1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

የአዲስ ዓመት እቅዶች እና ማሳኪያ መንገዶች

ዓርብ፣ ጳጉሜን 4 2014

ኢትዮጵያ ውስጥ አዲስ ዓመት በድምቀት የሚከበር በዓል ብቻ ሳይሆን ሰዎች በመጪው ዓመት ለማሳካት የሚፈልጉትን ነገሮች እቅድ የሚያወጡበትም ነው። ነገር ግን ምን ያህላችን ያቀድነውን እናሳካለን? እቅዶች ሳይሳኩ የሚቀሩትስ ለምንድን ነው?

https://p.dw.com/p/4Gc6r
Illustration | Neujahrsziele
ምስል Christian Horz/Zoonar/picture alliance

ኢትዮጵያን ጨምሮ የተወሰኑ ሀገራት አዲስ ዓመትን የሚያከብሩበት ዕለት ከተቀረው የዓለማችን ክፍል የተለየ ነው።  በሁሉም ሀገራት ግን አንድ በጋራ የሚደረግ ነገር አለ። በአዲስ አመት አዲስ እቅድ ማውጣት!  

ኢትዮጵያ ውስጥ  አዲስ አመት በመስከረም ወር ሲከበር፤ ቻይናውያን ለምሳሌ በጥር ወር አጋማሽ ፣ ታይላንዳዊያን ደግሞ በሚያዚያ ወር አዲስ ዓመትን ያከብራሉ። ሁሉም ጋር ዓመተ ምህረቱ እና አከባበሩም ይለያያል። አብዛኛውን ጊዜ አዲስ ዓመት አዲስ እቅድም የሚወጣበት ነው።  እቅድ ማውጣት ከሕይወት የሆነ ነገር እንድንጠብቅ ያደርገናል። ሰዎች ምኞቶች እና ህልሞች ካሏቸው ደግሞ ይበልጥ የተሻለ ቦታ ለመድረስ ይፈልጋሉ፤ ይጥራሉም ይላሉ ባለሞያዎች። በአዲስ አበባ ዩኒቨርስቲ መምህር እና የህፃናት እና ወጣቶች የአዕምሮ ሀኪም የሆኑት ዶክተር ዮናስ ባህረ-ጥበብ እቅድ የግድ አዲስ ዓመትን አስታኮ መሆን ባይኖርበትም ከአዲስ ዓመት ጋር ማገናኘቱ ጥሩ ነው ይላሉ። « የተለመደ ነገር ነው። ነገር ግን ሌላም ጊዜም እቅድ ማውጣት ይቻላል። አይምሮዋችን መለወጥ አለበት ብሎ በተነቃቃ ጊዜም እቅድ ማውጣት ይቻላል።»

አቤኔዘር አዲስ አበባ ውስጥ የሚኖር የ28 ዓመት ወጣት ሲሆን፤ በርካታ በመጪው ዓመት ዕውን ማድረግ የሚፈልጋቸው ግቦች አሉት። እነዚህንም የሚያቅደው አዲስ አመትን አስታኮ በዚህ በጳግሜ ወር ነው።  « ጳግሜ ላይ አመታችንን እንገመግማለን። በ 13 ወር ፀጋ የተነሳ ጳግሜ ለኢትዮጵያውያን ልዩ ናት ። ያም ድባብ አለ። እና እኔ አነስ ያለች ድርጅት አለችኝ። የትርጉም ስራ የምሰራባት። ይህን ለማስፋፋት አስቤያለሁ።  በቤተሰቤ ዙሪያ፤ በጤና ዙሪያ፣ በሁሉም የህይወቴ አስፔክቶች ያስቀመጥኩት ግብ አለ» ይላል።

የወሎ ነዋሪ የሆነው መሀመድ ያለፈውን ዓመት በሀገሪቱ ጦርነት ምክንያት ሥራውን አቋርጦ በወታደርነት ያሳለፈ ሲሆን፤ በአዲሱ ዓመት ወደቀድሞ ሞያው የመመለስ እቅድ  አለው።  « ሀገራችን ሰላም ከሆነች ወደ ስራ የመግባት እቅድ አለኝ። የአማራ ልዩ ኃይልን የመቀላቀል ዓላማ ነበረኝ። ነገር ግን በቂ ኃይል አለኝ ብሏል። » መሀመድ የጋራዥ ባለሙያ ነው።

ለጊዜው ሚኪ ብላችሁ ጥሩኝ ያለን የ27 ዓመት ወጣት በመጪው ዓመት ሊያሳካው የሚፈልገው ምንም አይነት እቅድ የለም። ይህም ከተስፋ መቁረጥ የመነጨ ነው። « አሁን ላይ እቅድ የማይታሰብ ነው። ሰርቶ መለወጥ አይቻልም። አብዛኛው ወጣት ምሮቱን ነው የሚያወራው።» ይላል የመንግሥት ሰራተኛ የሆነው ሚኪ።

ፍርድ ቤት ውስጥ የሚሰራው ሚኪ በአሁኑ ሰዓት እንደ ብቸኛ አማራጭ የሚያየው ከሀገር መውጣትን ነው። ለዚህም ምክንያት የሚለው በሀገሪቱ ያለው ጦርነት፤ ርሃብ እና ድህነት ናቸው።  
አምባዬ በአንፃሩ ተስፋ ይታየዋል። ለአዲሱም ዓመት እቅድ አለው፤ ይህም አሁን ከሚሰራው የእቃ ማድረስ ሥራ ጋር የተያያዘ ነው። አምባዬ ሲያናግረንም በዓመት በዓል ገበያ ምክንያት በሥራ ተጠምዶ ነው፤ « በዚህ ዓመት የእቃ ማድረስ ስራ ስሰራ ነበር። ማህበረሰባችንም አስተሳሰቡን እየቀየረ ነው። ስልክ ደውሎ እቃ ያዛል። ስናደርስም ቲፕ ይሰጠናል። እና ብድርም ማግኘት የሚቻልበት መንገድ እየተመቻቸ ስለሆነ በመጪው ዓመት እነዚህን እቃ አድራሾችን የሚያገናኝ አፕሊኬሽን የመስራት እቅድ አለኝ»

እቅድ ብቻ ግን ከግብ አያደርስም። አዲስ ዓመትን አስታኮም ሆነ ሳይሆን የምናወጣቸው እቅዶች እንዲሳኩ በርካታ ከግምት ውስጥ የምናስገባቸው  ነገሮች አሉ።  የህፃናት እና ወጣቶች የአዕምሮ ሀኪም ዶክተር ዮናስ « እቅድ ከማውጣታችን በፊት ጥሩ አድርገን ራሳችንን ማበረታታት እና ማነቃቃት ይኖርብናል» ይላሉ። ጥሩ እና መጥፎ ጎኑን መለየት፣ ብዙ ነገሮች ሳይሆን ዋና ዋና የሚባሉ ጥቂት ነገሮችን መምረጥ እና ዲሲፕሊን ወሳኝ ናቸው ይላሉ ዶክተር ዮናስ።

ሌላው ግባችንን ለማሳካት ልማድ ልናደርገው የሚገባን ነገር፤ ዶክተር ዮናስ እንደሚሉት እቅዳችንን በጽሑፍ ስናስቀምጥ ነው።  በትርጉም ሥራ ላይ የተሰማራው አቤነዘርም ግቡን በዓመቱ መጨረሻ የሚገመግመው በዚህ መንገድ ነው። « ምን ምን ስራዎችን ሰርቻለሁ፤ ምን ይቀረኛል የሚለውን በዛ ነው የምገመግመው።»

በአሁኑ ሰዓት አዲስ አበባ ውስጥ ከአንድ ቦታ ወደ ሌላ ቦታ እቃ በማድረስ ሥራ ላይ ተሰማርቶ የሚገኘው አምባዬ፤ አንዳንዴ ሁለት እቃ በማድረስ ብቻ ቀኑ እንደሚቃጠል ገልፆልናል። በዚህም ምክንያት ይህንን ማሻሻል የሚችል መተግበሪያ ወይም አፕሊኬሽን የመሥራት እቅድ እንዳለው ገልፆልናል። ነገር ግን ይህን እንዴት ነው በአዲሱ ዓመት እውን ማድረግ የፈለገው? የኮምፒውተር ሳይንስ ተማሪ የሆነው አምባዬ « ትንሽ ኮምፒውተርን ሸሽቼው ነበር። ግን ይህንን የሚሰሩ ጓደኞች ስላሉኝ ተቀናጅተን መስራት እንደምንችል ርግጠኛ ነኝ» ይላል።

Infografik gute Vorsätze 2019 EN
 Addis Ababa City
ምስል Seyoum Getu/DW
China Neujahr Jahr des Tigers
የቻይና አዲስ አመት ምስል Costfoto/picture alliance

ልደት አበበ

ማንተጋፍቶት ስለሺ