1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

የንባብ ባሕላችንን እንዴት እናዳብር?

ሐሙስ፣ ግንቦት 18 2014

የዘመኑ ቴክኖሎጂ በወለደው የኢንተርኔትን በመጠቀም የማንበብ ባሕል ሌላ ቅርጽ ይዞ ብቅ ቢልም ወጣቶች በቴክኖሎጂው አብዛኛው ጊዜያቸውን አጫጭር መረጃዎችን በማንበብ በአካባቢያቸው ስላዩት ወዘተ መረጃዎችን በማንበብና በማጋራት እንደሚያሳልፉት ጥናቶች ይጠቁማሉ።

https://p.dw.com/p/4BqwB
Symbolbild International Book Day, Veröffentlichung von Büchern im Iran
ምስል irna.ir/Hamidreza Torabi Fard

የንባብ ባሕል


ፊደል ተቀርጾ ሃሳብን መገለጽ ከተጀመረበት ጊዜ ጀምሮ የንባብ ባሕል የረዥም ጊዜ ታሪክ አለው። በአገራችን የነበሩ የተለያዩ ነገሥታት የብራና ጽሑፎችን በማሰባሰብ ቤተ መጻሕፍት ያደራጁ እንደነበር የታሪክ ድርሳናት ያትታሉ። ከዘመናዊ ትምህርት እና የህትመት ማሽን መስፋፋት ጋ ተያይዞም የሕትመት ውጤቶች ማንበብ እየተስፋፋ መጥቷል። እንደየዘመኑ ሁኔታ በአገራችን በተለያዩ ጊዚያት የንባብ ባሕል ከፍና ዝቅ ሲል ተስተውሏል። ወርቃማ የንባብ ባሕል ሊባል የሚችል ጊዜ እንደነበርና ከዘመኑ ቴክኖሎጂ ጋ የማንበብ ባህሉም መልክና ቅርጹ እየተቀየረ እንደሆነ በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ የትያትር ጥበባት ረዳት ፕሮፌሰር ነብዩ ባዬ አጫውተውናል።
የቤተ መጻሕፍት እንደልብ አለመገኘት የሕትመት ውጤቶች ዋጋ መናርና ተደራሽ አለመሆን አሁን አሁን ደግሞ ከኢንተርኔት መስፋፋት ጋ በተያያዘ የንባብ ባሕል ቀንሷል የሚሉ ቢኖሩም የዘመኑ ቴክኖሎጂ በወለደው የኢንተርኔትን በመጠቀም የማንበብ ባሕል ሌላ ቅርጽ ይዞ ብቅ ብሏል። ወጣቶች በቴክኖሎጂው አብዛኛው ጊዜያቸውን አጫጭር መረጃዎችን በማንበብ በአካባቢያቸው ስላዩት ወዘተ መረጃዎችን በማንበብና በማጋራት እንደሚያሳልፉት ጥናቶች ይጠቁማሉ በማለት ረዳት ፕሮፌሰር ነብዩ ባዬ ያስረዳሉ።

ሚያዝያ 27 ቀን 1936 ዓ.ም. የተመሠረተውና 75ኛ ዓመቱን የደፈነው  ‹‹ብሔራዊ ቤተ መጻሕፍት ወመዘክር›› ከተቋቋመ ቦኋላ ዘመናዊ ቤተመጽሕፍት በየቦታው እየተቋቋሙ የንባብ ባሕሉ እንዲያድግ የራሱን አስተዋጽአ ማበርከቱን በአወንታዊ ጎኑ ከምስጋና ጋ የሚጠቀስ ነው።
አሁን ካለው የሕዝብ ቁጥር አንጻር በአገራችን ያሉ ቤተ መጻሕፍት እዚህ ግባ የሚባሉ አይደሉም። በመንግሥት በኩል ቤተ መጻሕፍትን ለማስፋፋት የሚደረጉ ጥረቶች ቢኖሩም በቂ እንዳይደሉ ብዙዎች ይስማሙበታል። በተለይ የግል ባለወረቶች በዚህ መስክ እንዲሰማሩ ማትጊያ ከመስጠት አንጻር ገና ያልተሞከረ ነው። ረዳት ፕሮፌሰር ነብዩ ባዬ በጉዳዩ ላይ አጽንኦት ይሰጣሉ።
« ኢትዮጵያ ታንብብ» በሚል መርህ በተለያዩ የአገሪቱ ክፍሎች በተለይም ሕጻናት የማንበብ ባሕል እንዲያዳብሩ የሚደረጉ እንቅስቃሴዎች ሊበረታቱ ይገባል። የነገ አገር ተረካቢዎችና አስተዳዳሪዎች ገና ከህጻንነታቸው ጀምሮ የንባብ ባሕል የሚያዳብሩበት መንገድ ማመቻቸት ትልቁ የወላጆች የቤት ሥራ ሊሆን ይገባል።
 

Temsalet Phenomenal Ethiopian women a book published by TSEHAI Publishers
ምስል TSEHAI Publishers

ዮሐንስ ገብረ እግዚአብሔር 

ሽዋዬ ለገሠ