1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

የአዳዲስ ክልሎች ምሥረታ ዝግጅት በደቡብ

ዓርብ፣ የካቲት 17 2015

የደቡብ ክልልን በሁለት ክልሎች ለማደራጀት ቅደም ዝግጅት በማድረግ ላይ እንደሚገኝ የደቡብ ኢትዮጵያ ክልል ምስረታና ነባሩን ክልል በአዲስ የማደራጀት ማስፈፀሚያ ፕሮጀክት ጽ/ቤት አስታወቀ። ጽ/ቤቱ “የደቡብ ኢትዮጵያ“ እና “ ማዕከላዊ ኢትዮጵያ ክልል “በሚል ይዋቀራሉ ተብለው ለሚጠበቁት ክልሎች የህገ መንግስትና ሌሎች ሰነዶች ተዘጋጅተዋል።

https://p.dw.com/p/4NwhI
Äthiopien Referendum Arbaminch
ምስል Shewangizaw Wegayehu/DW

“የደቡብ ኢትዮጲያ “ እና “ ማዕከላዊ ኢትዮጵያ ክልል“

በኢትዮጵያ ካለፉት አምስት ዓመታት ወዲህ የታየው የፖለቲካ ለውጥ ለሦስት አሥርተ ዓመታት በዘለቀው የደቡብ ብሄር ፣ ብሄረሰቦችና ህዝቦች ክልል አዳዲስ የአደረጃጀት ጥያቄዎች እንዲነሱ ምክንያት ሆኗል፡፡ በተለይም የሲዳማ በ2012 ዓም ፤ የደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ ደግሞ በ2014 ዓም ከክልሉ በመነጠል የራሳቸውን ክልላዊ መንግሥት ማቆማቸውን ተከትሎ ክልሉ ተመሳሳይ የእንደራጅ ጥያቄዎችን ሲያስተናግድ ነው የከረመው ፡፡ 

አሁን ላይ ክልሉ እየከሰመ መምጣቱን የሚያረጋግጡት የመጨረሻዎቹ ሁለቱ ክልሎች “ የራሳችን “ ያሉትን ክልላዊ መንግሥት ለማደራጀት ከጫፍ የደረሱ ይመስላል ፡፡ አዳዲሶች ክልሎች “ የደቡብ ኢትዮጲያ “ እና “ ማዕከላዊ ኢትዮጵያ ክልል “  በሚል የሚዋቀሩት የኢፌድሪ ፌዴሬሽን ምክር ቤት አሁን ያለው የደቡብ ብሄር ፣ ብሄረሰቦችና ህዝቦች ክልል በሁለት ተከፍሎ እንዲደራጅ ባለፈው ዓመት የነሀሴ ወር 2014 ዓ.ም ባሳለፈው ውሳኔ መሠረት ነው ፡፡

በፌዴሬሽን ምክር ቤቱ ውሳኔ መሠረት ወላይታ፣ ጋሞ፣ ጎፋ፣ ደቡብ ኦሞ፣ ኮንሶ  ጌዴኦ ዞኖችና እንዲሁም  አማሮ፣ ቡርጂ፣ ዲራሼ፣ አሌ እና ባስኬቶ ልዩ ወረዳዎች  “ የደቡብ ኢትዮጲያ ክልል “ በሚል በህዝበ ውሳኔ በጋራ የሚደራጁ ይሆናል ፡፡ ቀሪዎቹ የሀላባ፣ ስልጤ፣ ከምባታ ጠምባሮ፣ ሀዲያ እና ጉራጌ እና የም ልዩ ወረዳ “ ማዕከላዊ ኢትዮጵያ ክልል “ በሚል በሌላኛው የጋራ ክልል በአንድ ላይ እንደሚደራጁ ነው የነሀሴ ወር  የፌዴሬሽን ምክር ቤቱ ውሳኔ የሚያመለክተው ፡፡

Äthiopien Arbaminch Referendum
ሕዝበ ውሳኔ በደቡብ ክልልምስል Shewangizaw Wegayehu/DW

የህገ መንግሥት ሠነዶች ዝግጅት 

አሁን ያለውን የደቡብ ክልል በሁለት ክልሎች ለማደራጀት የደቡብ ኢትዮጵያ ክልል ምስረታና ነባሩን ክልል በአዲስ የማደራጀት ማስፈፀሚያ ፕሮጀክት ጽህፈት ቤት የተባለ ተቋም ተመስርቶ ከተያዘው ዓመት መግቢያ አንስቶ በእንቅስቃሴ ላይ ይገኛል ፡፡  በክልሉ መንግሥት አማካኝነት የተቋቋመው ይሄው የፕሮጀክት ጽህፈት ቤት  በሥሩ የህገ መንግሥት አርቃቂን ጨምሮ የተለያዩ ኮሚቴዎችን ያቀፈ ነው ፡፡ ጽህፈት ቤቱ አሁን ላይ “ የደቡብ ኢትዮጵያ “ እና “ ማዕከላዊ ኢትዮጵያ ክልል “  በሚል ይዋቀራሉ ተብለው ለሚጠበቁት ክልሎች የህገ መንግስት እና ሌሎች ሰነዶችን በረቂቅ ደረጃ ማዘጋጀቱን ጽህፈት ቤቱ ገልጿል፡፡አሁን ላይ በሰነዶች ዙሪያ የተለያዩ ማህበረሰባዊ መሠረት ካላቸው አካላት ጋር እየተመከረባቸው እንደሚገኙ ነው የጽህፈቱ ቤቱ  ዋና ሥራአስኪያጅ አቶ ኩታዬ ኩስያ ለጋዜጠኞች የተናገሩት ፡፡

ህገ መንግሥት የማርቀቁ ሥራ በሁለት ተከፍሎ ከፌዴራል እና ከክልል ህገ መንግሥቶች አንፃር ሲሰራበት መቆየቱን የሚናገሩት የጽህፈቱ ቤቱ  ዋና ሥራአስኪያጅ አቶ ኩታዬ “  በተለያዩ ኮሚቴዎች በረቂቅ ደረጃ ተዘጋጅተው የቀረቡት ሠነዶች የህዝብን ፍላጎት መሠረት ያደረጉ ናቸው ብለን እናምናለን ፡፡ ቀደምሲል በነባሩ ክልሎች በሀብትና በሥልጣን ክፍፍል ረገድ ይስተዋሉ የነበሩ ክፍተቶችን በአሁኑ ሠነዶች ውስጥ  ለመሙላት ተሞክሯል “ ብለዋል ፡፡ 

በረቂቅ ሠነዶቹ ላይ  ከፌዴሬሽን ምክርቤት፣ ከፌዴራል የፍትህና ህግ ኢንስቲትዩት እንዲሁም ከደቡብ ክልል የፍትህ አካላት ባለሙያዎች ስልጠናና ምርምር ማዕከል የተውጣጡ የህግ ባለሙያዎች አስተያየት እንዲሰጡባቸው መደረጉን የጠቀሱት አቶ ኩታዬ “ በአሁኑ ወቅትም በተለያዩ ማህበራዊ መሠረት ላይ የሚገኙ አካላት ሀሳብ እንዲሰጡበት የሚያስችሉ መድረኮችን ተዘጋጅተዋል “ ብለዋል ፡፡

Äthiopien Arbaminch Referendum
ሕዝበ ውሳኔ በደቡብ ክልልምስል Shewangizaw Wegayehu/DW

የአደረጃጀት ሂደቱ በባለሙያዎች እይታ 

በአዳዲሶቹ ክልሎች የአደረጃጀት ዝግጅት ዙሪያ ዶቼ ቬለ DW የተለያዩ የህግ ባለሙያዎችና ተመራማሪዎች አስተያየቶችን ለማሰባሰብ ሞክሯል፡፡ አብዛኞቹ አስተያየት ሰጪዎች በደቡብ ኢትዮጵያ የዎላይታ ፣ በማዕከላዊ ኢትዮጵያ ክልል ደግሞ በጉራጌ ዞን በኩል የሚታየው በተናጠል የመደራጀት ፍላጎት በአደረጃጀት ሂደቱ ላይ አሉታዊ ጫና ሊያሳድር ይችላል የሚል ግምት እንዳላቸው እየገለጹ ይገኛሉ ፡፡ በሀዋሳ ዩኒቨርሲቲ የህግ መምህር የሆኑት ረዳት ፕሮፌሰር ሽመልስ አሻግሬ ሥጋቱን ከሚጋሩት መካከል አንዱ ናቸው ፡፡ በክልሉ ከሲዳማና የደቡብ ምዕራብ ህዝቦች ራሳቸውን ችለው ከወጡ ወዲህ  የዎላይታ እና የጉራጌ ብሄረሰቦች  በተናጠል የመደራጀት ፍላጎቶች እየተንጸባረቁ እንደሚገኙ የጠቀሱት ረዳት ፕሮፌሰር ሽመልስ “  በተለይ በጉራጌ በጣም ግልፅ በሆነና በዞን ምክር ቤቱ ጭምር እኔ በራሴ እደራጃለሁ  በማለት በጋራ ክልል ውስጥ ለመግባት ፍላጎት እንደሌለው አሳውቋል  ፡፡ በአንፃሩ የዎላይታ ጉዳይም ምርጫ ቦርድ ራሱ ባረጋገጠው መረጃ ህዝበ ውሳኔው ከባድ የህግ ጥሰቶች እንዳሉበት የታወቀ ነው ፡፡ አሁን እነኝህ ሁለቱ ትልልቅ ቁጥር ያላቸው ህዝቦች ያነሱት ጥያቄ ሳይመለስ ፕሮጀክቱ አደረጃጀቱን ወደ መሬት ለማውረድ በተጀመረው ሂደት ላይ አሉታዊ ጫና ሊኖረው ይችላል “ ብለዋል፡፡

ሸዋንግዛው ወጋየሁ

አዜብ ታደሰ 

ኂሩት መለሰ