነስ አስፈላጊ መሆኑንም የዘርፉ ከፍተኛ የህክምና ባለሙያ ዶክተር ውብታየ ዱሬሳ ተክሌ አክለው ገልጸዋል። አድማጫችንን ለተሳትፏቸው እንዲሁም ሙያዊ ማብራሪያ የሰጡንን ዶክተር ውብታየን እናመሰግናለን።
ሸዋዬ ለገሠ
ኂሩት መለሰ