የአሜሪካዋ ዉጪ ጉዳይ ሚንስትር በአፍሪቃ
ረቡዕ፣ ሐምሌ 25 2004
የዩናይትድ ስቴትስ ዉጪ ጉዳይ ሚንስትር ሒላሪ ክሊንተን በተለያዩ የአፍሪቃ ሐገራት የሚያደርጉትን ጉብኝት ትናንት ማታ ከሴኔጋል ጀምረዋል።ክሊንተን አስራ-አንድ ቀናት በሚፈጅ ጉዟቸዉ ሰባት የአፍሪቃ ሐገራትን ይጎበኛሉ።የጉብኝቱ አላማ ከሐገር ሐገር ቢለያይም ጥቅል ተልዕኮዉ ግን፥ የአሜሪካ ባለሥልጣናት እንዳሉት፥ አፍሪቃዉያን ሠላምና መረጋጋት ለማስፈንና ዲሞክራሲያዊ ሥርዓት ለመገንባት የሚያደርጉትን ጥረት ለማበረታት ነዉ።ርዕሠ-መንበሩ ፕሪቶሪያ ደቡብ አፍሪቃ የሚገኘዉ የፀጥታ ጥናት ተቋም ሐላፊ ዶክተር ጃኪ ሲለርስ እንደሚሉት ደግሞ ጉብኙ የአፍሪቃ ተፈላጊነት እያደገ መምጣቱንም አመልካች ነዉ።ነጋሽ መሐመድ አጭር ዘገባ አለዉ።
ጉብኝቱ በሁለት ነገር ከወትሮዉ ይለያል።ብዙ ሐገሮችን በመጎብኘት ከአሜሪካ ዉጪ ጉዳይ ሚንስትሮች ሁሉ ወይዘሮ ሒላሪ ክሊንተንን አንደኛ ያደርጋቸዋል።በሥፖርተኞች ቋንቋ ሪከርድ ይሰብራሉ።-አንድ።
በሚቀጥለዉ ዓመት መግቢያ ጡረታ ለመዉጣት ሥላሰቡ በዘመነ-ሥልጣናቸዉ የተባበሩዋቸዉን የአፍሪቃ መሪዎች ያመሰግናሉ።ይሰናበታሉም።ሁለት።ግን የፖለቲካ ተንታኝ ዶክተር ጃኪ ሲለርስ እንደሚሉት ጉብኝቱ ከዚሕም በላይ ነዉ።
«እንደሚመስለኝ ይሕ ከስንብት በጣም የበለጠ ነዉ።ባለፉት አንድና ሁለት ዓመታት አፍሪቃ በዓለም ያላት ተቀባይነት እየተለወጠ ነዉ።በዩናይትድ ስቴትስ ጭምር።ቀደም ሲል አፍሪቃ የምትታየዉ እርዳታ የማይበቃት ጉድ፥ በሙስና የተዋጠችና የአሸባሪዎች መናኸሪያ ተደርጋ ነበር።አሁን ግን አፍሪቃ በዓለም አቀፍ ያላት ተፈላጊነት እየጨመረ ነዉ።ለመወረቻነት፥ ለጥሬ ዕቃ ምንጭነት ትፈለጋለች።ሐምሳ አራቱ ሐገራት በተባበሩት መንግሥታት ጠቅላላ ጉባኤ ያላቸዉ ተፈላጊነት እየበረታ ነዉ።»
ይሕ የአፍሪቃ ለዉጥ-ዶክተር ሲለርስ እንደሚሉት የዩናይትድ ስቴትስን ትኩረትን ስቧል። ሥለ አፍሪቃ ያላትን መርሕና አመለካከትም ለዉጧልም።አሜሪካኖችን የሳበዉ የአፍሪቃ ለዉጥ መሠረት ግን በርግጥ አፍሪቃዉያን እራሳቸዉን ያመጡት ነዉ? ወይስ ቻይና እና ሕንድን የመሳሰሉት አዳዲሶቹ ሐብታሞች አፍሪቃ መግባታቸዉ?
«በጣም ጥሩ ጥያቄ ነዉ።ምክንያቱም ዩናይትድ ስቴትስ ከቻይና ጋር የገጠመችዉ ፉክክር የአሜሪካንን የዉጪ መርሕ ማረቁ ምንም ጥርጥር የለዉም።የአፍሪቃን ገበያ ለማግኘት በዩናይትድ ስቴትስና በቻይና መካካል የሚደረገዉ ዉድድርም እየተጠናከረ ነዉ።ግን ይሕ ብቻ አይደለም አፍሪቃ ለአሜሪካ ሸቀጥ ጥሩ ቅምጥ ገበያነቷም ግንዛቤ አግኝቷል።»
ወይዘሮ ክሊንተን የደቡብ ሱዳኑን ፕሬዝዳት ሳልቫ ኪርን ሲያነጋግሩ ሁለቱ ሱዳኖች በሚያደርጉት ድርድር «የታየዉን ቀና ለዉጥ-ያበረታታሉ» ይላል-የአሜሪካ ባለሥልጣናት መግለጫ።የሱዳኖች ድርድር ግን ከአዲስ አበበባ ወደ ባሕርዳር ከመዛወሩ ሌላ በነበረበት እየረገጠ ነዉ።
እና የሚበረታታዉ ዉጤት በርግጥ ግራ ነዉ።የትልቂቱ ሐገር ትልቅ ዲፕሎማት ጁባን መጎብኘት ግን ለአዲሲቱ ደሐ-ሐገር ትልቅ ትርጉም አለዉ።የትልቂቱ ሐገር ትልቅ ጥቅምም ከጁባና ካርቱም በላይ ድፍን ሳሔልን ያጠቃልላል።
«የሱዳኑን ጦርነት ለማስቆምና በዉጤቱም ሱዳንን ሰሜንና ደቡብ ሱዳን በመክፈሉ ሒደት ዩናይትድ ስቴትስ ትልቅ ሚና ተጫዉታለች።ሥለዚሕ እነሱ አሜሪካኖች በጣም ጠቃሚ ናቸዉ።ዩናይትድ ስቴትስ ሱዳን ዉስጥ ተፅኖ አላት።ከዳካር እስከ ሱዳን በሚደርሰዉ የሳሔል አካባቢ በቅርብ መከታተል ትፈልጋለች።በሳሔል አካባቢ ያለዉ አለመረጋጋት ዩናይትድ ስቴትስን ያሰጋል።»
በሳሔል አካባቢ የተበረካተዉ የአሸባሪዎች፥ የሽፍቶችና የአደንዛዥ ዕፅ ነጋዴዎች ዝዉዉር ሲለርስ እንደሚሉት አሜሪካኖችን ሲበዛ ያሳስባል።ክሊንተን በናይሮቢ ቆይታቸዉ ከኬንያ ሌላ የሶማሊያዉን ፕሬዝዳት ሼኽ ሸሪፍንም ያነጋግራሉ።
«ኬንያና ኢትዮጵያ ባካባቢዉ ለዩናይትድ ስቴትስ ዋነኛ ተባባሪዎች ናቸዉ።እርግጥ ደቡብ ሱዳንም አለች።ግን ደሐ፥ አቅመ ትንሽና አዲስ ሐገር ናት።እና አሜሪካ በሶማሊያ ሠላም ለማስፈን በሚደረገዉ አፍሪቃ መራሽ ጥረት መካፈል፥ መደገፍም ትሻለች።በተለይ ኬንያ፥ አሚሶምና ኢትዮጵያ የሚደርጉትን ጥረት።»
ክሊንተን ኢትዮጵያን ግን አይጎበኙም።እርግጥ ነዉ የሚሰናበቱት፥ የሚያመሰግኑት የኢትዮጵያ መሪም አዲስ አበበ መኖራቸዉ አጠራጣሪ ነዉ።ክሊንተን የአፍሪቃ ሕብረት መሪዎችን በተለይም በቅርቡ የተመረጡትን የሕብረቱን ኮሚሽን ፕሬዝዳት ድላሚኒ ዙማን ችላ ማለታቸዉን ግን ዶክተር ሲለርስ «አስገራሚ» ብለዉታል።ብቻ ዳካር፥ ጁባ፥ናይሮቢ፥ ሉሉንግዌ፥ ፕሪቶሪያ፥ ካምፓላን ጎብኝተዉ፥ አክራ ላይ ለቅሶ ደርሰዉ ወደ ሐገራቸዉ ይመለሳሉ።
ነጋሽ መሐመድ
ተክሌ የኋላ