ረቡዕ፣ ጥቅምት 16 2009
በተመሳሳይ አዲስ ስታንዳርድ የተሰኘዉ ወርኃዊ የእንግሊዝኛ መጽሔት፣ በዚሁ ምክንያት ሕትመቱን ለማገድ መገደዱን በትላንትናዉ ዕለት ማሳወቁን ዘግበናል።የኢትዮ/ምህዳር ዋና አዘጋጅ የሆኑት አቶ ጌታቸዉ ወርቁ ይህን ችግር ለመፍታት ወደ መንግስት ኮሙኒኬሼን ጽሕፈት ቤት እና የፍትህ ሚኒስቴር ሄደዉ አቤቱታ ቢያቀርቡም ምንም መፍትሄ
እንዳላገኙ ይናገራሉ። ወደኢትዮጵያ አሳታሚዎች ማኅበርም ይህኑ አቤቱታችን ወስደን ነበር ይላሉ አቶ ጌታቸዉ።
ይህንን ለማጠራትና የበለጠ መረጃ ለመማግኘት ከመንግሥትም ሆነ ከአሳታሚዎች ማኅበር በኩል ያደረግነዉ ሙከራ ሳይሳካልን ቀርቷል። አዋጁ ሌሎች ሀገሪቱ ዉስጥ ያሉት የንግድም ሆነ የፖለቲካ የኅትመት ዉጤቶች ላይ፣ በተለይም ሃሳብን በነፃ ማንሸራሸር ላይ ምን ተፅዕኖ ይኖረዋል ብለን በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ የጋዜጤኝነትና ኮሙኒኬሼን ትምህርት ዘርፍ ዲን የሆኑት ዶክተር አብዲሳ ዜራይን አነጋግረን ነበር። የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ ሲደነገግ የሲቪልና የዴሞክራሲ መብቶችን ያቅባል የሚሉት ዶክተር አብዲሳ ይህም «እንደፈለጉ የመጻፍ፣ የመተቸትና አማራጭ ሃሳብ ማቅርብን ይገድባል» ይላሉ።
ከ1997 ምርጫ በኋላ በኢትዮጵያ በተለያዩ ሁኔታዎች የፕሬስ ዉጤቶች ችግር ዉስጥ የገቡበት ምህዳር እንዳለ የሚናገሩት ዶክተር አብዲሳ የአስቸኳይ ጊዜ አዋጁ ግን አባብሶታል ይላሉ።
የፌስቡክ ተከታታዮቻችንን አዋጁ በኅትመት ዉጤቶች ላይ ስላስከተለዉ ተፅዕኖ አስተያየታችሁን እንዲያጋሩን ጠይቀን፤ አንዳንዶች «የግል ኅትመቶች ኃላፊነት የጎደላቸው ናቸው፣ ለ 25 ዓመታት ጥላቻን ነው የሰበኩን የፈጠራ ወሬ ነው የመገቡን» ሲሉ፣ ሌሎች ደግሞ «ምን ያልተዘጋ ነገር አለ፣ ሀገራችን ሁሉ ነገር የተበላሸ ነው ሀገራችን ወዴየት እንደምታመራ እንጃ ፈጣሪ ይወቅ» የሚሉ አስተያየቶችን ሰንዝረዋል። «እባካችሁ እንኑርበት፤» ያሉንም አሉ።
መርጋ ዮናስ
ሸዋዬ ለገሰ