1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል
ሕግ እና ፍትሕኢትዮጵያ

የአቶ ታዬ ደንደዓ እና የእነ ቀሲስ በላይ የችሎት ውሎ

ሐሙስ፣ ግንቦት 29 2016

የፌዴራል ከፍተኛ ፍርድ ቤት ልደታ ምድብ ሶስተኛ የሙስና ወንጀል ችሎት ቀሲስ በላይ መኮንን እና ሌሎች አራት ተከሳሾች በተጠረጠሩበት «ከባድ የአታላይነት የሙስና ወንጀል እና ሰነዶችን አስመስሎ የማዘጋጀት» የክስ ሂደት ላይ በሰጠው ብይን ተከሳሾች ማረሚያ ቤት እንዲወርዱ አዟል፡፡

https://p.dw.com/p/4gkgn
ፍርድ ቤቱ በአቶ ታዬ ደንደአ ጉዳይ ብይን ለመስጠት ተለቃጭ ቀጠሮ ሰጥቷል
በልደታ ከፍተኛ ፍርድ ቤት በዋለው ችሎት የቀድሞ የሰላም ሚኒስትር ዴኤታ አቶ ታዬ ደንደዓ ከጠበቃው ጋር ቀርበው አቃቤ ህግ ያቀረበባቸውን የሰው ምስክር አድምጠዋል፡ምስል Seyoum Getu/DW

የአቶ ታዬ ደንደዓ እና የእነ ቀሲስ በላይ የችሎት ውሎ

ዛሬ አዲስ አበባ ውስጥ ያስቻለው የፌደራል ከፍተኛ ፍርድ ቤት ልደታ ምድብ 1ኛ የሕገመንግስትና ሕገ-መንግስት ስርዓት ላይ የሚፈጸሙ ወንጀል ጉዳዮች ችሎት የቀድሞ የሰላም ሚኒስትር ዴኤታ ታዬ ደንደአ ላይ የቀረበውን የአቃቤ ህግ ምስክር አድምጧል፡፡

ፍርድ ቤቱ በዛሬው ችሎት ከአቶ ታዬ ቤት ተገኝቷል በተባለው በህጋዊነት ያልተመዘገበ የጦር መሳሪያ ክስ ላይ የቀረቡትን የአቃቤህግ ምስክር በመስማት ጥፋተኝነት ላይ ውሳኔ ለመስጠትም ቀጣይ ቀጠሮ ይዟል፡፡

በሌላ በኩል ከኢትዮጵያ ንግድ ባንክ የአፍረካ ህብረት የሂሳብ ቁጥር አስመስሎ በተሰናዳ ሀሰተኛ ሰነድ ገንዘብ ለማውጣት ሞክረዋል በሚል ክስ የቀረበባቸው እነ ቀሲስ በላይ የዋስትና መብታቸው በመከልከሉ ወደ ማረሚያ ቤት እንዲወርዱ ዛሬ ተበይኗል፡፡

በአቶ ታዬ ደንደዓ ላይ የቀረበው የአቃቤ ህግ ምስክር

ዛሬ በልደታ ከፍተኛ ፍርድ ቤት በዋለው ችሎት የቀድሞ የሰላም ሚኒስትር ዴኤታ አቶ ታዬ ደንደዓ ከጠበቃው ጋር ቀርበው አቃቤ ህግ ያቀረበባቸውን የሰው ምስክር አድምጠዋል፡፡ የአቃቤ ህግ ሁለት ምስክሮች ዛሬ ችሎቱ ፊት እንደቀረቡ ተከሳሽ አቶ ታዬ ደንደዓ ዛሬ ለምስክርነት የቀረቡ ሁለት ምስክሮች ወንዶች ቢሆኑም ከዚህ በፊት በምርመራ ወረቀት ላይ የነበሩ ምስክሮች አንድ ወንድ እና አንድ ሴት መሆናቸውን ያመለክት ነበር በሚል ተቃውመውታል፡፡

ምስክሮቹ ቃላቸውን እንዲሰጡ ከመፈቀዱ አስቀድሞም ችሎቱ ለተከሳሽ እና ጠበቃቸው በሰጠው እድል ተከሳሹ እና ጠበቃው የቀረቡት ሁለቱ ምስክሮች በእለቱ በቦታው እንዳልነበሩ፤ ብሎም ከቀረቡት ምስክሮች አንዱ በሴት ጾታ ወ/ሮ በሚል በምርመራ መዝገብ ላይ ቀርቦ እንደነበር አንስተው ተቃውመዋል፡፡

በዚህ ላይ አቃቤ ህግ አስተያየት እንዲሰጥበት ችሎቱ መጠየቁን ተከትሎ አቃቤ ህግ የምስክሮችን ማንነት በተመለከተ የመንግስት ሰራተኛ መሆናቸውን ገልጾ በምርምራው ላይ የቀረበው የጾታ ልዩነት ቀላል የአጻጻፍ ስህተት ነው ብሏል፡፡

ተከሳሽ እነዚህን የቀረቡትን ሁለት ምስክሮች እንደማያውቃቸውም ከገለጹት በኋላ በችሎቱ በተሰየሙ ዳኞች የቀረበውን የምስክሮች የአድራሻ እና ከጾታ ጋር የተያያዙትን ውዝግቦች ለማጥራት መታወቂያቸውን ከተመለከተ በኋላ የምስክሮቹ ቃል እንዲሰማ ፈቅዷል፡፡

ቃለመሃላ ፈጽመው ምስክርነታቸውን ለችሎቱ የሰጡ ሁለቱ የአቃቤ ህግ ምስክሮች ታህሳስ 01 ቀን 2016 ዓ.ም. ከምሽቱ 5፡00 የአቶ ታዬ ደንደዓ መኖሪያ ቤት ስፈተሽ አንድ ታጣፊ ክላሽ ከመሰል ሁለት ካዝና ጥይት (ስቆጠርም ከ60 ጥይት) ጋር እንዲሁም አንድ ሽጉጥ ከአቶ ታዬ ቤት መገኘቱን አይተናል በሚል ተናግረዋል፡፡ ምስክሮቹ ለችሎቱ ቃላቸውን በሚሰጡበት ወቅትም ከተከሳሽ ጠበቃ እና በችሎቱ ከተሰየሙ ዳኞች በርካታ የመስቀለኛ ጥያቄዎች ቀርቦላቸው ነበር፡፡

የምስክሮች ቃል ተሰምቶ እንዳበቃም አቃቤ ህግ ዛሬ የቀረበውን የሰው ምስክር ከዚህ በፊት ከቀረቡ የሰነዶች ማስረጃዎች ጋር በማበር የጥፋተኝነት ብይን ይሰጥልኝ ሲል ጠይቋል፡፡ ችሎቱም የሁለቱን ምስክሮች ቃል ሰምቶ ካበቃ በኋላ በሁለቱም ወገን የተሰጡትን አስተያየቶች ተቀብሎ መዝገቡን መርምሮ ውሳኔ ለመስጠት ለሰኔ 18 ቀን 2016 ዓ.ም. ተለዋጭ ቀጠሮ ሰጥቷል፡፡

የአቶ ታዬ ደንደዓ የሰብዓዊ መብት ቅሬታዎች

ችሎቱ የዛሬው ዋና ጉዳይ የሆነውን የምስክሮች ቃል የማድመት ሂደትን ካጠናቀቀ በኋላ ተከሳሽ አቶ ታዬ ደንደዓ ከሰብዓዊ መብት ጋር ተያይዞ አልተሟሉልኝም ያሉትን ቅሬታዎች ለችሎቱ አቅርበዋል፡፡ “የእኔም የባለቤትም የባንክ ሂሳብ ተዘግቶ ለስድስት ወራት ያህል እስካሁን ባለመከፈቱ ልጆቼ እና ቤተሰቦቼ ችግር ላይ ወድቀዋል” ያሉት አቶ ታዬ ይህ እንዲያበቃ ፍርድ ቤቱ ለሚመለከተው አካል ትዕዛዝ እንዲሰጥላቸው ጠይቀዋል፡፡ አቶ ታዬ በታህሳስ አንድ ቀን ተጀምሮ ታህሳስ 24 ቀን የተጠናቀቀው የቀረበባቸው የምርመራ ሂደት እስከ ሚያዚያ ወር ቆይቶ ክስ መከፈቱንም ያልተገባ በሚል ተቃውመው አስተያየት ሰጥተዋል፡፡

አቶ ታዬ ሁለት ከመንግስት ጋር ቅርበት ያላቸው መገናኛ ብዙሃንን በስም ጠቅሰው የስም ማጠልሸት ተግባር እንደፈጸሙባቸው በመግለጽ ቀርቦብኛል ባሉት የስም ማጥፋት ላይ የማስተባበያ ዘገባ እንዲሰሩም ችሎትን ጠይቀዋል፡፡

ፍርድ ቤቱ በጉዳዩ ላይ ብይን ለመስጠት ተለዋጭ ቀጠሮ ሰጥቷል
አቶ ታዬ ደንደአ የቀድሞዉ የሠላም ሚንስትር ደ ኤታ በቀረበባቸዉ ክስ ዛሬ የአቃቤ ሕግ ምሥክሮች ቃላቸዉን ሰጥተዋልምስል Million Haileselasi/DW

ከዚህም በተጨማሪ ተከሳሹ አቶ ታዬ ከዚህ በፊት ግንቦት 13 ቀን 2016 ዓ.ም. በዋለው ችሎት ከዚህ በፊት በምርመራ ጊዜ በኤግዚቢትነት የተያዙ ብዙ ንብረቶች ብመለሱም ሁለት የእጅ ስልኮቻቸው፣ አንድ ላፕቶፕ ኮምፒዩተር እና መደመር ሲመረመር የሚል ረቂቅ ጽሁፍ ንብረቶቻቸው በመሆናቸው እነዲመለሱላቸው ፍርድ ቤቱ ትዕዛዝ እንዲሰጥላቸው ብጠይቁም እስካሁን አለመፈጸሙንም አክለው ገልጸዋል፡፡

ፍርድ ቤቱም አቶ ታዬ ዘርዝረው የጠየቁአቸው እነዚህ የመብት ጥያቄዎች በጽሁፍ እንዲቀርቡለትና ከዚያም ትዕዛዝ እንደሚሰጥ አስታውቆ የዛሬን ችሎት ደምድሟል፡፡

የፍትህ ሚኒስቴር የተደራጁና ድንበር ተሻጋሪ ጉዳዮች ዳይሪክቶሬት ዐቃቤ ሕግ በተከሳሽ አቶ ታዬ ደንደአ ላይ በ1996 ዓ.ም የወጣውን የወንጀል ህግ አንቀጽ 251/ሐ እና አንቀጽ 257/ሰ ስር የተመላከተውን ድንጋጌ እና የጦር መሳሪያ አዋጅን መተላለፍ የሰላም ሚኒስትር ዴኤታ ሆነው ሲሰሩ የሀገርን፣ የመንግስት እና የህዝብን ደህንነት ማስጠበቅ፣ ማረጋገጥ ሲገባቸው ይህን ወደጎን በመተው ከመንግስት ጋር ጦርነት ውስጥ የገቡትን የ“ኦነግ ሸነ እና ፋኖ” ዓላማን ለማሳካት ተንቀሳቅሰዋል፤ በስማቸው በተከፈተ ማህበራዊ ሚዲያ ላይ መሰል ይዘት ያለው መልእክቶችን አስተጋብተዋል የሚል ሶስት ክሶች ማቅረቡ ይታወሳል፡፡

ተከሳሹ ፍቃድ ሳይኖራቸው የጦር መሳሪያ አዋጁን በመተላለፍ በታኅሣስ 1 ቀን 2016 ዓ.ም ከረፋዱ 5:00 ሰዓት ላይ በልደታ ክ/ከተማ ወረዳ 6 በሚገኝ መኖሪያ ቤታቸው ውስጥ በተደረገ ብርበራ አንድ ታጣፊ ክላሽንኮቭ ከሁለት የክላሽንኮቭ ካዝና ከ60 ጥይት ጋር ተይዞባቸዋል መባሉም ይታወቃል።

የእነ ቀሲስ በላይ መኮንን የፍረድ ቤት ውሎ

በሌላ በኩል በሚያዚያ ወር መጀመሪያ የአፍሪካ ኅብረት ግቢ ውስጥ በሚገኘው የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ ቅርንጫፍ በአካል በመቅረብ "ከኅብረቱ የክፍያ ሰነድ ጋር ተመሳስለው የተዘጋጁ" በተባሉ ሀሰተኛ ሰነዶች በመጠቀ ከስድስት ሚሊዮን ዶላር በላይ ከህብረቱ የባንክ ሒሳብ ወደ ሌላ ሒሳብ ለማዘዋወር ሲሞክሩ ተገኝተዋል በሚል በፖሊስ ተይዘው ክስም የተመሰረተባቸው ሊቀ ዐዕላፍ ቀሲስ በላይ መኮንን እና ሌሎች ተከሳሾች ዛሬ ማረሚያ ቤት እንዲወርዱ ተበይኖባቸዋል።

ዛሬ ያስቻለው የፌዴራል ከፍተኛ ፍርድ ቤት ልደታ ምድብ ሶስተኛ የሙስና ወንጀል ችሎት ቀሲስ በላይ መኮንን እና ሌሎች አራት ተከሳሾች በተጠረጠሩበት «ከባድ የአታላይነት የሙስና ወንጀል እና ሰነዶችን አስመስሎ የማዘጋጀት» የክስ ሂደት ላይ በሰጠው ብይን ተከሳሾች ማረሚያ ቤት እንዲወርዱ አዟል፡፡

በክሱ ላይ ዐቃቤ ሕግ ምስክሮች እንዲሰሙለት ባቀረበው ጥያቄ መሰረት ፍርድ ቤቱ የምስክሮችን ቃል ለመስማት ለሰኔ 26 እና 27 ቀን 2016 ዓ.ም ተለዋጭ ቀጠሮ ሰጥቷልም።

እነ ሊቀ አዕላፍ ቀሲስ በላይ መኮንን ከዚህ በፊት ያቀረቡት የወስትና መብት ጥያቄ የቀረበባቸው ክስ ከአስር ዓመት በላይ የሚያስፈርድ ከባድ ክስ ነው በሚል የዋስትና ጥያቄያቸው ተቀባይነት ሳያገኝ መቅረቱ አይዘነጋም፡፡

ሥዩም ጌቱ

ነጋሽ መሐመድ

ሸዋዬ ለገሰ