1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

የአደባባይ ሰልፍ ጉዳይ

ሰኞ፣ መጋቢት 30 2016

የኢትዮጵያ መንግሥት ደጋፊዎች ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ ሥልጣን የያዙበትን ስድስተኛ ዓመት ምክንያት በማረግ ሰልፍ እየወጡ ነው። "ጦርነት ይቁም ሰላም ይስፈን" ሁሉን አቀፍ ውይይት እና ድርድር ከታጣቂ ኃይሎች ጋር ይካሄድ በሚል ሰልፍ ለማድረግ ሞክረው ከነበሩ ፖለቲከኞች መካከል የተወሰኑት ከወራት እሥር በኋላ የተፈቱት ባለፈው ሳምንት ነው።

https://p.dw.com/p/4eY95
የጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ መንግሥት ደጋፊዎች ሰልፍ በሸገር ከተማ
የኢትዮጵያ መንግሥት ደጋፊዎች ከግጭት መላቀቅ በተሳናቸው በኦሮሚያ እና በአማራ ክልሎች ጨምሮ በተለያዩ የሀገሪቱ ክፍሎች ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ ሥልጣን የያዙበትን 6ኛ ዓመት ምክንያት በማድረግ ሰልፍ እየወጡ ነው። ምስል Seyoum Getu/DW

የአደባባይ ሰልፍ ጉዳይ

ሰሞኑን አዲስ አበባን ጨምሮ በተለያዩ አካባቢዎች ጠቅላይ ሚኒስት ዐቢይ አሕመድ ወደ ሥልጣን የመጡበትን ስድስተኛ ዓመት ምክንያት በማድረግ የድጋፍ ሰልፎች እየተደረጉ ነው።

ባለፈው ሕዳር 30 ቀን 2016 ዓ. ም "ጦርነት ይቁም ሰላም ይስፈን" ሁሉን አቀፍ ውይይት እና ድርድር ከታጣቂ ኃይሎች ጋር ይካሄድ በሚል ሰልፍ ለማድረግ ሞክረው ከነበሩ የሰልፉ አስተባባሪ ፖለቲከኛች መካከል የተወሰኑት ከወራት እሥር በኋላ የተፈቱት ባለፈው ሳምንት ነው።

የኢሕአፓ ምክትል ሊቀ መንበር ተፈቱ ፣ ሊቀ መንበሩ ታሰሩ

በፈቃዳቸው ለመንግሥት ድጋፍ ለመስጠት የሚወጡ ሰዎች መብታቸው መሆኑን የጠቀሱ ያነጋገርናቸው የዲሞክራሲ ተቋም መሪ የሆኑ ሰው ትልቅ ችግር የሚሆነው በዚያው ልክ መንግሥትን "የሚቃወሙ ሰዎች ሰልፍ ሊወጡ የሚችሉበት እድል የሌለ መሆኑ ነው" ብለዋል።

ሕጎች ስለ ሰላማዊ ሰልፍ ምን ይላሉ?

የኢፌዴሪ ሕገ መንግሥት አንቀጽ ሰላሣ "ማንኛውም ሰው ከሌሎች ጋር በመሆን መሣሪያ ሳይዝ በሰላም የመሰብሰብ፣ ሰላማዊ ሰልፍ የማድረግ ነፃነትና፣ አቤቱታ የማቅረብ መብት አለው" ሲል ይደነግጋል።

የጠቅላይ ሚንስትር ዐቢይ አህመድ ስድስት የስልጣን ዓመታት እና ድጋፍ

"ይህ መብት የወጣቶችን ደህንነት፣ የሰውን ክብርና መልካም ስምን ለመጠበቅ፣ የጦርነት ቅስቀሳዎች እንዲሁም ሰብዓዊ ክብርን የሚነኩ የአደባባይ መግለጫዎችን ለመከላከል ሲባል በሚወጡ ሕጎች መሠረት ተጠያቂ ከመሆን አያድንም" በሚልም ተጠቅሷል፡፡

አዲስ አበባ ለመንግሥት ድጋፍ ለማሳየት የተደረገ ሰልፍ ላይ የተሰቀለ የጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ ፎቶ
ኢትዮጵያ ሦስት ክልሎች ያዳረሰ ብርቱ ጦርነት ውስጥ በገባችበት ወቅት የመንግሥት ደጋፊዎች አዲስ አበባን ጨምሮ ሰልፎች አድርገው ነበር። ምስል Tiksa Negeri/REUTERS

ምንም እንኳን ሰሞኑን የድጋፍ ሰልፎች ቢስተዋሉም "ጦርነት ይቁም ሰላም ይስፈን" በሚል የአደባባይ ሰልፍ ለማድረግ ሲንቀሳቀሱ ከነበሩ 13 ፖለቲከኞች አራቱ ሕዳር 27 ቀን ተይዘው ቆይተው የተለቀቁት ሰሞኑን ነው። ከእነዚህ መካከል የኢሕአፓ ተቀዳሚ ምክትል ሊቀ መንበር መጋቤ ብሉይ አብርሃም ሃይማኖት አንዱ ናቸው። በዚህ ምክንያት የሰልፍ ጉዳይ መንታ ስሜትን ፈጥሯል።

የአስተያየት ሰጪዎች ምልከታ

"ሕጋዊ የሆንን አካላት የጠራነውን ሰልፍ እንደ ወንጀል አድርገው በዚህ ሰዓት ሰልፍ አይቻልም ብለው እኛንም አሰሩ፣ ከዚያም በኋላ ማስፈራራት ፣ ማፈን፣ ማሰር ......በሚያሳፍር መልኩ ደግሞ ይሄን ሰሞን የስድስት ዓመቱን የለውጡ መንግሥት ያመጣቸው በጎ ሥራዎች በሚል ለራሳቸው ሰልፍ እያስወጡ ይገኛሉ" ብለዋል። 

ነጻነታቸውን ስለተነፈጉ ሰዎች የተደረገ ብሔራዊ ምርመራ

እነዚህን ሰዎች ለእሥር የዳረገው እንቅስቃሴ በነበረበት ወቅትም ሆነ አሁን የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ያፀደቀው የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ በተለይ በአማራ ክልል በሥራ ላይ ይገኛል። የመብቶች እና ዴሞክራሲ እድገት ማዕከል ሥራ አስፈፃሚ በፍቃዱ ኃይሉ በፈቃደኝነት የድጋፍ ሰልፍ ማድረግ መብት ቢሆንም ፣ ችግር የሚሆነው የሚቃወሙትንም እድል አለመስጠት ሲኖር መሆኑን ገልፀዋል።

ባሕር ዳር ከተማ
ሰልፍ ከተደረገባቸው ክልሎች መካከል በአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ የሚተዳደረው የአማራ ክልል ይገኝበታል። ምስል Simon Montgomery/robertharding/picture alliance

በተለይ ዛሬ ሰኞ በተራዘመ የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ ድንጋጌ ውስጥ በሚገኘው አማራ ክልል አንዳንድ ከተሞች ውስጥ መንግሥትን የሚደግፉ ሰልፎች መደረጋቸው ታይቷል። ፖለቲከኛው እንደሚሉት ግን እዚህ መዲና አዲስ አበባ እንኳን አዋጁ ብዙ ክልከላ ማድረጉን ገልፀዋል።

በኦሮሚያ ክልል የጸጥታው መደፍረስ እና ዳፋው

የሰላም ሚኒስቴር ሚኒስትር ዴኤታ የነበሩት አቶ ታዬ ደንደአ ከመታሠራቸው በፊት “የጦርነት ከበሮ በመታንበት አደባባይ ዜጎች በሰላማዊ ሰልፍ ጦርነትን እንዳይቃወሙ መከልከል መጥፎ ትርጉም አለው” ሲሉ ጥርነት ይብቃ የሚሉ ሰዎች ያንን ከማድረግ መከልከላቸውን ተቃውመው ጽፈው ነበር።

ምንም እንካን የፀጥታ እና ደኅንነት የጋራ ግብረ ኃይል እንቅስቃሴው "በሰላማዊ ሰልፍ ሽፋን አዲስ አበባ ውስጥ ሁከት እና ብጥብጥ ለመፍጠር" ታቅዶ የነበረ መሆኑን ቢገልጽም።

ይህ ለድጋፍ ሲፈቀድ፣ ለተቃውሞ የተነፈገው መብት ምን ያስከትል ይሆን በሚል አቶ በፍቃዱ ኃይሉን ጠይቀናቸዋል። መንግሥት ሲፈልግ ከፍተኛ ጥበቃ በማድረግ ሰልፎች የመደረጋቸውን፣ መፈክሮች የመስተጋባታቸውን ያህል በመንግሥት ላይም ቢሆን የተቃውሞ ድምጾች ሲኖሩ ክልከላዎች የመብዛታቸው አዝማሚያ መነጋገሪያ ሆኗል።

ሰለሞን ሙጬ

ሸዋዬ ለገሠ

እሸቴ በቀለ