የአሜሪካ ምርጫ ውጤት በሚወስኑት ሰባቱ የአሜሪካ ግዛቶች
ሰኞ፣ ጥቅምት 25 2017በነገው እለት የሚደረገውን የአሜሪካ ምርጫ ውጤት በሚወስኑት ሰባት የአሜሪካ ግዛቶች ውስጥ ሁለቱም እጩ ተወዳዳሪወች ያለብዙ ልዩነት ተፋጠው እንደሚገኙ ተገለጸ። የግዛቶቹ ነዋሪወች ከሁለቱም ፓርቲወች የተውጣጡ፣ በአሰፋፈራቸው፣ በጾታቸውና በዘራቸው መነሻነት የምርጫ አቅጣጫቸውን የሚወስኑ መሆኑም ተጠቅሷል። ደውቸ ወለ ያነጋገራቸው ከነዚሁ ወሳኝ ግዛቶች ውስጥ በአራቱ፣ በፔንሲልቫኒያ፣ በጆርጅያ፣ በኔቫዳ እና በሰሜን ካሮላይና የሚኖሩ ትውልደ ኢትዮጵያውያን መራጮች የዘንድሮው ፉክክር ከወትሮው በተለየ መልኩ የተካረረና፣ ግዛቶቹን ማን እንደሚያሸንፍ ለመገመት አስቸጋሪ የሆነበት እንደሆነ ገልጸዋል።
አሜሪካውያን ቀጣዩን ፕሬዝዳንት ለመምርጥ ሰአታት ቀርተዋቸዋል። ያም ሆኖ ማነም ሰው በእርግጠኝነት ቀጣዩ ፕሬዝዳንት ማን ሊሆን እንደሚችል ለመገመት በማይችልበት እጅግ ተቀራራቢ ደረጃ ላይ ናቸው። ለዚህ ደግሞ በተለምዶ ‘ስዊንግ ስቴት’፣ በመባል የሚጠሩት፣ የኋይት ሃውስን ቁልፍ የያዙት ሰባት የአሜሪካ ግዛቶች ዋና አውደ ፉክክርናቸው። በጣም በጠበበ ልዩነት ሁለቱም እጩወች የተፋጠጡባቸው ግዛቶች ፔንሲልቫንያ፣ ሚቺጋን፣ ዊስኮንሰን፣ ኔቫዳ እና ሰሜን ካሮላይና ናቸው።
እነዚህ ግዛቶች የፉክክር ቀጠና ተብለው የሚታወቁበት ምክንያት በየትኛውም ምርጫ ወቅት ሁልጊዜ ወደ አንድ ፓርቲ ወይም ወደ አንድ እጩ የማያዘነብሉ፣ ሁሉም እጩወች ጥረው፣ ግረው፣ ቀስቅሰውና ለምነው የሚያገኟቸው መሆናቸው ነው። የተለያየ ዳራ ያለው ህዝብ የሚኖርባቸው፣ የሚቀያየር የኢኮኖሚ ስጋት እና የፖለቲካ ትኩረት የሚፈራረቅባቸው፣ ለመተንበይ የማይመቹ፣ ኋይት ሃውስን ለማሸነፍ ዋና መንገድ በመሆናቸውም ጭምር ነው። እናም እንደ ሁል ጊዜው፤ ዶናልድ ትራምፕም ሆኑ ከማላ ሃሪስ በነዚሁ ግዛቶች ላይ የምረጡኝ ቅስቀሳቸውን አጧጡፈዋል። ብዙ ገንዘብ አፍስሠው አየሩን በማስታወቅያ አጨናንቀዋል። በያንዳንዱ የምርጫ ዞን ተመላልሰው ቀስቅሰዋል። ከነዚሁ ግዛቶች ውስጥ አንዷ የሆነችውና ሁለቱም እጩወች ያለማናቸውም መሪነት የተፋጠጡባት ግዛት ፔንሲልቫንያ ናት።የግዛቷ ነዋሪ የሆኑት ትውልደ ኢትዮጵያዊው መራጭ አቶ ፈቃዱ የህዝቡ ድጋፍና የሚመረጥበት ጉዳይ ትኩረት ከቦታ ቦታ ይለያያል ባይ ናቸው።
በግዛቷ የሚኖሩ ኢትዮጵያውያን ከዚህ ቀደም ተደራጅተው ዲሞክራቶችን ሲደግፉ መቆየታቸውን የገለጹት አቶ ፈቃዱ፣ በተለይ ከጾታና ከማህበራዊ ጉዳዮች ጋር በተያያዘ ዲሞክራቶች የያዙት አቋም ብዙወችን ወደ ሪፐብሊካን አልያም በዘንድሮው ምርጫ ወዳለመሳተፍ እየገፋቸው መሆኑን ገልጸዋል። ሌላዋ የፉክክር መድረክ የሆነችው ግዛት ኔቫዳ ናት። ደማቋን ላስቬጋስን ጨምሮ በአብዛኛው አገልግሎት ሰጪ ተቋማት ላይ ያተኮረ ኢኮኖሚ ያላት ኔቫዳ፣ በዘንድሮውም ምርጫ ወሳኝ ሚና ይዛ የሁለቱም ተፎካካሪወች ማዕከል ሆናለች። አቶ እስክንድር ወርቁ በላስ ቬጋስ፣ ኔቫዳ ነዋሪ ናቸው። በኔቫዳ ግዛት ውስጥም የህዝቡ አሰፋፈር በድምጽ አሰጣጡና በውጤቱ ላይ ሚና እንዳለው አቶ እስክንድር ጠቁመዋል።
በላስ ቬጋስ ውስጥ ብዙ ትውልደ ኢትዮጵያውያን መኖራቸውን ያስታወሱት አቶ እስክንድር፣ አብዛኛወቹ ለዲሞክራቶች፣ ከግብር እና ከኢኮኖሚ አንጻር ምርጫውን የሚያዩት ደግሞ ለሪፐብሊካኖች እንደሚመርጡ ተናግረዋል። ሌላዋ ግዛት ጆርጅያ ናት። ባለፉት አራት አመታት በተለይ የአፍሪካ አሜሪካውያን የፖለቲካ ተሳትፎ ሰፍቶ ግዛቷ ከቀይ፣ ሪፐብሊካን ግዛትነት ጎራ ወጥታ እንዲህ በቀላሉ ወደማትወሰድ፣ ውድ ግዛትነት መቀየሯን የአትላንታ፣ ጆርጅያ ነዋሪ የሆኑት ዶ/ር ማሾ አብረሃ ነግረውኛል። አያይዘውም በዘንድሮው ምርጫ ማ፤ ማንን ይመርጣል የሚለው ጥያቄ የሚመለሰው በጾታ፣ በእድሜና በዘር አወቃቀር ጭምር እንደሆነ ጠቁመዋል። ዶ/ር ማሾ፤ ሃበሻ ለሃሪስ የሚል የፖለቲካ የድጋፍ ቡድን ቅስቀሳ እያደረገ እንደሆነና ኢኮኖሚና፣ የስደተኞች ህግ ዋና ርዕሰ ጉዳዮች መሆናቸውም ጠቁመዋል።
ሰሜን ካሮላይና ሌላዋ ወሳኝ ግዛት ናት።በአብዛኛው ወግ አጥባቂ ህዝብ ያለባት ግዛት እንደሆነች የግዛቷ ነዋሪ የሆኑት ማህሌት ተሾመ ገልጸዋል። መራጩ ህዝብ በአብዛኛው ወደ ሪፐብሊካን የማድላት አዝማምያ ያለው ቢሆንም በዘንድሮው ምርጫ ግን ውጤቱ ወዴት አቅጣጫ ሊሄድ እንደሚችል ለመገመት ያዳግታል ብለዋል።
እነዚህ ወሳኝ ግዛቶች ነገ በሚደረገው ምርጫ የአሜሪካንን ፕሬዝዳንት ማንነት የሚወስኑ ናቸው። የሁሉም መርጭ ህዝብ ተስፋ ከሁለቱ እጩወች አንዳቸው በማያወላዳ ሰፊ ልዩነት አሸንፈው፣ በምርጫው እለት አሸናፊው ይለይ ዘንድ ነው። ግና የዘንድሮው ምርጫ ማንም ሰው እርግጠኛ ያልሆነበት፣ እስካሁን የተደረጉ መጠይቅ ውጤቶች ሁለቱንም እጩወች ለመለየት በሚከብድ ተቀራራቢ ውጤት ላይ ያስቀመጡበት፣ ዶናልድ ትራምፕም በምርጫው ከተሸነፉ ውጤቱን አልቀበልም ሊሉ የሚችሉበትን መደላድል ከወዲሁ ያስቀመጡበት እለት ላይ ነው ያለነው። እናም ሁሉም አሜሪካዊ ነገ ምን ይዛ እንደምትመጣ ለማየት በጉጉት እየጠበቀ ነው። ውጤቱን አብረን የምናየው ይሆናል።
አበበ ፈለቀ
አዜብ ታደሰ
ነጋሽ መሐመድ