1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል
ውዝግቦችአውሮጳ

የአውሮፓና ብሪታኒያ መሪዎች ስብሰባ በፓሪስ

ማክሰኞ፣ የካቲት 11 2017

ሦስት ዓመት የዘለቀው የሩሲያና ዩክሬን ጦርነት በመጨረሻም ከዩክሬን ጎን ቆመው በቆዩት አውሮፓና አሜሪካ መካከል ልዩነት ፈጥሮ የዲፕሎማሲና ወታደራዊ ውዝግብ አስክትሏል።

https://p.dw.com/p/4qgjX
Frankreich Paris 2025 | EU-Gipfel zur Ukraine | Macron empfängt Starmer
ምስል Aurelien Morissard/AP Photo/dpa/picture alliance

የአውሮፓና ብሪታኒያ መሪዎች ስብሰባ በፓሪስ

አዲሱ የአሜሪካ የመከላከያ ሴክሬታሪ ሚስተር ፔተ ሀግሴዝ ባለፈው ሳምንት ብራስልስ በኔቶ የሚኒስትሮች ስብሰባ ላይ ዩክሬንን አስመልክቶ ያሰሙት ንግግር አውሮፓውያኑ ያልጠበቁት ባይሆንም ግን ያስደነገጣቸው ነበር። ፕሬዝድንት ትራምፕም ከፕሬዝዳት ፑቲን ጋር ለድርድር መስማማታቸውን አሳውቀው ዲፖሎማቶቻቸው በሳኡዲ አረቢያ እንደሚገናኙ በገለጹት መስረት ዛሬ የሁለቱ አገሮች ከፍተኛ ዲፖሎማቶች ጦርነቱ የተከፈተባትን ዩክሪንና ዋና ተውናያኑን አውሮፓን ሳይጨምሩ የመጀመሪያ ስብሰባቸውን አካሂደዋል።

ስብሰባው የተጠራበት ምክኒያት

ዩክሬን በሩሲያ የተከፍተባትን ጦርነት አሜሪካና አውሮፓ በአንድነት ካዩክሬን ጎን በመቆም ወታደር ከማሳማራት ውጭ ያላደረጉት ነገርና የላኩት የጦር መሳሪያ ያልነበረውን ያህል፤ ዛሬ ፕሬዝዳንት ትራምፕ ብቻቸውን በማዕቀቦች ከተበተቡትና በዓለም አቀፉ የጦር ወንጀለኞች መዳኛ ፍርድ ቤት የእስር ማዘዣ ከወጣባቸው የሩሲያ መሪዎች ጋር ለድርድር መቀመጣቸው አውሮፓውያኑን ይይዙት ይለቁት  አስጥቷቸዋል እየተባለ ነው ። የፈረንሳዩ ፕሬዝዳንት ኢማኑኤል ማክሮን የብርታኒያውን ጠቅላይ ሚኒስተርንና የአውሮፓ ሕብረት ሙምማንትን ጭመሮ የ11 የሕብረቱ ሃገራትን መሪዎች በፓሪስ ለአስቸኳይ ስብሰባ ጠርተው ያወያዩትም ለዚህ አሜሪካ አዲስ ፖሊሲና እርምጃ የጋራ አቋም ለመውሰድና እራስን ማጠንከር ስለሚቻልበት ሁኔታ ለመወያየት እንደሆነ ተገልጿል። በሚካሄዱ ድርድሮችና የሰላም ስምምነቶች ዩክሬንና  አውሮፓ ከሌሉበት ዋጋ ሊኖረው እንደማይችል ለማስገንዘብ እንደሆነም ተነግሯል።

ዋናው የዩክሬንና ሩሲያ አጀንዳ ዩክሬንና አውሮፓ ባልተጋበዙበት በሪያድ ውይይት እየተደረገ ባለበት ወቅት ፓሪስ ላይ ስብሰባ መጥራቱ ትርጉም የለውም የሚሉ ወገኖች ያሉትን ያህል ፕሬዝዳንት ትራም አሜርካ ከአውሮፓ ጋር ለዓመታት የገነባቸውን ወዳጅነትና አጋርነት የሚንድ አቋም ሲያራምዱ ዝም ብሎ ማየት ተገቢ አይደለም በማለት የስብሰባውን አስፈላጊነትና ወቅታዊነት የሚገልጹ አሉ። በአውሮፓ ፓርላማ የውጭ ግንኑነት ኮሚቴ አባል የሆኑት ጀርመናዊቱ ሃናህ ኒውማን  በስብሰባው አስፈላጊነት ከሚያምኑት ውስጥ ናቸው፤ «እኛ አውሮፓውያንና ብራታኒያም አቋማችን ምን እንደሆነና በውይይትና ድርድሩ መሳተፍ ያለብን መሆኑን ማሳወቅና ግልጽ መልክት ማስተላለፍ አለብን» በማለት አውሮፓና ብሪታኒያ በዚህ ወቅት ተሰብስበው ይህን መልክት ማስተላለፋቸው ተገቢ መሆኑን ገልጸዋል

Russland Riad 2025 | US-russische Gespräche zum Nahen Osten mit Sergej Lawrow und Marco Rubio
ምስል Russian Foreign Ministry/Press S/picture alliance

የስብሰባው ውጤትና የአሜሪካ አቋም

ሆኖም ግን ስብሰባው የተፈለገውን የአቋም አንድነት እንዳላስገኘ ነው የተለጸው። መሪዎቹ ከሰላም ስምምነቱ በኋላ የዩክሬን ሰላም እንዴትና በማን ይረጋገጥ በሚለው ጥያቄ የጋራ መልስ የላቸውም ነው የተባለው። የብሪታኒያው ጠቅላይ ሚኒስተር ስታርመር ብርታኒያ በዩክሬን ሰላም ከተፈጠረ ብሪታኒያ ወታደሮቿን ከሌሎች አገሮች ወታደሮች ጋር በዩክሬን ልታሰማራ ትችላለች በማለት ይህ የሚሆነው ግን የአሜሪካ ድጋፍ መኖሩ ሲረጋገጥ ብቻ መሆኑን ገልጸዋል።  

አሚሪካ ግን በግልጽ ወታደሮቿን እንደማታሰማራ ብቻ ሳይሆን የሌሎችም በዩክሬን የሚሰማሩ ወታድሮች ስምሪትም በኔቶ ማቀፍ ውስጥ ሊሆን እንደማይችል ነው የመከላከያ ሲክሬታሪው ሄግሴዝ ያሳወቁት፤ «በዩክሬን ሰላም የሚያስከብሩ ወታደሮች  የሚሰማሩ ከሆነ፤ ስምሪቱ ከኔቶ ማዕቀፍና ከድርጅቱ አንቅጽ አምስት ድንጋጌ ውጭ መሆን ይኖረብታል» በማለት የሀገራቸውን አዲስ አቋም በግልጽ አስቀምጠዋል። የአውሮፓ አገሮችም ወታደር በማሰማራቱ በኩል ያልተስማሙ ሲሆን  የተስማሙት ለዩክሬን የሚሰጡትን እርዳታ አጠናክሮ ለመቀጠልና የራሳቸውን የመከላከያ ሀይልም በጀት በማሳደግ ጭምር ማጠናከር በሚለው ላይ መሆኑ ታውቋል።

የሪያዱ ስብሰባ ተጨማሪ ፋይዳዎች

  በሌላ በኩል ዩክሬንና አውሮፓን አግልሎ ዛሬ በሪያድ የተካሄደው የሩሲያና አሜሪካ ልዑካን ስብሰባ፤ ለዩክሬንና ሩሲያ የሰላም ድርድር የመጀመሪያ ምዕራፍ እንደሚሆን ተገምቷል። ስብሰባው የአሜሪካና ሩሲያን ግንኙነት ዳግም ያስቀጠለና ለአስተናጋጇ ሳኡዲ አረቢያና መሪዎቹም ጥሩ ስምና ገጽታ ያስገኘ እደሆነም ተገልጿል።

ገበያው ንጉሤ

ሸዋዬ ለገሠ

ኂሩት መለሰ